“ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ ፣ መጥተህም ተከተለኝ” የሚለው ቃል ታላቁ ቅዱስ እንጦንስ ሁሉን ትቶ ጌታን የተከተለበት ፣ በረሃ ገብቶ የመነኮሳት አባት የሆነበት ነው (ማቴ. 19 ፡ 21) ። ይህ ቃል ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ፣ አባ ጳኵሚስና ብዙ መነኮሳት ዓለምን የናቁበት ንብረታቸውን ሸጠው ለድሆች የሰጡበት ነው ። ያላቸውን ሁሉ ሸጠው መከተል ለሁሉም ባለጠጎች የተላለፈ መልእክት አይደለም ። አንዳንዶች በሀብታቸው ለእግዚአብሔር አሥራት ፣ ለድሆች ምጽዋት እየሰጡ ለማገልገል ተጠርተዋል ። አንዱ በሰማዕትነት ፣ አንዱ በሰባኪነት ፣ አንዱ ያለውን ሁሉ ሸጦ ለድሆች በመስጠት ፣ ሌላው ከሀብቱ ላይ በመስጠት እግዚአብሔርን ያገለግላሉ ። ጥሪና አገልግሎት ለየራስ ነው ። የሚገርመው ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ሰጥተህ ተከተለኝ የተባለው ሰው ይህን ምክር አልተጠቀመበትም ። እያዘነ ወደ ቤቱ ተመለሰ ። ለእርሱ የተነገረው ቃል የመነኮሳት አባት የሆነውን ቅዱስ እንጦንስን ከዓለም ለየ ። እኛ እየተመከርን የምናፈሰውን ቃል አጠገባችን ተቀምጦ የሚሰማው ሊታነጽበት ይችላል ።
“ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉ የእውቀት ቤት ከሆነችው ከቤተ ክርስቲያን ተቀምጦ የማይማር ፣ አሳቢ አባት ሳለው ራሱን የማይችል ፣ ሊቅ አጠገብ ተቀምጦ የሚያፌዝ ብዙ ሰው አለ ። የሩቁ የሚያከብራቸውን የቅርብ የሚንቃቸው ብዙ ታላላቅ የጸሎትና የምክር ሰዎች አሉ ። ዕድል ያልመጣችበት ጊዜ የለም ፣ ብዙ ሞኞች ግን ዕድል ታልፋቸዋለች ። አገራችንን ብንመለከት የራስዋን ሊቃውንት ታሳድዳለች ፣ የፈረንጅ አማካሪን ግን በውድ ዋጋ ትገዛለች ። ነቢዩ ኤልሳዕ ግያዝ የሚባል ደቀ መዝሙር ነበረው ፣ የሶርያው ትልቅ ባለሥልጣን ወርቅና ብር ከንቱ ነው አያድንም ብሎ ወደ ኤልሳዕ መጥቶ ተፈወሰ ። እጅ መንሻም ለኤልሳዕ መስጠት በፈለገ ጊዜ ኤልሳዕ እምቢ አለው ። ለእግዚአብሔር ሰው መስጠት ተገቢ ነው ፣ ለሠራተኛው ደመወዙ ይገባዋልና አገልጋዩም በጸሎት መቀበል አለበት ።
ንዕማን የተባለው የሶርያ ባለሥልጣን ግን ከአረማውያን ወገን ነበርና ፈውስን በገንዘቡ የገዛው መስሎ እንዳይሰማው ፣ ክብርን ሁሉ ለእግዚአብሔር እንዲሰጥ ፣ ልቡም ለእስራኤል አምላክ እንዲማረክ ኤልሳዕ እምቢ አለው ። ከማያምን ሰው ገንዘብን ሳይሆን ልቡን መቀበል አስፈላጊ ነው ። የእግዚአብሔር ሥራ አማንያን አምነው በሚሰጡት ገንዘብ መከወን አለበት ። የሶርያው ንዕማን ብርና ወርቅን ንቆ ወደ ድሀው ነቢይ ሲመጣ ፣ የነቢዩ ደቀ መዝሙር ግያዝ ግን ብርና ወርቅን በማታለል ሲፈልግ እናያለን ። የገንዘብ ፍቅር ለምጻም ያደርጋል ፣ መልክን ያጠፋል ። ውስጥን ያዥጎረጉራል ። ሚና የሌለው ሰው ያደርጋል ። ስሙ አንቱ ፣ ሥራው ግን አንተ የሆነ ማንነትን ይሰጣል ። ከደቀ መዝሙርነት ጥሪ ያፈናቅላል ። ጌታን እንዲሸጡ ያደርጋል ። ግያዝ የኤልሳዕ ጸጋ የሚያርፍበት ተተኪ ነበረ ፣ ከጸጋ ይልቅ ገንዘብን መረጠ ። ያንን ገንዘብ አልበላውም ፣ መልኩም ጠፋ ። ይሁዳም ታንቆ ሊሞት ፣ ገንዘቡንም በሜዳ ሊበትን ጌታን ሸጠ ። ነቢዩ ኤልያስ ኤልሳዕን የመሰለ በድርብ ጸጋ የሚያገለግል ተማሪ አገኘ ፣ ኤልሳዕ ግን ተተኪ አላገኘም ። ተተኪ ማጣት እውነተኞቹ መምህራንም ይገጥማቸዋል ።
በማቴ. 19 ላይ የምናገኘው ባለጠጋ ለእርሱ የተሰጠውን ምክር በዘመናት የተነሡ አባቶች ተጠቀሙበት ። “ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ ፣ መጥተህም ተከተለኝ” የሚለው ቃል ለነ ቅዱስ እንጦንስ የጥሪ ደወል ነበረ ። አገርን በጸሎታቸው አጥር ሁነው የጠበቅዋት ፣ ቤተ ክርስቲያንን በአገልግሎት ያስከበሩአት ብዙ መናንያን የወጡት በዚህ ቃል ነው ። ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ገዳማት የነበሩ ፣ መነኮሳት እውቀትን ያስፋፉበት ፣ ለተማሪዎች የለቀቁት ስፍራ ነው ። በአገራችንም ገዳማት የፍልስፍና ፣ የቍጥር ትምህርት ፣ የቅኔ ፣ የትርጓሜ ፣ የዜማ ፣ የሥነ ጽሑፍ ፣ የመድኃኒት ቅመማ ፣ የቅርስ ጥበቃ ፣ የደንና የእጽዋት የምርምር ጣቢያ ፣ የፊደል ማስተማርያ ፣ የሥነ ልቡና መታከሚያ ናቸው ። የትምህርት ሚኒስቴር ሳይመጣ በፊት ለሁለት ሺህ ዓመታት ትምህርት ሚኒስቴር ሁና ያገለገለች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት ። ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት የትምህርት ማዕከል የነበሩት ገዳማት ናቸው ። ያ ወጣት ባለጠጋ አዝኖ የሄደበት ቃል ብዙዎች በደስታ ተቀብለውት ለቤተ ክርስቲያን መቀጠል ፣ ለዓለም ሥልጣኔ አስተዋጽኦ ያደረጉበት ነው ። የባለጠግነት ፈተና ምንድነው ?
ሐምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም.