“ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና ፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ ? ሕዝቤስ ማን ነው ?” 1ዜና. 29 ፡ 14 ።
ጌታ ሆይ ! ሁሉ በአንተ ፣ ሁሉ ከአንተ ፣ ሁሉ ለአንተ ነው ። ያላንተ ፈቃድ የሆነ ፣ ያላንተ ፈጣሪነት የተገኘ ፣ ካንተ በቀርም ክብሩን ሊወስድ የሚከጅል ማንም የለም ። ሁሉ ባንተ ነው ፣ የመሠረቶች መሠረት ነህ ፤ በውጥኖች ሁሉ ያንተ ውጥን ከሌለበት የአሳብ ቤት ሁኖ ይቀራል ። ባንተ አሳብና ባንተ ድርጊት መካከል ልዩነት የለም ። ያሰብከውን ታደርጋለህ ፣ ያደረከውንም አስበሃል ። ሁሉ ከአንተ ነው ፣ ነገርን ውብ አድርገህ ፣ አስማምተህ ፣ ለሥርዓት አስገዝተህ የምትሠራው አንተ ብቻ ነህ ። ሁሉ ላንተ ነው ፣ ሁሉን አድርገህልን ተመስገን ብቻ በሉኝ ያልከው አንተ ነህ ። ምስጋናችን የውለታህ ክፍያ ሳይሆን መታሰቢያ ነው ።
ዘመናዊው ልባችን ሁሉ በእኔ ፣ ሁሉ ከእኔ ፣ ሁሉ ለእኔ እያለ ሸፍቶብናል ። ሁሉ በእኔ ብለን በጭንቀት አምጠናል ፣ ሁሉ ከእኔ ብለን የካብን መስሎን ንደናል ፣ ሁሉ ለእኔ ብለንም ራሳችንን ማስመለክ ዳድቶናል ። ሁሉ በእኔ ብለን አሳብ የማንቀበል ሆነናል ። ሁሉ ከእኔ ብለን እኔ ያልሠራሁት አይጣፍጥም ብለናል ። ሁሉ ለእኔ ብለን በቁማችን ሐውልታችንን ሠርተን አስመርቀናል ። ሁሉ በእኔ ብለን ፈቃድህን ጥሰን ሄደናል ። ሁሉ ከእኔ ብለን የፈጠርከውን ሳይሆን የፈጠርነውን ከጅለናል ። ሁሉ ለእኔ ብለን ለራሳችን መልክዕና ውዳሴ ደርሰናል ። አቤቱ ልዑል ሆይ ሁሉ ባንተ ነው ። ነፍሴን ሳልረዳት ያወቅኸኝ አንተ ነህ ። አቤቱ አዶናይ ሁሉ ከአንተ ነው ። እጄ የሠራልኝ ፣ ሰዎች የቆረሱልኝ የመሰለኝ ነገር ያንተ ጸጋ ነው ። ኤልሻዳይ ሆይ ሁሉ ለአንተ ነው ፣ ለምስጋና መስነፌ ከንቱነቴ ነው ።
እረኛ ብሆን ንጉሥ ፣ በዱር ብኖር በቤተ መንግሥት እኔ እንጂ አንተ አትለወጥም ። እጄ ዘገነልኝ ፣ ክንዴ መከተልኝ ብዬ ራሴን አላታልልም ። ከብሬ የምበቀል ፣ አግኝቼ ሰውን የማዋርድ ብላሽ ነኝና አቤቱ ይቅር በለኝ ። ሁሉ ካንተ ነው ። ቤቴን ብሠራ ፣ ቤትህን ብሠራ የሠራኸው አንተ ነህ ። ለመወለድ አቅም ያልነበረኝ ለመኖር አቅም የለኝም ። ባንተ አሳብ ተፈጥሬ በራሴ አሳብ የምሳከር ነኝ ። ሁሉ ካንተ ነውና ዳኛ በደለኝ ፣ ባለጠጋ ነፈገኝ ፣ ንጉሥ ፈረደብኝ ብዬ አላዝንም ። ሁሉ ከአንተ ነው ። ዘመድ አላለቀሰልኝም ፣ ጓደኛ አልሳቀልኝም ብዬ በሸለቆና በተራራው አላጉረመርምም ። አጥቶም አግኝቶም መከፋት ከእኔ ይራቅ ። አጥቼ ዝም አሉኝ ብዬ ሰዎችን መኰነን ፣ አግኝቼ አልሳቁም ብዬ በሰው መደነቅ ከእኔ ይራቅ ። ሁሉ ካንተ ነውና ሁሉም ምስጋና ላንተ ይሁን ። የኀዘኔ ደራሽ አንተ ነህ ፣ የእልልታዬ አጋርም አንተ ነህ ። ሲከፋኝም ስደሰትም ያንተው ዕዳ ነኝ ።
በምድር ላይ ላንተ እንደ መስጠት የሚያስደስት ምንም ነገር የለም ። አባት ለልጁ ሰጥቶ ስጠኝ ይለዋል ። ሰጥተኸኝ ስጥ ያልከኝ አንተ አባቴ ነህ ። ቤትህን ለመሥራት ልበ አምላክ ዳዊት እንኳ ፈቃድ አላገኘም ። ያንተን ቤት መሥራት ፣ ሰብኮ ማሳመን ፣ አምልኮ ማስመለክ ዕድል ነው ። እኔ ባልሠራውም ለሚሠራው ድካሙን እንዳቀልለት እርዳኝ ። እኔ ካልሠራሁት ድርግም ይበል ማለትን ከእኔ አርቅ ። በማልኖርበት ዘመንም ያንተ ሥራ ይሠራ ። እነዚያ ባዶ እጆቼ ፣ ድቃቂ ሳንቲም የነጠፉ መዳፎቼ ዛሬ በረከት ካገኙ ያንተን ላንተ እሰጣለሁ ። ሁሉ ካንተ ነውና ለመስጠት ልቡን ፣ ለመቸር አቅሙን ለሰጠኸኝ ምስጋና እንዳቀርብ እመኛለሁ ። ሳትቆጥር ሰጥተኸኝ ሳለ ቆጥሬ እንዳልሰጥህ እርዳኝ ። ሊሰጥህ ከጅሎ እጁ ላጠረበት በረከት አፍስስለት ። ሰጥተኸው ሳለ ሰይጣን እጁን ለቆለፈበት አርነት አውጅለት ።
በምስጋና የተፈራህ ፣ ተወደህ የምትከበር ፣ ተፈቅረህ የምትመለክ አንተ እግዚአብሔር ነህና ምስጋና ለታላቅነትህ ይሁን !!!!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም.