መግቢያ » መጽሐፍ ቅዱስ » አዲስ ኪዳን » የሉቃስ ወንጌል » የኤማሁስ መንገደኞች /ክፍል 2

የትምህርቱ ርዕስ | የኤማሁስ መንገደኞች /ክፍል 2

 “እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር ፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው ።” ሉቃ. 24፡21
በመጽሐፈ መሳፍንት በምዕራፍ 8፡4 ላይ ያለው ቃል በጣም ይገርማል፡- “ጌዴዎንም ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ ደርሶ ተሻገረ ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር” ይላል ። ደክሞ ማሳደድ ፣ ወድቆ ማፍራት ፣ ጠውልጎ ስለ ክርስቶስ መናገር ይኖራል ። መድከማችንን የምናውቀው እኛ ነን ። ጠላት የሚያየው የሚዋጋልን ጌታ የማይደክመው መሆኑን ነው ። እንደ ወደቅን የምናውቀው እኛ ነን ። ቃሉ ግን ትንሣኤና ሕይወት ነው ። መጠውለጋችን ለራሳችን የነገርነው “ደክሞኛል” የሚል ዜና ነው ። ብቻ ስለ ክርስቶስ መናገር ካላቆምን እርሱ አብሮን ይጓዛል ። እግዚአብሔር መድከምን ፣ መውደቅን ፣ መጠውለግን መጨረሻችን አላደረገውምና ምስጋና ይገባዋል ። ከድካማችን የተነሣ አሁንስ ያሳደድሁት ሊያሳድደኝ ነው ስንል ጠላት እየመጡ ነው ብሎ መለከት ይነፋል ። እኛ ድካማችንን ጠላት ብርታታችንን ያወራል ። እኔ ወድቄአለሁ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔርን ሥራ መሥራት አልችልም ስንል ብዙዎች በእኛ ሲነሡ እናያለን ። ጠውልገንና ተሰላችተን ሳለ ግድ ሆኖብን የምንናገረው ዜና ክርስቶስ ብዙዎችን እንዳበረታ  ምስክርነት ስንሰማ እንደነቃለን ። በጸሎት አስቡን ሲሉን ውስጣችን እየሳቀ እሺ እንላለን ፣ ከቀናት በኋላ ጸሎታችሁ ሠመረ ብለው ሰዎች ወደ እኛ ሲመጡ እግዚአብሔር ስለ ስሙ ከእኛ ጋር እየሠራ እንደሆነ ይገባናል ። ዛሬ የምጸልይለት ድውይ አይፈወስም ፣ ምክንያም ጥሩ አይደለሁም ስንል በሽተኛው ዘሎ ይቆማል ። ፈውስ የእኛ ብቃት ማረጋገጫ ሳይሆን እግዚአብሔር ለሚያቃስተው በሽተኛ ያለው ደግነት መሆኑን የምንረዳው ቆይተን ነው ።
የኤማሁስ መንገደኞች ሰንበትን ውለው አርፈው የጀመሩት ጉዞ ቢሆንም ጠውልገው ነበር ። ውስጣቸው ደክሞ ነበርና እግራቸውን ማንሣት አቅቷቸው ፣ በተሰላቸ ድምፀት ስለ ክርስቶስ ሞት ይናገሩ ነበር ። ሰዎች ክርስቶስን ስለ ሰቀሉበት ምክንያታቸው እንጂ ክርስቶስ ስለ ተሰቀለበት የሥላሴ ፈቃድ አልተረዱም ነበር ። ሁሉም ነገር ከምድር ስናየውና ከሰማይ ስናየው ልዩነት አለው ። ተኝተን ብናድርም ፣ ዐርፈን ጉዞ ብንጀምርም ውስጣችን ተስፋ ከቆረጠ አሁንም እንደ ደከምን ነው ። ተኝቶ አለመንቃት ፣ በልቶ አለመበርታት ከተስፋ ጋር የተያያዘ ነው ።
እግዚአብሔር የቆምንበት ስውር እጅ ፣ የምንነሣበት የትንሣኤ ምሥጢር ነው ። የኤማሁስ መንገደኞች ስለ ክርስቶስ ሞት ሲያወሩ ሁለት ሰዎች የሚናገሩ ብቻ አይመስሉም ። የደመቀ ጉባዔ ይመስል ነበር ። ይነጋገሩ ነበርና ሁለቱም አድማጭም ተናጋሪም ነበሩ ። ይመራመሩም ነበረ ። ለምንና እንዴት እያሉ ይጠይቁ ነበር ። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ አብሮአቸው ሦስተኛ ሁኖ ይጓዝ ነበር ። እነርሱ ግን ልብ አላሉትም ነበር ። እንዳያዩት ዓይናቸው ተይዞ ነበር ። እርሱን ዓይናማዎች ፣ አሻግረው የማየት አቅም ያላቸው ሳይሆን የሚያምኑ ብቻ ያዩታል ። ጉዞአቸው ወደ ፀሐይ መጥለቂያ በመሆኑ ምንም ነገር እንዳያዩ ተሰናበቿ ፀሐይ ጋርዳቸው ነበር ። ሁሉም ነገር አብቅቷል በሚል ስሜት ተስፋቸው ልትጠልቅ ተቃርባ ነበር ። ተስፋ መቍረጥና ጨለማ ሁለቱ ከባድ ናቸው ። ወደ ሁለቱም ይጓዙ ነበር ። ተስፋ የቆረጡ ልጆቹ ባያዩትም ክርስቶስ አብሯቸው ይጓዛል ። ምክንያም ሰይጣን ተስፋ የቆረጡትን በጣቱ ወደ ሲኦል ቢገፋቸው ጥልቁ ላይ ይገኛሉ ። ተስፋ መቍረጥ ለሰይጣን በፈቃድ እጅን  መስጠት ነው ።
ትሑቱ ጌታ ንግግራቸውን በትሕትና አቋረጠ ። ስለ እርሱ ከመናገሩ በፊት ስለ እርሱ እንዲናገሩ ፈቀደ ። ስለ እርሱ የሚናገሩት ጨለማ ያጠላበት ቢሆንም እርሱ ግን ተሸናፊ አይደለሁም ብሎ ቸኩሎ ራሱን አላስተዋወቀም ። እግዚአብሔር የማይቸኩለው የሚሰጋው ነገር ስለሌለ ነው ። “እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው ? አላቸው ።” የልባቸው ብሎን እንደ ላላ ፣ ለመበተን እንደ ተቃረቡ ተረድቷል ። እኛን ሳያስፈቅድ ልባችንን የማየት አቅም አለው ። ልባችን የእርሱ ነበር ፣ ቀጥሎ ሁለት ቁልፍ ቀርፆ አንዱን በእጁ ሲይዝ አንዱን ለእኛ ሰጠን ። መጠውለጋቸው በፀሐይ ትኩሳት አልነበረም ፣ ሰዓቱ ሠርክ ነውና ። መጠውለጋቸው የመንገድ ድካም የወለደው አልነበረም ። ተስፋ መቍረጥ ጉልበታቸውን መትቶባቸው ፣ ፊታቸውን አጨልሞባቸው ነበር ። ተስፋ የሚሰጠውን ማማር አጥተውት ነበርና አዘነላቸው ።
“ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው።” ለቀባሪው አረዱት የተባለው ተፈጸመ ። እርሱ በርግጥም እንግዳ ነበረ ፣ ዓለም ግን አልተቀበለችውም ። ሲወለድም በበረት የተወለደ ትልቅ እንግዳ ነበር ። ሰዎች ልባቸውን ዘግተውበት መስቀል ላይ የዋለ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ትተውት ቢሸሹም የአባትነት መነሻ የሆነው እግዚአብሔር አብ ከእርሱ ጋር ነው ። ብቸኝነት ያለ እግዚአብሔር መኖር እንጂ ያለ ሰው መኖር አይደለም ። ከብቸኝነት የማይሻሉ ፣ ከባዶ ቤት ከፍ የማይሉ ሰዎች አሉ ። ኖረው የሌሉ ፣ ተገኝተው የሚያደክሙ ፣ ራሳቸውን እንጂ ስሜታችንን ለማዳመጥ ያልታደሉ አሉ ። መጠውለግን የሚያነብ ፣ ስሜትን የሚረዳ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ሰዎች ጋር ለመኖር ስሜትን መቆጣጠር ግድ ነው ። ከነሐቃችን የሚቀበለን መድኃኔ ዓለም ብቻ ነው ። ራሳችንን በሸሸን ሰዓት የተቀበለን እርሱ ነው ። ራሳችንን ለማየት ባፈርን ጊዜ በእቅፉ ያረጋጋን አማኑኤል ነው ። በርግጥ ጌታ አላውቅም ያለው አንድ ነገር አለ ። ጠላት እስከ ዘለቄታው ማሸነፉን ጌታ አያውቅም ። እርሱ እያወቀ እንዳላወቀ አብሮን ይጓዛል ። የእኛን መንገድ ስንጨርስ ወደ እርሱ መንገድ እንደምንመለስ ተስፋ በማድረግ በሙከራዎቻችን ሁሉ በዝግታ ያየናል ።
“እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው ። እነርሱም እንዲህ አሉት ። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ፤ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር ፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው ። ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፡- ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር ። ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም ።”
እግዚአብሔር ስለ እግዚአብሔር ጠየቀ ። ሊተርክ የሚገባው ሟች ሲተረክለት ሰማ ። መሥዋዕት ሁሉ በዝምታው ሲናገር ይኖራል ። አንድ መሥዋዕት ብቻ ነባቢ/ተናጋሪ ነው ። እርሱም ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ነው ። እምነት ማለት ዓለምን ኰንኖ ክርስቶስን ማጽደቅ ነውና ክርስቶስን አክብረው ዓለምን ወቀሱ ። በሰው ፊት ብርቱ የሆኑ አሉ ፣ በእግዚአብሔር ፊት ግን የተናቁ ብዙ ነገሥታትን እናውቃለን ። ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ብርቱ ነበረ ። ብርታቱ የቃሉ ትምህርት የእጁ ተአምራት ነው ። ሌላ ብርታት አለው ፣ ስለ ጠላቶቹ ቤዛ የሆነ ነው ። ይህን ብርታት አላወቁም ነበረ ። እስራኤልን ነጻ ያወጣል ብለው ጠብቀውት ነበረ ፣ እርሱ ግን የመጣው መላው ዓለምን ነጻ ለማውጣት ነው ። እርሱ የነፍስ ነጻ አውጪ ነው ። የመነሣቱን ዜና ቢሰሙም ፣ መቃብሩ ባዶ መሆኑን ሌሎች ቢያረጋግጡላቸውም እነርሱ ግን አላመኑም ነበር ። አለማመን ተስፋ አስቆረጣቸው ። ወደ መኖሪያ ከተማቸው እንዲሄዱ አደረጋቸው ። የተዉትን መጀመር ፣ የጀመሩትን መተው ከተስፋ መቍረጥ ውስጥ ይወጣል ። ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው የተዉትን ሱስ ጀምረዋል ፣ የጀመሩትን ወንጌል ጥለዋል ።
“እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ” በማለት ገሠጻቸው ። ተግሣጹን ስለ ተቀበሉ ቀጣዩን ምሥጢር አወቁ ። የክርስቶስ ሞት ገዳዮች መግደል ስለቻሉ ያከናወኑት ሳይሆን መላው ብሉይ ኪዳን እውነት የሆነበት ነው ። ምክንያቱም በተስፋ ፣ በምሳሌ ፣ በመሥዋዕት ፣ በትንቢት ፣ በክህነት ፣ በመቅደስ የክርስቶስ ሞት ሲነገር ኑሯልና ። የገላትያ ሰዎችም የተሰቀለውን ክርስቶስ ስለ ረሱ የማታስተውሉ ተብለዋል ። የማያስተውሉ የሚባሉት ንግድ ያልገባቸው ሳይሆኑ ክርስቶስ ያልገባቸው ወይም ለመስቀሉ ጀርባቸውን ለዓለም ፊታቸውን የሰጡ ናቸው ። በመንፈስ ጀምሮ በሥጋ መጨረስ አለማስተዋል ነው ።
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ተረጎመላቸው ። ባያውቁትም እርሱ ግን ያውቃቸው ነበር ። የአማኝ ዋስትናውም በእግዚአብሔር መታወቁ ነው ። የመንግሥተ ሰማያት ደስታም እግዚአብሔር እኛን ማወቁ ነው ። እነርሱም እንግዳ ነው ሳይሉ ፣ አናውቀውም በማለት ሳይገፉት ፣ ለእምነታቸው አስቧልና ለሥጋው አሰቡለት ። “ከእኛ ጋር እደር ፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል” ብለው ግድ አሉት ፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ ። ይህ ተማጽኖ ከዚያ ዘመን ይልቅ ዛሬ ያስፈልጋል ። ማታው እየቀረበ ፣ ቀኑ እየመሸ ነውና አብሮን ቢያድር መልካም ነው ። የጨለማ ወዳጅ እርሱ ብቻ ነውና ። የሚያስፈራንን የሚያስፈራው ስለ እኛ የሚዋጋው ጌታ ብቻ ነው ።
በቤታቸው የአባወራው ወንበር ላይ አስቀመጡት ። አባወራው መባረክ የሚገባውን ማዕድ እንዲባርክ ጋበዙት ። እንግዳውን አከበሩት ። ትልቅነታቸውን ለእርሱ ተዉለት ። በቤታቸው ሾሙት ። እርሱም እንጀራውን ባርኮ ሲሰጣቸው ዓይኖቻቸው ተከፈቱ ። ጠውልገው የነበሩ እንደገና ታደሱ ። ደክሟቸው የነበሩ እንደገና ተነሡ ። የምሥራቹን ይዞ ማደር ነውር ነው ብለው አሰቡ ። ለአሥራ አንድ ኪሎ ሜትር የዛሉ እንደገና ተመለሱ ። ቅድም በዝለት አሁን በብርታት ። ቅድም በተስፋ መቍረጥ አሁን በተስፋ ተመለሱ ። ክርስቶስን ሲያገኙ እንደ እነርሱ አዝነው የነበሩት ደቀ መዛሙርት ትዝ አሏቸው ። በበረቱበት ምሥጢር ሊያበረቱአቸው ተመለሱ ። ቀኑ ሳይመሽ ከጌታቸው ጋር ታረቁ ። በቍጣችሁ ፀሐይ አይጥለቅ ያለው በተስፋ መቍረጣችሁም ፀሐይ አይጥለቅ ይላል ። በዋሉበት ስሜት እንዳያድሩ አዳምን በምሽት የፈለገ ፣ ሲመሽ ደረሰላቸው ።
ዛሬም ሰው ያሸነፈ መስሎአችሁ ያዘናችሁ ፣ የውግረት ድንጋይ ቀና አላደርግ ብሎአችሁ በካብ ውስጥ የምታጣጥሩ ክርስቶስ ተነሥቷል ። ወደ ኤማሁስ በዝለት የሄዳችሁ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ ። ኢየሩሳሌም የገዳዮች ሳይሆን የምስክሮች ቤት ናት ። ወደ ፀሐይ መጥለቂያ ጉዞ የጀመራችሁ ፣ እየተናገራችሁ እንኳ እግዚአብሔር ትቶኛል የምትሉ ይህች ጀንበር ሳትጠልቅ ተመለሱ ። ክርስቶስ ተነሥቷል ። ኢየሩሳሌምን ለክፉዎች አትልቀቁ ። እውነት ብታጎነብስም አትሰበርም ።
ጸሎት
ተስፋ ያደረግሁት ባይሆንም ተስፋ የሆንከው አንተ አምላኬ ግን ካጠገቤ ነህ ። አንተ እያለኸኝ ዓለም ጎደለብኝ ማለቴ ነውር ነው ። ከቤት ውጭ ያሉ ሳቆች በቤት ውስጥ የሉም ። እቤት ያልጀመሩ ደግነቶች ከተማውን ሞልተውታል ። የእይታ እንጂ የእውነታ ሰው መሆን ርቆኛል ። እግዚአብሔር ሆይ ፣ በተስፋህ እንደገና አንሣኝ ። ተስፋ አዳምን 5500 ዘመን አኖረው ። ተስፋ በዋዜማውም በበዓሉም ደስታ ነው ። እንዲሁ በተስፋ ደስ አሰኘኝ ። መነሣትህ መነሣቴ ይሁንልኝ ። በከበረው ደምህ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 7/ለ
ሚያዝያ 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም