የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምስክር ያሉት ሲከስስ

“እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው።” ቊ. 45
ልጆች እንዲሁ አያድጉም ። ዛሬ አድገው ሲታዩ እንዲህ የነበሩ ይመስላል ። የዛሬው ጽዳት ትላንት ብዙ ቆሻሻ ነበረው ። የዛሬው ቀልጣፋ ንግግር ፣ ትላንት ብዙ ኮልታፋነት ነበረው ። የዛሬው ፍጹምነት ፈላጊ ትላንት ብዙ ስህተት ነበረው ። ልጆች ሲወፍሩ ወላጆች እየከሱ ፣ ልጆች ሲቀሉ ወላጆች እየጠቆሩ ፣ የልጅ ፊት ሲጠራ የወላጆች ፊት ማድያት እየወረረው ነው ። ከሚገለጠው ፍቅር ወላጅ መግለጥ የማይችለው የተሰወረ ፍቅር አለ ። ከሚያደርገው በጎነት ወላጅ አቅም አንሶት ያላደረገው ደግነት ይበልጣል ። ልጅ ከወለዱ ጀምሮ ወላጆችን ያስረሳው ወላጅነት ፣ ወዳጆችን ደህና ሰንበቱ ያለ እናት አባትነት ፣ ትልቁን ኩራት በትንሹ ሕጻን ውስጥ እጥፍጥፍ አድርጎ የከተተ ያ ሞግዚትነት በልጁ ላይ ብዙ ተስፋ አለው ። ተስፋ ስላለው ልጁን ጋርዶ ለማሳደግ አጥሩን ከፍ ያደርጋል ። የሁሉ ልጅ ባለጌ የእርሱ ልጅ ጨዋ ሁኖ ይታየዋል ። ልጁ የማያድግ የሁል ጊዜ ማሙሽ ይመስለዋል ። 24 ሰዓት ዘበኝነት ፣ ከልጅ ጋር ከፍ ዝቅ ሲሉ መዋል በውስጡ ብዙ ራእይ አለው። ልጅ በወላጆቹ ላይ ራእይ ባይኖረው ፣ ወላጆች ግን በልጃቸው ላይ ራእይ አላቸው ። ያ እንደ ሕጻን ብቻ ሳይሆን እንደ ልዑል ያደገው ልጅ ፣ ማሙሽ ተኝቷል ዝም በሉ የተባለለት እንቅልፋም ፣ ዛሬ ነቅቶ እርሱ እንቅልፍ ይነሣል ። የመከሩትን ወላጆች ተዉኝ በነጻነት ልኑር ይላል ። የቀጡትን ወላጆች ያን ጊዜ ጎድታችሁኛል ይላል ። የዘመናት ቅያሜውን ያወጣዋል ። በአቅም ማነስ እሺ ያለበትን ነገር አሁን አቅም አለኝ እንቢ ማለት ይጀምራል ።
“የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል” እንዲሉ ወላጅ በሌሎች ያየው የነበረው የድንበሩ ወይም የሩቁ ችግር የቤት ይሆናል ። የጫፉ ዕይታ የቅርብ ይሆናል ። በዜና የሚሰማው በገህድ የሚታይ ይሆናል ። ሽማግሌ ይጠራል ። ልጄ ሊያሳብደኝ ነው ይባላል ። ትንሹ ልጅ ትልቅ ሁኗልና ጆሮው የማይቆነጠጥ ፣ ዝምተኛው ተናጋሪ ሁኗልና አፉ የማይበርድ ይሆናል ። ልጅ ነው አያውቅም የተባለው ፣ በሕጻንነቱ ያየው ነው ረስቶታል የተባለው ጉዳይ አድጎ ገዝፎ የተቀበረው ከመቃብር ወጥቶ ብቅ ይላል ። ሽማግሌዎቹ ሲወለድ ያዩ እንዲህ ይላሉ ፡- አባትህ እኮ አንተ ከተወለድህ ጀምሮ ብዙ መከራ ተቀብሏል ፣ የእናትህ ስኳር የጀመረው አንተ ከተወለድህ ጊዜ ጀምሮ ነው ይሉታል ። ያበጠው ልጅ መተንፈስ ያቅተዋል ። ጨረቃ ላይ የወጣው የትላንቱ ማሙሽ ሁሉ ሰው ትቢያ ይመስለዋል ። እሺ እኔም ልናገር ብሎ የክሱን መዓት ሲደረድር ወላጆች ኩምሽሽ ይላሉ ። እሳት የማይገባው የተስፋቸው ገመድ መበጣጠስ ይጀምራል ። ይመሰክርልኛል ያሉት ልጅ ላለፉት ሃያ ዓመታት በልባቸው የተመኩበት አፉ ይከስሳቸዋል ። ትልቅ ናዳ ፣ የድንጋይ በረዶ ፣ የበጋ መብረቅ ይወድቅባቸዋል ። ጥላ ያሉት ልጅ ዋዕይ ፣ ከለላ ያሉት ልጅ ወጨፎ ፣ ዓይኔ ያሉት ልጅ ዓይን አውጣ ፣ ምስክር ያሉት ልጅ ከሳሽ ይሆናል ። ያች ቀን ከባድና ቆይታ ግን የምትረሳ ናት ። ልጅ ልጅ ነዋ ።
ለዘመናት  የተመኩበት ሙሴ ፣ ክርስቶስን የገፉበት ያ ምስክር ያሉት ነቢይ ፣ ክርስቶስን የከሰሱበት አንቀጽ ያ መስፍን ፣ መዳንን ገሸሽ ያሉበት ያ ዐቃቤ ሕግ አሁን ከሳሽ ሁኖ ሲመጣ ፣ በማያልፍ ዓለም በድላችኋል ሲላቸው ከባድና የማይካስ ጉዳት ነው ። ክርስቶስን ማጣት ሙሴንም ማጣት ነው ። ሙሴን ማክበር ማለትም ክርስቶስን ማመን ነው ። “እኔን የወደደ ካንገት ልጄን የወደደ ካንጀት” እንዲሉ ሙሴም እኔም የወደደ ካንገት ክርስቶስን የወደደ ካንጀት ወደደኝ ማለቱ እሙን ነው ።
አይሁድ በሚመጣው ዓለም ሙሴ ምስክር ይሆንልናል ብለው ያስባሉ ። ሙሴንም ለማስደሰት ብለው ክርስቶስን ይቃወማሉ ። ሳያውቁት ግን ሙሴ የታዘዘውን ጌታ ይገፋሉ ። ሙሴን የጠራውን ጌታ ይጥላሉ ። ያለና የሚኖር እኔ ነኝ ብሎ ለሙሴ ስሙን ያወጀውን ይሙት ይላሉ ። ለካ ክርስቶስን መግፋት ነቢያትን መግፋት ነው ። ነቢያት ፣ ነቢያት የተባሉት ስለ ክርስቶስ ስለተናገሩ ነው ።
ክርስቶስ ለሚያምኑት የመዳን ማኅተም እንደሆነ ለሚክዱት ደግሞ የኩነኔ አንቀጽ ነው ። ክርስቶስን ስንገፋ ነቢያት ሐዋርያት ብቻ ሳይሆኑ የገዛ ልባችንም ይከዳናል ። አባቶች ሁሉ በዘመናት መናፍቃንን የተከላከሉበት ሚዛናቸው ፡-
·       የክርስቶስን አምላክነትና ጌትነት ይነካል ወይ ?
·     መዳንን ያሳጣናል ወይ ? በማለት ነው ። አንድ ሰው መናፍቅ ፣ ከሃዲ የሚያሰኘው ዋነኛው ምክንያት በክርስቶስ አምላክነትና ጌትነት ላይ ጥርጣሬ ሲኖረውና ያንንም ሲያስተላለፍ ነው ።
 ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸው ታላላቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔያት የኒቅያ ፣ የቊስጥንጥንያና የኤፌሶን ጉባኤ ናቸው ። እነዚህ ጉባዔት ሁለቱ በዋናነት በክርስቶስ ላይ ለተነሣው የስህተት ትምህርት ምላሽ የሰጡ ውግዘት ያስተላለፉ ናቸው ። የኒቅያ ጉባዔ አርዮስ ወልድ ፍጡር በማለቱ ፣ የኤፌሶን ጉባዔ ንስጥሮስ ከማርያም የተወለደው ሰው ነው በማለቱ ነው ። ክርስቶስን የማያምን በእርሱም የሚያፍር የተራቆተ ፣ በአደባባይም የወደቀ ሰው ነው ። የሚያነሣውን ጌታ ክዷልና የሚያነሣው ፣ የሚያነጻውን ትቷልና የሚቀድሰው አያገኝም ። ከቤተ ክርስቲያንም የተለየ ነው ። ለቤተ ክርስቲያን ሚዛኗም ወርቋም ክርስቶስ ነው ። ሚዛኑም ወርቁም እንዳይጠፋብን እግዚአብሔር ይርዳን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ