አይሆንም አይሰጥህም
ስብከት ለማከናወን በጣም ደስ ይለናል ። በአደባባይ ቆሞ መናገር ያረካናል ። ሰዎችም የዛሬው ትምህርት ልዩ ነው ይላሉ ። ሰባኪውም ቅድሚያ ካልተሰጠው ፣ ሰዓቱን ካሳጠሩበት እየከፋው ይመጣል ። ለመስበክ ፣ የቤተ ክርስቲያን ማስተባበሪያ ሥራዎችን ለመሥራት የምንደሰተውን ያህል ለመጸለይ ደካሞች ነን ። ጸሎት ውጫዊ ሙገሳ ፣ የሰዎችን አድናቆት አያስገኝም ። በዚህ ምክንያት ምስጋና የሚወደው ፣ የሰዎችን ውዳሴ እንደ ተጠማ የሚኖረው ምስኪኑ ሥጋችን ጸሎትን ችላ ይላል ። ቢያደርገውም ያድፋፋዋል እንጂ ከልብ አይከውነውም ። የጸሎት ሕይወታችን ደካማ የሆነው ውዳሴ ከንቱ ስለማያመጣ ነው ። ስለ አገራችን ጸልየን እግዚአብሔር ድንቅ ነገርን አምጥቶ ቢሆን ሰዎች ግን ስለ አገር በአደባባይ ያወሩትን ሰዎች ያደንቃሉ ። እነርሱንም እንደ አርበኛ ይቆጥራሉ ። ዋናውን ሥራ የሠራው ጸሎተኛው ነው ። አዎ ስለ አገሩ ካወራው ስለ አገሩ የጸለየው ይበልጣል ። መጸለዩን ግን እግዚአብሔርና ራሱ ጸሎተኛው ብቻ ያውቁታል ። ልፋቱ በሰው ዘንድ የተደበቀ የሚመስለው ፣ ዋጋውን ከምድር የሚጠብቀው ፣ ፍርፋሪ ምስጋና የሚሻው ፣ አክብሮ ከሚያዋርደው ዓለም ገና ያልተለያየው ሰው ጸሎትን አይመርጥም ።
እግዚአብሔር ጸሎታችንን የሚከለክለን ደስታችን ስለማያስደስተው አይደለም ። ሕፃን ልጅ እሳት ለመንካት በጣም ይመኛል ፣ ወላጆቹ ግን ይከለክሉታል ። በመከልከላቸውም ጠባቂ ስለሆነው ፍቅራቸው እየገለጡ ነው ። እግዚአብሔር በመከልከል ይጠብቀናል ፣ ዕድሜአችንን ያረዝምልናል ። የጸሎት መልስ ብለን የምናስበው እሺ የሚለውን ብቻ ነው ፣ አይሆንም መልስ መሆኑን አልተረዳንም ። የፈለግነው ሁሉ ቢጠን ኖሮ እንኳን የእኛ ፣ የዓለምም ዘመን አይረዝምም ነበር ። ያልተመለሱ ጸሎቶቻችን የመኖራችን ምክንያት ናቸውና መታገሥ አለብን ። አይሆንም የተባልንበትን ጉዳይ በምስጋና መቀበል ያስፈልገናል ። ለእኛ ከሚጠቅመን ነገር የሚከለክል አምላክ የለንም ። ታላላቅ የምንላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ለምነው ያልተፈጸመላቸው ብዙ ናቸው ። ወደ እግዚአብሔር ልብ የቀረቡ ቅዱሳን ሰዎች “ጌታ ሆይ አንተን የሚያስከብርህ ከሆነ ስጠኝ ፣ አንተ የማትከብርበት ከሆነ አትስጠኝ” ብለው ልመናቸውን ያቀርባሉ ። ወደ መንፈሳዊ ብስለት ስንመጣ እግዚአብሔር ያልፈቀደው ነገር የእሳት ጠጠር እንደማፈስ መሆኑ ይገባናል ።
ታላቁ ነቢይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተስፋይቱን ምድር አትወርስም በተባለ ጊዜ እግዚአብሔር እንዲራራለት ለመነ ። የተሰጠው ምላሽ ግን አስደንጋጭ ነው ። “እግዚአብሔር ግን በእናንተ ምክንያት ተቈጣኝ አልሰማኝምም እግዚአብሔርም አለኝ፦ ይበቃሃል በዚህ ነገር ደግመህ አትናገረኝ ። ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርምና።” (ዘዳ. 3፡26)። ይህን የተናገረው ራሱ ሙሴ ነው ። ሙሴ የመሪ ሽኝት እንኳ አልተካሄደለትም ። የራሱን መቃብር ቆፍሮ የሞተ ሰው ነው ። የእግዚአብሔር ሰው ኑሮው እንጂ መቃብሩ ያማረ አይደለም ። ጌታችንን የቀበሩት ሁለት ሰዎች ናቸው ። ነቢዩ ዳዊት ስለ ልጁ ሕመም ጸለየ ፣ ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ ፣ በታላቅ ኀዘን ቢለምንም ልጁ ሞተበት ። እግዚአብሔር ባልሰማው ጊዜ ደስተኛ ነበረ (2ሳሙ. 12 ፡ 16-20)። ጌታችን ለእኛ አርአያ ሊሆን ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ ቢልም አላለፈችም (ማቴ. 26፡39)። ኑሮአችን እንደ ፈቃዱ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ሞታችንም እንደ ፈቃዱ እንዲሆን መጸለይ እንደሚያስፈልገን ሊያስተምረን ነው ። ቅዱስ ጳውሎስ በሕመም ሲሰቃይ እንዲርቅለት ብዙ ጊዜ ጸለየ ። የተሰጠው መልስ ግን አስደናቂ ነው ። “ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ ። እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል ፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።” (2ቆሮ. 12፡8-9)። የዘብዴዎስ ልጆች ዮሐንስና ያዕቆብ ሹመትን በፈለጉ ጊዜ ፣ እናታቸውን ሽማግሌ አድርገው በላኩ ሰዓት የምትለምኑትን አታውቁም ተብለዋል ።
በሌላ መንገድ እከፍልሃለሁ
እግዚአብሔር ጸሎታችንን ባልመለሰ ጊዜ በሌላ መንገድ ግን ይከፍለናል ። ሙሴ ልመናው አልተሰማም ፣ መቃብሩም አልታወቀም ። እስራኤል መቃብሩን ቢያውቁ ኖሮ ሙሴ ከተቀበረበት እንኖራለን ባሉ ነበር ፣ ደግሞም በሰይጣን ማታለል መቃብሩን ያመልኩ ነበር ። ይህን ስፍራ ሰይጣንም አላወቀውም ። ሰይጣንን እንደ አዋቂ መቍጠር አለማወቅ ነው (ይሁዳ. ቁ. 9)። ሙሴ ሞቶ ለሌሎች የአምልኮ ባዕድ ምክንያት አለመሆኑ ክፍያው ነው ። ነቢዩ ዳዊት ልጅ ቢሞትበት ሰሎሞንን የመሰለ ልጅ ቀጥሎ ተሰጠው ። ጌታችን በመሞቱ ዓለም ዳነ ። ቅዱስ ጳውሎስም ሕመሙ ቢጸናበት ሌላ ጸጋ ተጨመረለት ። እግዚአብሔር በሌላ መንገድ ይከፍላል ። ችግሮች እንዲኖሩ የሚፈቀዱት የጸሎት ሰው ሊያደርጉን ነው ። ያለ ሕመም እውነተኛውን ጸሎት ማቅረብ አይቻልም ። የተሰበረ ልብ ለአምልኮ ይረዳል ።
ያላሰብነውን ይሰጠናል
እግዚአብሔር የለመነውን ብቻ ሳይሆን ያለመነውንም ይሰጠናል ። ሙሴ ያለመነውን የሕዝብ መሪነት ተሰጠው ። እግዚአብሔር ግን እያዘጋጀው ነበር ። ዛሬ የምናልፍበት ነገር ለነገ ወንበራችን የዝግጅት ጣቢያ ሊሆን ይችላል ። እመቤታችን አምላክን ለመውለድ አስባም ለምናም አታውቅም ። ወደር የሌለው ጸጋ ተሰጣት ። እግዚአብሔር ለምኜው ለምን አልሰጠኝም ሳይሆን ሳለምነው የሰጠኝ በጣም ትልቅ ነው ብለን ማሰብ አለብን ።
ከሁሉ በላይ ሞታችንን የሰላም እንዲያደርግልን መለመን ይገባናል ። ለሌላውም ሰው ሸክም ሳንሆን ሰላማዊ የእንቅልፍ ሞት እንዲሰጠን መጸለይ ብዙ ጥቅም አለው ። የበሰለ ሰው የሚጸልየው ጸሎት ይህን ነው ፣ ኑሮ እንደ ምንም ይኖራል ፣ ሰላማዊ ሞት ግን ጸጋ ነው !
ተፈጸመ
ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም.