መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ለምትቀር ዓለም

የትምህርቱ ርዕስ | ለምትቀር ዓለም

በኪራይ ዓለም እየኖርህ ተከራይ ብለህ ሰውን የምትጠራ ፣ የሚከፍልህን የምታሰቃይ አንተ ሆይ ለገዛ ልጅህ መከራ እንደምታስቀምጥ ለምን ዘነጋህ? የጊዜ እንጂ የሰው ብርቱ የለውም። ትላንት የተወረሰባቸውን ረስተህ ዛሬ በቤትህ ሰው ታሰቃያለህ። ብሩን ወደህ ተከራዩን ትንቃለህ። በየዘመድ ቤት የተንከራተትህ ፣ የአንድ ቀን ማደሪያ የቸገረህ ነበርህ። ዛሬ እልፍኝ ከአዳራሽ የሰጠህ ሊባርክህ ብቻ አይደለም ሊፈትንህም ነው። የትላንት አከራይ ዛሬ ተከራይ ትሆናለህ። ግፍ ከተማን ያፈርሳል፣ ጽድቅ አገር ይሠራል። እግዚአብሔር የሰጠህ አደራ መሆኑን ዘንግተህ ግፍ ትሠራበታለህ። በግፍ ገንዘብ ልጆችህ በሱስ ያብዳሉ ። አንተም ጤና አላገኘህም። በማጉረምረም መከራ አይርቅም፣ በንስሐና በመለወጥ እንጂ።

የድሃ ልጅ ብለህ ስትሳደብ እንዴት አልፈራህም? ለነገሩ ድሀ ድሀ ብሎ መሳደብ ልማዱ ነው። በዓለም ላይ ጨካኝ የድሀ ልጅና ድህነትን ያየው ነው። ደግሞም ድሀ ወርቅ አይጠግብም። የገንዘብ ድህነት በአጋጣሚ ይወገዳል። የአእምሮ ድህነት በሎቶሪ አይወገድም፣ ብዙ መጣር ይፈልጋል። ማነው ባለጠጋ? የሰማይ የምድር ጌታ እንኳ በበረት ተወልዶ ዕርቃኑን ተሰቅሏል። ያንተ ካባ የአካል እንጂ የሕሊና መሸፈኛ መቼ  ይሆናል? ልጄ ጅማሬህና ፍጻሜህ ፍጹም ድህነት ነው። ዕራቁትህን መጥተሃል  ፣ዕራቁትህን ትሄዳለህ። ይዘህ አልመጣህምና ምንም ይዘህ አትሄድም። የዚህ ዓለም ሀብት በሰማያዊ አገር በአሻንጉሊት የሚደሰት ሽማግሌን የሚያስመስል ነው ። አሻንጉሊት ሕይወትም እውነትም የሌላት ለልጅ የምትመጥን ላዋቂ የማትመጥን  ናት ።

ያንን ችግር ተሻገርከው ማለት ችግር አለቀ  ማለት አይደለም። እግዚአብሔር የመከራ ድሀ አይደለምና አትታበይ። ተረኛ በዪ እንጂ ቋሚ የለም። እግዚአብሔር ጽዋውን እያዘዋወረ ስንቱን ይታዘበዋል። በዘመናት ሁሉ ረሀብን ታግሠውታል፣ ጥጋብን የታገሠ ጥቂት ነው።

የት እንደ ወደቀ ትዝ ያላለህን ሰው ሲቸግርህ አታስታውሰው። የወጣህበትን መሰላል በእግርህ አትገፍትረው ፣ አታቆሽሸው ። መውረጃው እንዳይቸግርህ ፣ ያቆሸሽከውንም መልስህ በእጅህ እንዳትጨብጥ አስተውል። ከመውጣትህ በፊት ስለ መውረድህ አስብ። ወጥቶ የቀረ ፣ ወርዶ የሞተ የለም። ስትወጣ እጁን የሰጠህ ሰው ስትወርድ በእግሩ ይረግጥሃል።

አንተ ተላላ ለነ ፈርዖን፣ ለእነ ናቡከደነፆር፣ ለእነ እስክንድር ለነ ቄሣር ለእነ ናፖልዮን ለነ ኃይለ ሥላሴ ያልሆነች ዓለም ለእኔ ትሆናለች ብለህ ካሰብህ ሞኝ ነህ።

ላይሞላ ዓለም የሰው ትዳር መቀማት፣ ነፃነትን ለባዕድ መሸጥ፣ ጠንቋይ ቤት ለፍጡር መስገድ፣ ፖለቲካ ቤት በባዶ ማጨብጨብ ፣ በግፍ በሚሞቱ ላይ መቀለድ፣ ሰውን  አፍኖ ማስከፈል …ይህ ሁሉ የረከስንበት ግብር ነው። ቋሚዎቹን እኛን የሞቱት እየረበሹን ነው። እነዚያ ወጣቶች በዝምታ እየከሰሱን ነው። እንጀራው ተገኝቶ የማይበላው እንጀራ አጥተው የሄዱት ሊቃውንት ረግመውን ነው። መብሉ ቀርቦ ከመብላት መባላት የሆነብን የእነዚያ ምስኪኖች ረሀብ ከሳሽ ስለ ሆነብን ነው ።

አንተ ሆይ !
ሰው በኳስ፣ ሰው በአዝማሪ ይጫወታል። በግፍ የምትጫወተው እስከ መቼ ይሆን? ሞትን እየፈራህ ሞትን በሰው ለምን ትፈርዳለህ? ላንተ ሲነጋ ለሌሎች  ጨልሞ ነው። ላንተ ሲጨልም ለእነርሱ ይነጋል። ዛሬ የምታዝዘው ምስኪን ነገ አለቃህ ሆኖ ይመጣል። ሰው ያለ ማቋረጥ የሚጓዝ ነውና አንተ ሲደክምህ እርሱ ይደርስብሃል ።

ዓለም ቀሪ ናት። ዓለም ከኋላ ናት። ዓለም ቀጥራ የምትቀር ናት። ዓለም ሲከተሏት የምትሸሽ ጥላ ናት። ሁሉንም ጥለህ ትሄዳለህ። ያንተ ወርቅ በሰማይ እንደ ዝገት ነው። ዘመድ አዝማድም የጠዋት ጤዛ ነው። የምድር ፍቅር ከእንካ ጋር ነው። ሀብትና ንብረትም ይሸሽሃል ። ስትቆም ያጨበጨቡልህ ስትወድቅ ይረግጡሃል። በሆሳዕናና በ ስቀለው መሐል ያለው አምስት ቀን ነው። ሆሳዕና ብለው ሲያከብሩህ ልብህ አይኩራ ቀጥሎ ይሰቀል ብለው ይጮኻሉ።

ምን ቆንጆ ቢሆኑ ቢቀጥኑ እንዳክርማ፣
መጠቅለል አይቀርም በነጠላ ሸማ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 4 ቀን 2ዐ17 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም