እመጣለሁ ብላ ትቀራለች ፣ ቀረች ሲባል ትመጣለች ። ስትመጣ ሰላምታ ፣ ስትሄድ ስንብት አታውቅም ፣ ዓለም መግቢያና መውጫ የላትም ። ዓለም ዋሾ ! በልብ እየከዳች በአፍ መተማመኛ የምትሰጥ ፣ እወድሃለሁ ያለችውን በርግጥ የምትጠላ ፣ ያከበረችውን የምታዋርድ ፣ የናቃትን የምትሰጋ ፣ ጭር ሲል የማትወድ ፣ በሞቀበት የምትገኝ ፣ የጠገበውን እየተናነቀው የምታጎርስ ፣ የራበውን በጥይት የምትሸኝ ዓለም ዋሾ ናት ።
ዓለም ዋሾ ! ሁለት ቃል የምትናገር ፣ ሁለት ቃል የምታናግር ፣ ያመሰገነችውን ሳትራገም እንቅልፍ የማይዛት ፣ ሲነጋ እንደ ባንዲራ የምትሰቅል ፣ ሲመሽ የምታወርድ ዓለም ዋሾ ናት ። ያላትን የምትደብቅ ፣ የሌላትን አለኝ የምትል ፣ ጉረኝነት የአፍ መጉመጥመጫዋ ፣ አምላክ ላትሆን ከአምላክ የምትለይ ፣ ያረጀውን ሕፃን ነህ ፣ ክርስቲያኑን ሰው እኮ ነህ እያለች ለማረድ የምታሰባ ፣ ክብርን አዋርዳ ገንዘብ የምትከፍል ፣ አካልን አርክሳ ወርቅ የምትሸልም ፣ ሬሳ አስከምራ ሥልጣን የምትሰጥ ፣ ትራስ አቅርባ እንቅልፍ የምትነሣ ፣ ቤት አድላ ደጅ የምታሳድር ፣ ጤናን ነሥታ ዝናን የምትቆልል ዓለም ዋሾ ናት ።
ሲገናኙ መሳቅ ሲለዩ ቦጨቅ ፣ የሰው ሥጋ በጾም በበዓለ ሃምሳ የምታወራርድ የሐሜት ገበታ ፣ ቀን በጨለመበት ላይ መብራት የምታጠፋ ፣ በወደቀው ላይ ምሣር የምታበዛ ፣ የበለው ቤት ፣ የውርደት ቀሚስ ሰፊ ዓለም ዋሾ ናት ። ጃንሆይ ያለችውን ሌባ ሌባ የምትል ፣ ቤተ መንግሥት ያኖረችውን እስር ቤት የምትሰድ ፣ አቡነ ያለችውን ቀሚስ ገልባ የምትሰድብ ፣ ቅዱስ ያለችውን ርኵስ ብላ የምትሰቅል ፣ ሕግ ያላት ወንጀለኛ ፣ ዳኛ ያላት የፍትሕ ቀበኛ ፣ ሰገነት ላይ አውጥታ የምትከሰክስ ፣ አመሏን ለርካሾች የምታወርስ ዓለም ዋሾ ናት ።
ንጋቷ ምሽት ፣ ቀትሯ እኩለ ሌሊት የሚተካው ፣ እንዳማሩ መኖር ፣ እንዳበሩ መቅረት የሌለባት ዓለም ዋሾ ናት ። ተቀጣጥረው የማይገናኙባት ፣ ተነፋፍቀው የሚጣሉባት ፣ ተዋደድኩ ብለው የሚጋደሉባት ፣ ሰርግና ሞት ያለ ወረፋ የሚገናኙባት ፣ ሙሽራው ሬሳ ሁኖ የሚቀበርባት ፣ ለደስታ የተተኮሰው ሰውን የሚገድልባት ፣ ሳቅና እንባ በጠባብ መንገድ የሚገናኙባት ፣ የክብርን ድንበር ሲጨርሱ የውርደት ከተማ የሚደርሱባት ፣ የወጣው ለመግባቱ እርግጠኛ የማይሆንባት ፣ የተኛው ለዘላለም የሚያንቀላፋባት ፣ ለሁሉ ጎዶሎ ቀንን ለመስጠት አድብታ የምትጠብቅ ዓለም ዋሾ ናት ።
የመልክ ሌባ ፣ የቁንጅና ባላጋራ ፣ የጉልበት ሰራቂ ፣ የቦክሰኛው እጅ ሽባ የሚሆንባት ፣ ሯጩ በጋሪ የሚሄድባት ፣ እንዳማሩ መሞት የማይገኝባት ፣ የሰጠችውን እንደ ሕፃን ቶሎ የምትቀበል ዓለም ዋሾ ናት ። አገኘሁ ብለው ተናግረው ሳይጨርሱ ማጣት የሚንኳኳባት ፣ አፈቀርሁ ብለው ምራቅ ሳይደርቅ የሚካሰሱባት ፣ ባልና ሚስት ባላጋራ የሚሆኑባት ፣ ሬሳው ሳይወጣ እያለቀሱ ስለ ውርስ የሚያስቡባት ዓለም ዋሾ ናት ።
ዓለም ዋሾ ! ከተወለዱ ቀን ጀምሮ ወደ ሞት የሚሄዱባት ፣ ጥርስ እየተሰበረ ፣ ዓይን እየደከመ ፣ እጅ እየታሰረ ፣ እግር እየዛለ በየዕለቱ ሞትን የሚለማመዱባት ፣ ማለዳዋ ወደ ሠርክ ፣ ሠርኳ ወደ ጨለማ የሚገሰግስባት ዓለም ዋሾ ናት ። ምንም ቢሰነብቱ መቅረት የሌለባት ፣ ምንም ቢያካብቱ ባዶ እጅ የሚሄዱባት ፣ ሕፃኑን በነጭ ጨርቅ ተቀብላ ፣ ሟቹን በነጭ ከፈን የምትሸኝ ዓለም ዋሾ ናት ። ጦርነትን እያወገዘች የጦር መሣሪያ የምታቀርብ ፣ በአደባባይ እየተሞናሞነች በጓዳ የምታጋድል ፣ ሕጋዊ ውሸት ያላት የዲፕሎማሲ ባለ ቀሚስ ፣ የጋራ ጥቅም እንጂ የጋራ ፍቅር የሌላት ፣ ምን አገኛለሁ እንጂ ምን እሰጣለሁ የማትል ዓለም ዋሾ ናት ። ማለፏ መድኃኒት ፣ ማለፋችን ዕረፍት ነው ። ድንኳን ናትና ዓለም ትፈርሳለች ፣ እውነተኛው ቤታችን በሰማይ ነው ። የወረት ዓለም ሲፈርስ የእውነት ዓለም ይገለጣል ። እርሱም የሰማዩ መንግሥት ነው ።
ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም.