ዘመናዊነት በሃይማኖት ላይ ብዙ ጥርጥርን የሚዘራ ሆኗል ። ሰዎችን ከመንፈሳዊነት ነጻ ለማውጣት የተጀመረ ሥርዓት እስኪመስል ብትን ትውልድን እያፈራ ነው ። ጸሎት በእምነት የሚከናወን በመሆኑ ጥርጥር እጅግ ይጎዳዋል ። ከፍቅር ይልቅ መብትን ፣ ከጸጋ ይልቅ ስሌትን የሚያስበው የእኛ ዘመን ለጸሎት ጀርባውን የሰጠ ይመስላል ። መብቶች ግን መብትን አላስገኙም ። ግለሰቦችም ፣ ገዥዎችም በየዕለቱ መብትን ይነጥቃሉ ። ከሁሉ በላይ የሰው ልጅ የምኞቱ ባሪያ ሁኗል ። በምድር ላይ የሚነሡ ነጻ አውጪዎች ሰውን ከራሱ ክፉ መሻት ሊያድኑት አይችሉም ። በግዳጅ መብታቸው ይጣስ የነበሩ ፣ አሁን ትንሽ ገንዘብ ሲያሳዩአቸው ራሳቸው ነጻነታቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ ። ባርነቱ የተስማማውን ማንም ነጻ ሊያወጣው አይችልም ። ዘመናዊነት ወዴት እየወሰደን እንደሆነ ሳናውቅ ዓይናችንን ጨፍነን እየተከተልነው ነው ። ዓይናችንን የምንገልጠው ምናልባት እገደሉ አፋፍ ላይ ሳይሆን አይቀርም ። ተፈጥሮ በብርቱ ጉዳት ደርሶበታል ፣ ሠዓሊውን የምንጠላው ከሆነ ሥዕሉን መቅደዳችን አይቀርም ። ለእግዚአብሔር ፍቅር አልባ የሆነው ዘመን የሠራውን ተፈጥሮ እያበላሸ ነው ። ባለጠጎችና የምግብ ዋስትና ተከብሮልናል የሚሉ ሕዝቦች የዓመት ቀለብ ስለ ያዙ “የዕለት እንጀራችንን ስጠን” ብለው መጸለይ ያስቃቸዋል ። ጸሎት ግን ለዕለታዊ ፍላጎት ደጅ መጥኛ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረጊያ ነው ።
ልጆቻቸው ሲታመሙ የእግዚአብሔርን ደጃፍ በብርቱ ያንኳኩ የነበሩ ወላጆች ዛሬ ፈጥኖ የሚታያቸው የሕፃናት ሐኪም ቤት ነው ። የልጆቻቸውን በሽታ ጎግል ያደርጋሉ እንጂ እግዚአብሔርን ለመማጸን አቅም ያጡ ብዙ ወላጆች ናቸው ። ወቅቱን ጠብቆ ዝናብ ባይመጣም በመስኖ ሥርዓት ተክሎችን ማሳደግ እንችላለን በሚለው ዘመን ገበሬዎች ስለ ዝናብ እንዳይጸልዩ አድርጓቸዋል ። ዋስትናው ከሌሎች ይልቅ የተሻለ የሚባለው የአየር መጓጓዣ ሰዎች ስለ መንገዳቸው እንዳይጸልዩ እንቅፋት ሆኗቸዋል ። እውነት የሚመስሉ የማኅበራዊ መገናኛ ጓደኞች አጠገባችን ስላለው ሰው ግድ እንዳይለንና እንዳንጸልይለት እንቅፋት ሆነዋል ። ብዙ ሰው አማረልኝ ብሎ የሚናገረው “በዚህ ዘመን ሁሉም ነገር ያለው በእጅህ ላይ ባለው ስልክ ነው” በማለት ነው ። ግን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ውስብስብ ነገሮች በዓለም ላይ ተከሥተዋል ። ዓለምን እየዘወረ ያለው የጦር መሣሪያ የበላይነትና ገንዘብ እንደሆነ እያየን ነው ። ጸሎትን ቢጠቀሙም የጸሎትን መንገድ የሀብት ማግኛ ፣ ጠላትን የመምቻ የምሥጢር ቍጥር አድርገው የሚጠቀሙበትም አሉ ። ጸሎትን በተዉና ጸሎትን ያለ መንገዱ በሚጠቀሙ ሰዎች ምክንያት ከእግዚአብሔር ልናገኘው የሚገባው በረከት እየዘገየ ነው ።
ጸሎት እግዚአብሔርን የምንለውጥበትና አሳብ የምናስቀይርበት መሣሪያ አይደለም ። እኛ የምንለወጥበት ነው ። በጸሎት ውስጥ እግዚአብሔር ሳንጠይቀው ለእኛ የፈጠረውን ድንቅ ነገር እናስተውላለን ። የእግዚአብሔርን ትልቅነት ስለምናይበት የእኛን ደቃቃነት እንገነዘባለን ። በሦስተኛ ደረጃ ችግራችን ከእግዚአብሔር አቅም አንጻር በጣም ትንሽ መሆኑን እንረዳለን ። ጸሎትን በትኩስ ፍቅር ማቅረብ ካልቻልን ጣዕሙን ማግኘት አንችልም ። በልማድ ፣ በአፍ ብቻ በማነብነብ ወደ ጣዕመ ጸሎት መድረስ አይቻልም ። ጸሎት የአማኝ እስትንፋስ ነው ። የሰው ልጅ ያለ አየር ለጥቂት ደቂቃዎች መቆየት አይችልም ። ያለ ጸሎትም ሥጋዊና መንፈሳዊ ህልውናን ጠብቆ መቆየት አይቻልም ። ክርስቲያን ያለ ጸሎት ምውት ነው ። ጸሎትም አንዳንዴ ፣ በሰንበት ቀን ሳይሆን ያለ ማቋረጥ መደረግ አለበት ። አሊያ ሕይወት መጠውለግ ይጀምራል ። ጾምን ከጤና ጋር ፣ ጸሎትን ከሥነ ልቡና ሕክምና አንጻር ማየት መንፈሳዊነት አይደለም ። ጸሎት ከሕያው እግዚአብሔር ጋር ያለን ሕያው ግንኙነት ነው ።
አየር በዙሪያችን ከቦናል ። የእግዚአብሔር በረከትም በዙሪያችን አለ ። ጸሎትም ይህን በረከት በር ከፍቶ የማስገቢያ መንገድ ነው ፣ አፍና አፍንጫውን የዘጋ አየር ማግኘት አይችልም ፣ ጸሎትም ክፍት ልብ ይፈልጋል ። አየር በነጻ ነው ፣ ጸሎትም የጸጋ መንገድ ነው ። አየር ሕይወት ላለው ሁሉ አስፈላጊ ነው ፣ ጸሎትም ሰውንና እንስሳን ፣ ተፈጥሮን በሙሉ መጠበቂያ ነው ። አየር ሁሉም ሰው በቀላሉ የሚስበው ነው ፣ ጸሎትም የተማረና ያልተማረ ሰው በእኩል የሚያደርገው ነው ። በአየር እጥረት የሚሰቃዩ አቅመ ቢስ ናቸው ፣ አእምሮአቸው ተገቢውን ሥራ መሥራት አይችልም ። ሥቃያቸውም የጠና ነው ። የማይጸልይ ሰውም በሁሉም ነገር ደካማ ነው ። አስተሳሰቡ የወደቀ ፣ ውስጣዊ ጥንካሬው በተስፋ ቢስነት የተመታ ነው ። በውስጡ ያለው ሥቃይም ቃላት የሚገልጡት አይደለም ። አባቶቻችን ቀንና ሌሊት በቁመትና በስግደት የለመኑበት ክርስትና ውስጥ ሆነን አምስት ደቂቃ አነብንበን ስንወጣ ማፈር አለብን ። እንዳይቀር የምናደርሰው ጸሎት ግቡን አይመታም ፣ እግዚአብሔር ሌሊቱን ያነጋልን እንዳይቀር ብሎ አይደለም። ተንበርክከን ሰግደን ፣ ከአምላካችን ጋር ሰፊ ጊዜ መነጋገር አለብን ። ጸሎት ሕይወታችንን ፣ ጉዳያችንን ፣ ዓለማችንን ይለውጣል ።
እየጸለያችሁ ነው ? የውስጤን የምነግረው ሰው የለኝም ትላላችሁ ፣ ልስማችሁ የሚለውን አምላክ ግን ገፍታሁ ትሄዳላችሁ ? የእናንተ ባልሆነች እስትንፋስ እየኖራችሁ የእስትንፋሳችሁን ጌታ ገሸሽ ትላላችሁ ። ብቸኝነት በጣም እያጠቃችሁ ነው ፣ መጸለይ ግን ትልቅ ጥንካሬ እንደሚያመጣ አልተረዳችሁም ። ብዙ ምሥጢራችሁን ስለ እናንተ ግድ ለሌላቸው ሰዎች በአደባባይ ታወራላችሁ ፣ በድብቅ ሰምቶ በግልጽ ለሚመልሰው አምላክ ግን ዱዳ ትሆናላችሁ ።
ይህ መንገድ አያዋጣም ጸልዩ! እንጸልይ !
ይቀጥላል
ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም.