የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የናዝሬቱ ኢየሱስ

“በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና። ተከተለኝ አለው” /ዮሐ. 1፡44/።
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1፡44-52 የሚናገረው ስለ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ስለ ፊልጶስና ስለ ናትናኤል መጠራት ነው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት የጥብርያዶስ አካባቢ የቤተ ሳይዳ ሰዎች ናቸው። አሁን ግን ጌታ ያገኛቸው ዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ነው። ይህ አካባቢ የዮሐንስን ትምህርት ለመስማት ካልሆነ በቀር የሚመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ጭው ያለ በረሃ ነበር። ዮሐንስ መጥምቅ የመረጠው ማንም የማይጋፋውን በረሃ ነው። ማንም የማይጋፋውን መሬት የመረጠ የወንበር ጠብ፣ ማንም የማይፈልገውን በረሃ የመረጠ የከተማ ፍጅት፣ ማንም የማይሻቸውን ድሆች የመረጠ የባለጠጎች ሽምያ የለበትም። የዛሬው የማይበርድ ጠብ ይኸው ነው። ወንበር፣ ከተማና ሀብታም። ይህ ሁሉ ስድድብ፣ ይህ ሁሉ ሽኩቻ በጎዳና ተዳዳሪዎች ሳይሆን እገሌን ሀብታም ወሰድክብኝ የሚል ነው። እንደ ዮሐንስ በረሃ ብንመርጥ እንደ እነ ፊልጶስ ፈልጎን የሚመጣ ይኖር ነበር። ጌታም የመረጠው የተናቁትን ከተሞች ነው። ለልደቱ ቤተ ልሔምን፣ ለእድገቱ ናዝሬትን ነው።
 ጌታችን ምንም አጭር ቃል እያሰማ እንዲከተሉት ቢሻም አስቀድሞ ግን ማንን እንደሚያገኝ ያውቅ ነበር። ሁሉንም ያገኛቸው እርሱን በተስፋ ሲያገለግሉትና ሲናፍቁት፣ ደግሞም መጻሕፍትን ሲያገላብጡ ነው። ፊልጶስና ናትናኤልም የተገኙት በዚህ አሳብ ተይዘው ሳለ ነው። እግዚአብሔር የመጠማት አምላክ ነው። የምናገኘው በተጠማነው መጠን ነው። እንደ ዋዛ በሚመስሉ ጊዜዎች የዘላለም አሳቡን በእኛ ይፈጽማል። እርሱ እግረ መንገድ እያለፈም የታቀደና ዘላቂ ተግባር ይፈጽማል። እርሱ ባለፈበት ዘላለማዊ አሻራ አለ። አሁንም ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ። በዚህ ቅጽበት ፊልጶስን አገኘው። እስካሁን የት ቆይቶ ነው? ስንል ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ ከጾመና ከጸለየ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ለመምረጥ ወደ ዮሐንስ ዘንድ መጣ። አዳዲስ አማኞችን ከማስከተል የሰነበቱ አማኞችን ማስከተል መልካም ነው። ስለዚህ ከዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስድስቱን ሊወስድ መጣ። ለክርስትናውም ሆነ ለመንፈሳዊነት አዲስ የሆኑ ሰዎችን እስኪያድጉ መጠበቅ መልካም ነው። እነዚህን ሰዎች ፈጥኖ ኃላፊነት መስጠት ጉዳት አለው። ላልተማረና ላልበሰለ ሰው ሥልጣን መስጠት ለእብድ ሰይፍ መስጠት ነው። ሐዋርያው ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪ አመራረጥ ሲናገር አንዱ መስፈርቱ፡- “በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን” ብሏል /1ጢሞ. 3፡6/። ይህ ሰው እስካሁን ትዕቢት አልተገኘበትም፣ አዲስ ሳለ መሾሙ ግን ትዕቢት ውስጥ ይከተዋል። ዲያብሎስ በትዕቢት ተፈርዶበታል። ትዕቢተኛም አዲስ ፍርድ አይፈረድበትም፣ ያንኑ የዲያብሎስ ፍርድ ተግባራዊ ይደረግበታል። አዲስ ክርስቲያንን መሪ ማድረግ ለራሱም ሕይወት ውድቀት ነው። ለቤተ ክርስቲያንም ፈተና ነው። በዓለም ያላቸውን እሴት ታሳቢ ተደርጎ በእግዚአብሔር ቤት የሾምናቸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን ሊያፈርሷት እየነቀነቋት ነው። የትኛው የድጓ መምህር፣ የትኛው የቅኔ መምህር፣ የትኛው የመጻሕፍት አዋቂ በጠበጠ? የሚሰማው ረብሻ ሁሉ ያለ ትምህርትና ልምድ ራሳቸውን በቀቡ ሰዎች ነው። ቤተ ክርስቲያን ሌላ የኑሮ ዘዴ ሆና በዓለም ቢሠሩ ውጤታማ የሚሆኑ ያለ ቦታቸው እያወኩባት ትገኛለች። “መስፈርት ከሌለው ከዚህ ዘመን ያድነን” ብለህ ጸልይ ያሉኝን አባት አልረሳም።
 ጌታ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ የሄደው ዕለቱን ነው። ታላላቅ ምስክርነት ከተቀበልን በኋላ መሰወር እንደሚገባን ሲያስተምረን ነው። ተጠምቆ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ። ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዕለቱን ወደ ዮሐንስ መጣ። ከዐርባ ቀን በፊት ራሱን ለዓለም ሊገልጥ፣ ከዐርባ ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ለመምረጥ መጣ። ደቀ መዛሙርትን ከመምረጥ በፊት በብርቱ መጸለይ መልካም ነው። አገልግሎት ቀጣይ የሚሆነው በአድናቂዎች ሳይሆን በደቀ መዛሙርት ነውና። ሕዝብ ከመሰብሰብ በፊት ደቀ መዛሙርት ማፍራት ሥራውን ያቀላል። ሕዝብ ተምሮ የሚሄድ ነው። ደቀ መዝሙር ግን ተክቶ የሚያገለግል ነው። “ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ” የሚባል ነው። ሕዝብ ጥሩ አባት ነበሩ እያለ የሚያስታውስ ነው፣ ደቀ መዝሙር ግን ጥሩ አባት የሚሆን ነው።
 ጌታ ፊልጶስን አግኝቶ ተከተለኝ አለው። ተከተለኝ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የደቀ መዝሙር መጥሪያ ደወል ነው። ብዙዎች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ የወጡበት፣ ከአባወራነት የአገር አባት የሆኑበት፤ ከትጉ ሠራተኝነት ነቢይ የሆኑበት ምሥጢር ነው። ተከተለኝ የተባለ ሰው የት ነው የምሄደው? አይልም። የጠራውን አምኖ የሚዘምት ነው። የጠራው አካል ምንም እንደሌለው ያያል። ነገር ግን ድምፁ የበለጸገ መሆኑን ይረዳል። ዛሬ ሌጣ ቢሆንም ነገ እልፎችን እንደሚያስከትት ይረዳል። መንገዱን የሚያውቀው መቅደም አለበት። ሥልጣን ያለው ተከተለኝ ማለት አለበት። ወዴት ነው የምሄደው የሚል የመረጃ ሰው ደቀ መዝሙር መሆን አይችልም። ልጆች ወላጆቻቸውን የሚከተሉት በእምነት ነው። የመንገድ ካርታ አይጠይቁም። እንዲህ አምነው የተጎዱ ልጆች ብዙ አላየንም። የእግዚአብሔር ሰዎችም ማን እንደ ጠራቸው ብቻ ያውቃሉ እንጂ የት እንደሚሄዱ አያውቁም። ቀጥሎ ምን እንደሆነ ማወቅ አያስፈልግም። የሚያስፈልገን የጠራንን ማወቅ ብቻ ነው። የጠራን ጌታ ነገም በእጁ ናት። ዛሬ በአንዳንድ መኪና ጀርባ ላይ “ተከተለኝ” የሚል ጽሑፍ እናነባለን። ክፉ አይደለም። እነርሱና አምላክ ይተዋወቃሉ። በሕይወት ግን ቅድምልኝ እንጂ ተከተለኝ ማለቱ አያዋጣም። እኛ በቀደምንበት ትግል፣ ትግል፣ ድል የሌለው ትግል ነው። እርሱ ሲቀድም ግን ጦርነቱ ባይቀርም ይቀንሳል። እርሱ ሲቀድም ጦርነቱን ወስዶ ድሉን ያስቀርልናል። እርሱን መከተል ይገባናል። ፈቃዳችንን ለፈቃዱ አሳልፈን መስጠት በእውነት ይገባናል። ከብልጠት ኑሮ ወጥተን በእምነት ጌታን መከተል ያስፈልገናል። ክርስትና ጮሌነት ሳይሆን ለጌታ ሞኝ መሆን ነው። ድሮ ለዓለም ሞኝ ሆነን የተባልነውን እንዳደረግን አሁን ደግሞ ለአዲሱ ገዥ ሞኝ ሆነን ለእርሱ መገዛት ያስፈልገናል።
 ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬትና ከጥብርያዶስ አካባቢ ጠራ።  በቤተ ልሔም ሲወለድም እረኞችን ጋበዘ እንጂ ሊቃነ ካህናትን አልጋበዘም። ለምን እርሱ የሰጠውን ሹመት መናቁ ነው? አይደለም። ሹመታቸውን ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለግላቸው ዝና ስላዋሉት፣ አገልጋይነትን ትተው መሳፍንትነትን ስለመረጡ፣ ከምድራውያን ገዥዎች ጋር ሆነው ድሃውን ስለጨቆኑ፣ ማንበብና ማመስጠር እንጂ በታሪካቸው የሰማዩን ብርሃን ለማየት ናፍቆት ስላላሳዩ ነው። ጥብርያዶስ ገጠራማ መንደር ነው። ያኔም አሁንም ያው ነው። ናዝሬትም ብዙ የማትማርክ ይልቁንም በዚያ ዘመን የዓመፀኞችና የነፍሰ ገዳዮች ከተማ ነበረች። ዛሬ ግን ናዝሬትን የማያውቃት የለም። በናዝሬቱ ኢየሱስ፣ ናዝሬት በሁሉ የታወቀች ናት። እርሱ በቤተ ልሔም ተወልዶ ሳለ የቤተ ልሔሙ ኢየሱስ መባልን አልፈለገም። እንኳን ለተናቀ ሰው ለተናቀም ከተማ ክብር ነው። ቤተ ልሔምን ለልደቱ፣ ናዝሬትን ለዕድገቱ፣ ኢየሩሳሌም ለሞቱ መረጠ።
እኛንም የወደደ ቡሩክ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ