የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መኖሬን ወደድሁት

“ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ ።” ኤፌ. 2፡11-12።

ክርስትና የግልግል መድረክ ነው ። የአገልጋይ ሥራም ሰውን ከገዛ አስተሳሰቡ ፣ ሰውን ከሰው ሲገላግሉ መዋል ነው ። “ገላጋይ ይሞታል” እንዲሉ ሙሴ ከእስራኤል ምኞት ጋር ሲታገል የተስፋይቱን ምድር ሳይወርስ ቀርቷል ። “ገላጋይ አጥቼ ግልገሌን በላኋት” እንዲሉ አገልጋይ አጥተውም የገዛ ነፍሳቸውን የበሉ አሉ ። መድከሙ ሳይታወቅለት ዴማስ ሲጠፋ ብቻ ታውቋል ። እንደ ባለጌ ተገላጋይ ገላጋዩን የሚመታ መሆን ፣ ያገለገሉንን መናቅና መሳደብ ተገቢ አይደለም ። በዛሬው ሕይወታችን ላይ የሰዎች አስተዋጽኦ አልነበረውም ብለን ካመንን በልቶ ካጅ መሆናችን ነው ። የእናቶችን ቀን የምናከብረው የእናቶችን ውለታ ለማስታወስ ነው ። ያኖረን እግዚአብሔር ነው ። ዋጋ የከፈሉልን የእግዚአብሔር ስጦታዎቻችን ደግሞ አሉ ። የአገልጋዮች ቀን መቼ ነው የሚከበረው ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። የኤፌሶን ምእመናን ከኦሪት ወደ ክርስትና የመጡ ሳይሆን ከጣዖት ወደ ክርስቶስ የተመለሱ ነበሩ ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ባለ ርስት ሁነዋል ። በዚህም ለምስጋና እንዲበቁ ሲፈልግ ለትዕቢት እንዳይዳረጉ ይሰጋል ። ከልባቸው ጋር የትዕቢት ጉባዔ እንዳያደርጉ ፣ ከሰዎችም ጋር የእኩል ነን ትግል እንዳይገጥሙ ፣ ጸጋውን አቃለው ፍቅርን እንዳይጥሉ አደራ ማለት ይጀምራል ።

የቀደመ ኑሮአቸውን አስረግጦ ይናገራል ። ሙት ነበራችሁ ፣ አሕዛብ ነበራችሁ ፣ የተናቃችሁ ቆላፋን የተባላችሁ ነበራችሁ ፣ ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ነበራችሁ … እያለ ሳያወላውል ይናገራቸዋል ። ይህ ሁሉ ያለፈና የተለወጠ ታሪክ ከሆነ አሁን መድገሙ ለምን ያስፈልጋል ? ቢሉ ሰው ስርየት ያገኘበት ታሪኩ ሌላውን የሚያስተምርበት ሕያው ደብተሩ ነው ። ክርስቶስ ለሕይወት ሁለት መልክ ይሰጣልና የቀደመው ገጹ ጥቁር ፣ የአሁን መልኩ ነጭ መሆኑ አስደናቂ ነው ። ደግሞም ሰው ሲወድቅ የለመነውን ጸጋ ሲቆምና ሲጸና ሊቃልለው ፣ በቅንነቴና በችሎታዬ ለዚህ በቃሁ ሊልበት ይችላል ። ባይናገርም ማሰብ ይጀምራል ። ሐዋርያው ምንጩን ለመቀደስ ፣ የልብ ትዕቢትን ለመግረዝ ሥራ ይጀምራል ። በነበር የተለወጠላቸው ታሪክ ታላቅ ምስጋና የሚያቀርቡበት ርእስ ነው ።

• በሥጋ አሕዛብ ነበሩ ፣
• ያልተገረዙ /ቆላፋን የተባሉ ነበሩ ፣
• ከእስራኤል መንግሥት የራቁ ነበሩ ፣
• ለተስፋው ቃል ኪዳን እንግዶች ነበሩ ፣
• ከእግዚአብሔር ተለይተው ነበር ፣
• ያለ ክርስቶስ ነበሩ ።

እስራኤላውያን የአንዱን አምላክ አምልኮ ከአባቶቻቸው እንዳገኙ አሕዛብም የጣዖታትን አምልኮ ከአባቶቻቸው ወርሰዋልና በሥጋ አሕዛብ ነበሩ ። እስራኤልንና አሕዛብን የለየው ድንበር አንዱን አምላክ ማምለክና አለማምለክ ነው ። ሰው ሁኖ በመፈጠር ሁሉም እኩል ቢሆንም ሰው ሁኖ በመኖር ግን አንዱ ካንዱ ይለያል ። ሰው የትኛውም እውቀትና ደረጃ ላይ ቢደርስ ከቤተሰቦቹ ተጽእኖ ውጭ ላይሆን ይችላል ። የቤተሰብን ተጽእኖ ሊያሸንፍ የሚችል ትልቅ አመክንዮና ለዚያ ምክንያትም መገዛት ነው ። ሰው ከቤተሰቡ ቀጥሎ የአካባቢ ከዚያም የጓደኛና የመምህራን ተጽእኖ ይታይበታል ። ብዙ ተጽእኖዎች ያሉበትን ሕይወት ክርስቶስ ቢማርከው የተሻለ ነው ። ምናልባት ርኵሳን መናፍስትን ከሚያመልኩ ቤተሰቦች ወጥተን ይሆናል ። እግዚአብሔር ከነደደው እሳት ፣ ከሚንተከተከው ፍላት ማዳን እንደሚችል የገዛ ሕይወታችን ምስክር ሊሆን ይችላል ። ግዝረት የእግዚአብሔር ሕዝብ የመሆን ምልክት ነው ። ግዝረት በውስጡ መሥዋዕትነት ፣ ቃል ኪዳን ያለው ምልክት ነው ። ውጫዊው ግዝረት የውስጡ እምነት መግለጫ ነው ። አሕዛብ የውስጡ እምነት ፣ የውጭው ትእምርት/ምልክት አልነበራቸውም ። ውጫዊ ምልክት ይዞ መጓዝ ለሰማዕትነትም የሚያበቃ ነው ። ውጫዊ ምልክት እንደ ቀላል የሚቆጠር አይደለም ። ሰው የልቡን በልቡ ይዞ በአፉ ለመካድ ሊሞክር ይችላል ። የውጭው ምልክት ግን አሳልፎ ይሰጠዋል ። ውጫዊ ምልክት ባመኑበት ያለ ማፈር ጽናትም ነው ። አሕዛብ ግን ቆላፋን ያልተገረዙ የተባሉ ናቸው ። ግዝረት በዚህ ዘመን ከጤና ፣ ከንጽሕና እንዲሁም ከውበት ጋር እንጂ ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የለውም ። የእኛ ትልቁ ምልክት ጥምቀት ነው ። የእስራኤል መንግሥት መንፈሳዊ ነው ። በምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ሰማያዊቷን ኢየሩሳሌም መጠበቅ ነው ። አሕዛብ ከዚህ መንግሥትም ርቀው ነበር ። ምድር ምድር ብቻ የሚያዩ ከሰማይ የቀረላቸው ምንም ነገር አልነበረም ። በአበው ተስፋ ፣ በነቢያት ትንቢት ፣ በካህናት ሱባዔ የሚጠበቀው ምጽአተ ክርስቶስን የማያውቁ ነበሩ ። እስራኤል ጊዜው ደረሰ ወይ ? እያሉ ሲዋትቱ አሕዛብ ግን ኖሮ ለመሞት ብቻ ይኖሩ ነበር ። እግዚአብሔር በአምልኮቱ ቀናተኛ ነውና አሕዛብ በሃይማኖትና በምግባር ወድቀው ከእርሱ ተለይተው ነበር ። ያለ ክርስቶስም እየተጓዙ የሞታቸውን ድንጋይ ተሸክመው ይንቀሳቀሱ ነበር ። ይህ ሁሉ ውድቀትና ድቀት በነበር የሚነገር ነውና ደስ ይላል ። የትላንቱ ትላንት አለፈላቸው ። ዛሬ ግን እስራኤል ወጥተው እነርሱ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ገቡ ። መኖራችንን ከወደድነው ክርስቶስን ስላገኘንበት ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ