መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » አትመጣም ወይ ?

የትምህርቱ ርዕስ | አትመጣም ወይ ?

ልጅ በእናቱ ሲጨክን ፣ አባት የወለደውን ለሞት ሲያስብ ፣ ገመና አደባባይ ሲወጣ ፣ ሁሉ ልብላ ባይ ሁኖ ገላጋይ ሲጠፋ ፣ ፍቅር ተቀብሮ ገንዘብ ሲነግሥ ፣ ሰው ረክሶ ንብረት ሲወደድ አትመጣም ወይ ? ራርተህ የማትጨክን ፣ አፍቅረህ የማትጥል ፣ አቅፈህ የማትገፈትር ፣ አበባ ሰጥተህ አፈር የማትበትን አንተ እግዚአብሔር ሆይ አትመጣም ወይ ? ወንዱ ወንድነቱ ፣ ሴትዋ ሴትነትዋ ሲጠፋት ፣ የተሰጠውን ትቶ ያልተሰጠው ላይ ሲባክን ፣ መሰላል ላይ የወጣው ከፍ ያለበትን ሲገፈትር ፣ እህል ያበደሩት አፈር ሲመልስ ፣ ለክፉ ቀን ወዳጅ ክፉ ምላሽ ሲሰጥ ፣ ታሪክ ሲጠፋ ፣ ትዝታ ሲሻር ፣ ልቅሶም ደስታም የግል ብቻ ሲሆን ፣ የሕይወት አጋር ሲታጣ ፣ ግላዊነት ሲነግሥ ማኅበራዊነት ሲናድ ፣ በሞት መንገድ በፍጥነት ሲነዳ አትመጣም ወይ ? ሰው የሚፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገውን የምትሰጥ ፣ የሰውን ፈቃድ በቅዱስ ፈቃድህ የምታርም ፣ የአንድ ቀን መታመንን እንኳ የማትረሳ ፣ ደከሙ ሰነፉ ብለህ የማትገፋ አንተ ቡሩክ እግዚአብሔር አትመጣም ወይ ?

አብሮ አደግ ሲረሳሳ ፣ ባለ ቃል ኪዳን ሲለያይ ፣ ፍቅር እንደ ጠዋት ጤዛ ሲረግፍ ፣ ልቡን አስቀምጦ በጥርሱ የሚያጫውት ሲበዛ ፤ ጠቢብ መጠገን ፣ ፈላስፋ መግለጥ ፣ ሽማግሌ መፍታት ፣ አለቃ መምራት ሲሳነው የምትጠበቀው አንተ ነህ ፣ አትመጣም ወይ ? የባሰ አታምጣ እየተባለ በማያልቅ ይባስ ውስጥ የሰው ልጅ ሲጓዝ ፣ ቋንቋ ተደባልቆ መደማመጥ ሲያቅት ፣ መሬት እንኳ መሸከም አቅቷት ስትንቀጠቀጥ ፣ ወቅታት ሲታወኩ ፣ ተፈጥሮ ሲታመስ ፣ ያንተ ሥራ እየፈረሰ የሰውን ሥራ ለማቆም ትግል ሲበዛ አትመጣም ወይ ? አንተ ቅዱስ ሆይ ፍጹም ሳለህ የሰናፍጭ ቅንጣት እምነትን ከእኛ ትጠይቃለህ ፣ እኛ ጎዶሎ ሳለን ፍጹም ነገር እንፈልጋለን ። ይሆናል አይሆንም ያንተ ቃል ነው ፣ እኛ የማይሆነውን ይሆናል ፣ የሚሆነውን አይሆንም እንላለን ። አዳምን በልጠነው አዳምን እንወቅሳለን ። መከራን እየፈራን ለሰው መከራ ስናሸክም አይሰቀንም ። አትመጣም ወይ ? ሁሉ ይለወጣል አንተ ግን አትለወጥም ። የሰው ተስፋ አጉል ነው ፣ አስቀምጦ የሚቀር ነው ። ያንተ ቃል ግን የማያረጅ ፣ ራሱን ሳያስፈጽም የማይተኛ ነው ። በዚህ አባይ ዘመን አትመጣም ወይ ? እንኳን ድንቁርናው እውቀቱም በሚያስፈራበት በዚህ ጊዜ አትመጣም ወይ ?

እንባ እንባ ሲል እንባም ሲጠፋ ፣ ልብ ደም አርግዞ ውጥረቱ ሲበዛ ፣ ስሜት መግለጫ አጥቶ ሲታመቅ ፣ የማልቀሻ ቦታ ጠፍቶ ሰው የውሸት ሲስቅ ፣ ሁሉም ባለ ጉዳይ ሁኖ አጋዥ ሲጠፋ ፣ የልብን የሚነግሩት የልብ ሰው ሲታጣ ፣ ኖረው እንዳልኖሩ የሚሰማ ስሜት በብዙዎች ውስጥ ሲነግሥ አንተ አትመጣም ወይ ? አጥበህ የምታስጌጥ ፣ አባብለህ የምትሾም ፣ አጽናንተህ የምታቆም አንተ ሆይ አትመጣም ወይ ? ሰው ምን ይችላል ብለህ ነው ዝም ያልከው ? ከእኛ እርምጃ ያንተ ዝምታ ቢበልጥም ግን ጨርሶ ሳይደክመን አትመጣም ወይ ? ሁኔታው ሲጫነን ፣ ነገሩ አልገባ ሲለን እኛን ያስፈራን የማያስፈራህ ፣ ለመፍትሔ የምትደርስ ፣ ከሁኔታው በላይ የሆንህ እግዚአብሔር ሆይ አትመጣም ወይ ? የሃይማኖትን ርስት ትተን ድንበር ድንበሩን ስንዞር ፣ ለራበው ዳቦ እያላስን ረሀቡን ስናፋፍም ፣ ለሞቱት አዝነን ከቆመው ጋር ለሞት ስንፈላለግ ፣ አይዞህ ባይ መሆን አቅቶን ሰብረን ስናደቅ ፣ እንደ ጲላጦስ በአደባባይ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ብለን ስንታጠብ ፣ ለሚጠባበቁን ዝናብ የሌለው ደመና ስንሆን አትመጣም ወይ ? የሠራኸው መጫወቻ ፣ የሞትክለት የሞት ልጅ ሲሆን አትመጣም ወይ ?

አንተ የአንድነት መሠረት ነህ ። አንተ የሌለህበት ጅምር ፣ አንተ ያልቀደምህበት መንገድ ድካም ብቻ ነው ። ሳትሄድ “ቶሎ ና” በሉኝ ያልከው ፣ ትምጻእ መንግሥትከ እያልንህ በልባችን ያለኸው ፣ እመጣለሁ ብለህ ፍጥረትን በተስፋ ያስገዛኸው አትመጣም ወይ ? ይህ ዓለም እንግዲህ ቤት አይሆንም ፣ መኖሪያ አዘጋጅቻለሁ መጥቼም እወስዳችኋለሁ ያልኸው አትመጣም ወይ ?

ትመጣለህ ፣ የሳሳው ዓይናችን ይጠግብሃል ፣ የናፈቀው ልባችን ያገኝሃል ፣ የተጠማው መንፈሳችን ይረካብሃል ። በዝናብ ነጠብጣብ ልክ ምስጋና ላንተ ለእግዚአብሔር ይሁን ። በአሸዋ ቍጥር ልክ ክብር ላንተ ይሁን ። በፀጉራችን ልክ ውዳሴ ላንተ ይሁን ። እየጠበቅንህ ነው አትመጣም ወይ ?

ሰኔ 26 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ