የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዓለሙን አፈቀረ

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” /ዮሐ. 3፡16/፡
ራስን መካድ በክርስትናው ትልቅና የማይታለፍ መርሕ ነው ፡፡ በክርስቶስ ለማመን ራስን መካድ ያስፈልጋል ፡፡ በማመን ውስጥ መካድ አለ ፡፡ አንድ ነገርን ያመነው አንድ ነገርን ክደን ነው ፡፡ ክርስቶስን ለማመንም ራስን መካድ ግድ ይላል፡፡ የዘላለም ሕይወት ያለው ክርስቶስን በማመን ነው ፡፡ አንድ ዓለት ላይ ብንቆም የሚችለን ስላመነው ሳይሆን ባለ አቅም ስለሆነ ነው ፡፡ ታዲያ ማመናችን እርሱን አይጠቅመውም ፡፡ እኛን ግን ከረግረግ ወጥተን እግሮቻችን እንዲጸኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ እንዲሁም የግል እምነታችን ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም ፡፡ የምናምንበት ነገር ለመታመን የሚበቃ መሆን አለበት ፡፡ እኛን ለመሸከም ጽኑ መሆን ያስፈልገዋል ፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ መታመን የሚገባውና የመታመንን ዋጋ ላመኑት መስጠት የሚችል ነው ፡፡ ባናምነው ታማኝ ሆኖ ይኖራል ፡፡ ብናምነው ግን ክብር እናገኛለን ፡፡ አንድን ንጉሥ ባንቀበለው ለእኛ ይቀርብናል እንጂ አለመቀበላችን ንጉሥነቱን አያስቀረውም ፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ ባናምነው ንጉሥ ሁኖ ይኖራል እንጂ ክብሩ አይቀንስም ፡፡ ለእኛ ግን ባለሟልነትና ክብር ይቀርብናል ፡፡ የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኘው እምነት በክርስቶስ ማመን ነው ፡፡ ባለንበት ዘመን ሰዎች በራሳቸው ያምናሉ ፡፡ ወይም እምነታቸውን ያምናሉ ፡፡ እንዲህ ይሆንልኛል ብትል ይሆንልሃል ፣ ይህ የእኔ ነው ብትል ያንተ ይሆናል የሚል አስተሳሰብ ይዘው ይገኛሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ወንጌልን ለምድራዊ ብልጽግና ብቻ እንዲፈልጓት አድርጓቸዋል ፡፡ በራስ እምነት ማመን ምድራዊ ነገርን ብቻ እንድንከጅል ሲያደርግ በክርስቶስ ማመን ብቻ የዘላለም ሕይወትን ያውጅልናል ፡፡
 በምድር ላይ ስለ ሰማይ ዋስትና የሚሰጥ እምነት በክርስቶስ ማመን ብቻ ነው ፡፡ ብዙ እምነቶች ያንተ ዕጣ የሚለየው በሰማይ ነው ብለው ያስባሉ ፡፡ ወንጌል ግን በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው በማለት በመጪ ሳይሆን በአሁን ድምፅ ያረጋግጥልናል ፡፡ ይኖረዋል ሳይሆን አለው በማለት ተጨባጭ ያደርግልናል ፡፡ የታላላቅ እምነት መሪዎች የዘላለም ሕይወትን በእርግጠኝነት ማብሰር አልቻሉም ፡፡ አሁን ያለነው ምድር ነው ፤ የምናውቀው የአሁኑን ነው ፡፡ ሰማይ ስንሄድ ስለ ሰማይ እናውቃለን በማለት ብቻ ጠያቂዎቻቸውን አሰናብተዋል ፡፡ የዘላለም ሕይወትን በእርግጠኝነት የሰበከው ክርስቶስ ብቻ ነው ፡፡ ይህን ቃል የተናገረው ለኒቆዲሞስ ነው ፡፡ ልጅነትና የዘላለም ሕይወት ምን አገናኘው? ስንል ልጅ ወራሽ በመሆኑ ነው ፡፡ ምድራዊ አባት የሞት ገደብ ያለበት በመሆኑ ምድራዊ ነገርን ብቻ ያወርሳል ፡፡ ሰማያዊ አባት ደግሞ ሕያው ሲሆን የዘላለም ሕይወትን ያወርሳል ፡፡ እግዚአብሔር መንግሥቱን በልጅነት እንድናገኝ የፈለገው አቅማችንን አይቶ ነው ፡፡ ባሪያ የቱንም ያህል ቢሠራ ደሞዝ እንጂ ውርስ አያገኝም ፡፡ ልጅ ግን በልጅነቱ ብቻ ወራሽ ነው ፡፡
እግዚአብሔር ዓለሙን ሁሉ አፈቀረ ፣ ዓለሙ እንዲድንም ፈቀደ ፡፡ እግዚአብሔር አብ አንድ ልጁን ወደ ዓለም የላከው የወደቀውን አዳም ለማንሣት ነው ፡፡ በአዳም ውስጥ ደግሞ ፍጥረት ሁሉ አብሮ ወድቋል ፡፡ ስለዚህ አዳም ሲነሣ ፍጥረት ሁሉ ይነሣል ፡፡ ቅድመ ውሳኔን የሚመለከት አስቀድመው ለጽድቅና ለኩነኔ የተመደቡ አሉ የሚል አሳብ የሚያራምዱ ሰዎች አሉ ፡፡ ለዚህ የሚያቀርቡት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ባሻገር አንድ የትሕትና አሳብም አለ ፡፡ ከእኔ ይልቅ የተሻለ ቅድስናና ትጋት ያላቸው ወደዚህ ሳይደርሱ እኔ መድረሴ አስገራሚና የእርሱ ብቻ ምርጫ ነው የሚል ነው ፡፡ ቅድመ ውሳኔ እርግጥ ከሆነ ሰዎችን ለኃጢአት የሚያነሣሣ ነው ፡፡ በጎ የመሥራት ፍላጎታቸውንም የሚገድል ነው ፡፡ ምክንያቱም ሰውዬው ክፉም ሠራ በጎ የሚጸናው የእግዚአብሔር ምርጫ ነውና ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ፡-
1-  በጎዎች የክፋትን ድንበር እንዲጥሱ ክፉዎች ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለሱ ያደርጋል ፡፡
2-  እግዚአብሔር አስቀድሞ ለወሰነው ነገር ነቢያት ሐዋርያትን ሊቃውንትን በመላክ ለምን ያደክማቸዋል?
3-  ክርስቶስ ዳግመኛ ለፍርድ ለምን ይመጣል? ምክንያቱም ሰዎች እርሱ ሁኑ ያቸውን በአቅማቸው መለወጥ አይችሉምና ፡፡ ደግሞስ መድቦ ወስኖ እንዴት ለፍርድ ይመጣል ?ተጠያቂነት በሌለበት ፍርድ የለምና ፡፡
4-  እግዚአብሔር ከነጻ ፈቃድ ጋር ፈጠረን ብለን መናገር እንዴት እንችላለን?ምርጫ በሌለበት ነጻነት ጥቅም የለውምና ፡፡
5-  ከሁሉ በላይ አንድ ጊዜ ተመርጫለሁ የሚሉ ዘላኖችንና አንድ ጊዜ ተመድቤአለሁ ብለው በኃጢአታቸው የሚገፉ ሰዎችን ያተርፋል ፡፡
6-  የስብከተ ወንጌል ጉዞን ልምሾ ያደርጋል ፡፡
7-  የክርስቶስ ሞት ዓለምን አይወክልም የሚል ክህደት ያመጣል ፡፡ ቃሉ ዓለሙን እንዲሁ አፈቀረ ዓለሙን እንዲድን ልጁን ላከ ይላልና /ዮሐ. 3፡16-17/፡፡
ቅድመ ውሳኔን በሚመለከት የሚነሡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እስኪ እንመልከት፡-
1-  “ያዕቆብንምወደድሁ፥ዔሳውንምጠላሁ” /ሚልክ. 1፡2/፡፡ የእስራኤል ልጆች የእግዚአብሔርን ፍቅር ባለመገንዘብ መንፈሳዊ ተግባራቸውን በግዴለሽነት ይፈጽሙ ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ወድጄአችኋለሁ ሲላቸው በምን ወደድከን? በማለት ከራሳቸው የሆነ ምክንያት ይፈልጉ ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ግን የልጅነት ዘመናቸውን በማስታወስ ያዕቆብን ወደድሁ በማለት ይናገራል ፡፡ ያዕቆብና ዔሣው ሁለቱም የይስሐቅ ልጆች ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር ግን የያዕቆብን የኑሮ ፍሬ መሰከረ ፡፡ ያዕቆብን ወደድሁ ዔሣውን ጠላሁ ያለው መቼ ነው ? ያዕቆብና ዔሣው ካለፉ በኋላ ነው ፡፡ ይህን ቃል የተናገረው ቅድመ ክርስቶስ 400 ዓመት ላይ በነቢዩ በሚልክያስ ነው ፡፡ ያዕቆብና ዔሣው የነበሩት ቅድመ ክርስቶስ 1700 ዓመት ገደማ ነው ፡፡ ስለዚህ ያዕቆብን ወደድሁ ዔሣውን ጠላሁ ያለው ኑሮአቸው ተፈትኖ ካበቃ ከ1300 ዓመታት በኋላ ነው ፡፡ ትንቢተ ሚልክያስን ስናይ እንዲመለሱ እንጂ ተወዳችኋልና እንደ ፈለጋችሁ ኑሩ የሚል የኃጢአት ዋስትና ያለው አይደለም ፡፡
2-  “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ የሚመጣ የለም ፣ እኔም በመጨረሻ ቀን አስነሣዋለሁ” /ዮሐ. 6፡44/ ፡፡ ይህን ቃል በመጥቀስ እግዚአብሔር ያልሰበው ወደ እግዚአብሔር ሊመጣ አይችልም ስለዚህ የሳባቸው ወገኖች አሉ የሚል አስተሳሰብ የሚይዙ ወገኖች አሉ ፡፡ ዮሐንስ ምዕራፍ 6 ስለሦስት ዓይነት ምግብ የሚናገር ነው ፡፡ ስለ ተአምራት ምግብ ፣ ስለ መናና ስለዘላለም እንጀራ የሚናገር ክፍል ነው ፡፡ የዕለት እንጀራን በተአምራት የመገባቸው ሰዎች ምነው እንደ እስራኤል ዐርባ ዓመት ሳንሠራ ቢመግበን በሚል ስሜት ጌታን መከተል ፈለጉ ፡፡ ጌታም ከዕለትም እንጀራ ከዘመናትም መና የሚበልጥ አንድ ምግብ እንዳለ እርሱም ራሱ መሆኑን ገለጠላቸው ፡፡ እነርሱ ግን የዕለት እንጀራ ቢያበረክትላቸው እናንግሥህ እናዳላሉ አሁን ደግሞ እንውገርህ አሉ ፡፡ ጌታም ይህን ምግብ ለማግኘት የአብ ፍቅር የሳበው ካልሆነ በቀር የእንጀራ ፍቅር የጥቅም ፍቅር ወደ ክርስቶስ አያመጣም በማለት ተናገራቸው፡፡ ጌታ እኔም በመጨረሻ ቀን አስነሣዋለሁ አለ ፡፡ የተአምራት እንጀራም የሰማይ መናም ለተመገቡአቸው ትንሣኤ አይሰጡም ፡፡ ክርስቶስ ራሱን በእኛ ውስጥ ሲያስቀምጥ ትንሣኤ እናገኛለን ፡፡ እርሱ እውነተኛው የሕይወት መብል ነውና ፡፡ ይህ ክፍል ብናገላብጠው ስለ ቅድመ ውሳኔ አይናገርም ፡፡
3-  “ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኩር ይሆን ዘንድ ፣ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው ፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው” /ሮሜ . 8፡29-30/ ፡፡ ይህ ክፍል አንዱን ለጽድቅ ፣ አንዱን ለኩነኔ ወሰነ የሚያሰኝ ምንም ነገር የለውም፡፡ እንደውም ሁሉም ክርስቶስን እንዲመስሉ አስቀድሞ መወሰኑን የሚናገር ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ውሳኔ ለሁሉ ጽድቅ ነው ፡፡ ኩነኔ ግን የሰው ውሳኔ ነው ፡፡ እስቲ ጥቅሱን እንመለከተው ፡፡ ወሰነ ፣ ጠራ ፣ አጸደቀ ፣ አከበረ በሚሉ ድንጋጌዎች የተዋቀረ ነው ፡፡ ወሰነ የሚለው ከዓለም በፊት ክርስቶስን እንመስል ዘንድ መወሰኑን ይገልጣል ፡፡ የወሰነውን ደግሞ በፍጥረት ጠራ ወይም በመፍጠር ጠራ ፡፡ መፈጠር ጥሪ ነውና ፡፡ የተፈጠረው ሰው በኃጢአት በወደቀ ጊዜ በክርስቶስ አጸደቀን ፡፡ ያጸደቀን ደግሞ ገና በስደት ዓለም አለንና በዕለተ ምጽአት ያከብረናል ፡፡
4-  “ይህ ብቻ አይደለም ፣ ነገር ግን ርብቃ ደግሞ ከአንዱ ከአባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ  ፣ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ ፣ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ ፣ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ ፣ ለእርስዋ ፡- ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለላት” /ሮሜ . 9፡10-12/፡፡ ይህን ቃል በመጥቀስ አንዱ ለጽድቅ አንዱ ለኩነኔ ተወስኗል የሚል አሳብ ይነሣል ፡፡ ክፍሉ ግን የሚናገረው ስለ መግዛትና መገዛት ወይም ስለ ኑሮ ደረጃ እንጂ ስለጽድቅና ኩነኔ አይደለም ፡፡ አዎ ዛሬም ቢሆን እኩል የኑሮ ደረጃ የለንም ፡፡ ይልቁንም በአዲስ ኪዳን በሰማያዊና በምድራዊ በረከት የተባረክን በመሆናችን የኑሮ ደረጃ አሳሳቢያችን አይደለም ።
5-  “ለሙሴ፡- የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና። እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ” /ሮሜ .9፡15-16/።እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል የተናገረው መቼ ነው?ስንል በዘጸ. 33፡19 ላይ ነው ፡፡ የእስራኤል ልጆች የጥጃ ምስል ሠርተው በሰገዱ ጊዜ የእግዚአብሔር ቁጣ ነደደ ፡፡ መዓቱ በተከለከለች ጊዜ እኔ ከእናንተ ጋር አልወጣም መልአኬን እሰዳለሁ ባለ ጊዜ ጽኑ ኀዘን አዘኑ ፡፡ እነርሱን የመልአክ ትዕግሥትም እንደማይችላቸው አውቀዋል ፡፡ እግዚአብሔርም ከቁጣው በበረደ ጊዜ ሙሴን ሲያነጋግረው ፡- “ይቅር የምለውን ይቅር እለዋለሁ ፣ የምምረውንም እምራለሁ” አለው ፡፡ ምን ማለቱ ነው?ስንል ይቅርታዬን የምሰጠው በራሴ ደግነት ተመሥርቼ እንጂ ሰው ስለሚገባው አይደለም ማለቱ ነው ፡፡ ይህን ቃል የምንረዳው የምምረውን እምረዋለሁ ከሚለው ላይ የምኮንነውን እኮንነዋለሁ ብለን ከራሳችን ጨምረን በማንበብ ነው ፡፡ ክፍሉ ስለ ምሕረት የሚናገር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረቱ ለእኛ ሩጫ የሚከፈል ዋጋ ሳይሆን አስቀድሞም በባሕርዩ መሐሪ ስለሆነ ነው ፡፡ እኛ ይቅርታን ከመፈለግ ውጭ አማራጭ የለንም፤ እግዚአብሔር ግን እኛን ይቅር ለማለት በመፍቀዱ ልናደንቀው ይገባናል ፡፡ 
6-  “መጽሐፍ ፈርዖንን፡- ኃይሌን በአንተ አሳይ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ይነገር ዘንድ ለዚህ አስነሣሁህ ይላልና። እንግዲህ የሚወደውን ይምረዋል፥ የሚወደውንም እልከኛ ያደርገዋል” /ሮሜ. 9፡17-18/፡፡ በግብጻውያን ላይ የወረዱት ዐሥሩ መቅሰፍቶች እግዚአብሔር ፈርዖንንና ሕዝቡን የቀጣበት ነው ፡፡ ፈርዖንን እግዚአብሔር መቼ ነው? እልከኛ ያደረገው ስንል ይህ ጥቅስ ዋቢ የተደረገበትን ዘጸ. 9፡16 ማየት ያስፈልጋል ፡፡ ይህ ክፍል የሚበዙት መቅሰፍቶች ከተፈጸሙ በኋላ የተነገረ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ እልከኛ ያደረገው እንዴት ነው?ፈርዖንን ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ፈጥነው የማይታዘዙትን ሰዎች ልብ አጽንቶ ለቅጣት ያመቻቻል ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሲመጣ ከኃይል ጋር ይመጣል ፡፡ ፈጥነን ከታዘዝን ኃይሉ ይረዳናል ፡፡ ከዘገየን ግን ኃይሉ ይመለስና ትእዛዙ ይቀራል ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ልባችንን አጽንቶ ለቅጣት ያመቻቸናል ፡፡ ፈርዖንን መጀመሪያ በድምፅ ቀጥሎ በዐሥር መቅሰፍቶች ሊመለስ ስላልቻለ እግዚአብሔር በመጨረሻ ልቡን አጽንቶ በኤርትራ ባሕር ጥሎታል ፡፡ ሰዎች የንስሐ ድምፅ ሲመጣላቸው በማንኛውም ጊዜ ማድረግ የሚችሉት ይመስላቸዋል፡፡ ሲያረጁ ወይም ብርቱ መከራ ሲገጥማቸው ወዲያው ማድረግ የሚችሉት ይመስላቸዋል ፡፡ ንስሐ የምንገባው ግን የንስሐ ጸጋ ሲለቀቅልን ነው ፡፡ የንስሐ ጸጋ ከንስሐ ድምፅ ጋር አብሮ ይመጣል ፡፡ ስለዚህ ፈጥኖ መታዘዝ ይገባል ፡፡ የንጉሥን ትእዛዝ መፈጸም ብቻ ሳይሆን ፈጥኖ መፈጸምም ይገባል ፡፡ ብዙ ሰዎች የንስሐ ጥሪ ሲቀርብላቸው ኖሮ ብዙ ዘመን አልፎ ከዚህ በኋላ እንደማይኖሩ ቢያውቁትም መመለስ አይፈልጉም ፡፡ በፈርዖንም የሆነው ይህ ነው ፡፡
7-  “ነገር ግን እግዚአብሔር ቍጣውን ሊያሳይ ኃይሉንም ሊገልጥ ወዶ፥ አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለ ጠግነት ይገልጥ ዘንድ፥ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ከቻለ፥ እንዴት ነው?” /ሮሜ .9፡22-23/፡፡ እግዚአብሔር ለምሕረት ሲያዘጋጅ ለጥፋት ግን የሚዘጋጁት ራሳቸው ጠፊዎቹ ናቸው፡፡ ጥቅሱን ልብ ብለን መመልከት ይገባል ፡፡ ይህን የሚመስል ቃል አለ ፡፡ በመጨረሻ ቀን ለጻድቃን፡- “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” ይላቸዋል ፡፡ ለሰው የተዘጋጀው መንግሥተ ሰማያት ነው ፡፡ ኃጥአንን ግን፡- እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ”ይላቸዋል ፡፡ የዘላለም እሳት የተዘጋጀው ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ነው /ማቴ. 25፡34 እና 41/፡፡
8-  “ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው” /ሮሜ . 1፡24/፡፡ አሳልፎ የሰጣቸው እነማን ናቸው?ስንል እግዚአብሔርን ለማወቅና ለማምለክ ያልፈቀዱትን ሰዎች ነው ፡፡ ይህ አሳልፎ መስጠት ገበሬ እንደ ተወዉ ማሳ ማለት ነው ፡፡ ገበሬ የተወው ማሳ የማይበቅልበት አረም እንደሌለ እግዚአብሔር እጁን ያነሣበት ሰውም የማይበቅልበት ብልግና የለም ፡፡ እንግዲህ ራሳችንን በጽድቅ ውስጥ ስናገኘው ክብሩን ለእግዚአብሔር እንስጥ ፤ ራሳችንን በኩነኔ ውስጥ ስናገኘው ኃላፊነቱን እኛው እንውሰድ፡፡
እግዚአብሔር አንዱን ለጽድቅ ሌላውን ለኩነኔ ፈጥሮታል የሚሉ ሰዎችን የሚረታው ዋነኛው ቃል እግዚአብሔር ዓለሙን አፈቀረ፤ በዓለሙ እንዲፈርድ ልጁን ወደ ዓለም አልላከም የሚለው ቃል ነው /ዮሐ. 3፡16-17/፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ጨካኝ መንግሥታትም ብንማልድ እግዚአብሔር ደስ እንደሚሰኝ በገለጠበት አንቀጽ ፡- ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው”ብሏል /1ጢሞ.2፡3-4/፡፡ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ የሚወድ እግዚአብሔርን አንዱን ለጽድቅ ሌላውን ለኩነኔ መድቧል ማለት አይገባም ፡፡ ዘጠና ዘጠኙን ያልበደሉ መላእክት ትቶ የበደለውን አንዱን አዳም ፍለጋ የወጣው ታዲያ ለምንድነው?
ዓለሙን አፈቀረ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ