መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » መጽሐፍ ቅዱስ » መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል አንድ

የትምህርቱ ርዕስ | መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል አንድ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
 መጽሐፍ ቅዱስ
                                  ፣ ረቡዕ ሰኔ ፲፰  ፳፻፮ ዓ/ም

አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ በእርሳቸው ጀርባ ተጭኖ ወደ ጎጃም እንደ ገባ ብዙ ጊዜ ይናገሩ ነበር፡፡ እኚህ ሰው የተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሶችን ይዘው ወደ ትውልድ ቀያቸው ወደ ጎጃም ይሄዳሉ፡፡ በዚህም ለቄሱ አንድ አንድ፣ ለምእመን አንድ ለሁለት ሰጥተው ይመለሳሉ፡፡ ጎጃም ምን እንዳለ ለመስማት ከጎጃም የመጡ ማር ነጋዴዎችን ለማነጋገር ወደ ጎጃም በረንዳ ሲሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠባት የገጠር መንደር አጠገብ የሚኖር ሰው አገኙና “በጎጃም ምን ይወራል?” አሉት፡፡ እርሱም “ጎጃምማ የሚያድን መጽሐፍ አግኝቷል፣ የሚገርመው መጽሐፉ ያለፈው በደጃችን መሆኑ ነው፤ ይህስ ቢቀሙትም የሚያጸድቅ ነበር” በማለት ቊጭቱን ሲነግራቸው ልባቸው በደስታ ፈነጠዘች፡፡ ዳግመኛ ወደ ጎጃም ሄደው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያድሉ ሁለት ምስክርነት ሰሙ፡፡ 
አንድ ለሁለት የተሰጣቸው ጎረቤቶች አንዱ መጽሐፉን ይዞ አልለቅ ይለዋል፡፡ እንደ መጽሐፈ ቅዳሴ ዕለቱን የሚዘልቀው መስሎት፡፡ ጎረቤቱም፡- “አልጨረስክም ወይ?” ሲለው ቆይ ትንሽ ታገሠኝ ይለዋል፡፡ ቆይቶ ሲመጣም ሊለቅለት አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ለአጥቢያ ዳኛው ይከሰዋል፡፡ “አንድ መጽሐፍ ለሁለት ቢሰጠን ለብቻው ይዞ አልለቅም አለኝ” አለ፡፡ ዳኛውም ገጾቹ ይቆጠሩና እኩል ገንጥላችሁ ተካፈሉ ብለው ፈረዱ፡፡ 

ሌላው ምስክርነት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ያልደረሰው አንድ ምእመን ከቄሱ ቤት ይገባና እስከ ዛሬ የሚያድነውን መጽሐፍ ደብቃችሁብን እያለ በዓይኑ መጽሐፍ ቅዱሱን ይፈልጋል፡፡ እርሳቸውም እንደ ጌጥ ራስጌአቸው አስቀምጠውት ነበር፡፡ ያም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሲያይ ብድግ አድርጎ ይሮጣል፡፡ ቄሱም “አትመልስም ወይ” እያሉ በጩኸት ቢከተሉትም ሊቆም አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ እንደማይደርሱበት አውቀው ቆም ብለው “ሰማህ አንተ” ሲሉት “አቤት” ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም “የያዝከው መጽሐፈ እውስጡ እኮ አትስረቅ ይላል” አሉት” እርሱ ግን መልሶ “ራሱን አይደለም” ብሎ ሮጠ ይባላል፡፡ 


መጽሐፍ ቅዱስ የእያንዳንዱ ነፍስ ጥማት ነው፡፡ ይልቁንም ቃሉን መመገብ ለጀመሩት ሊያቋርጡት የማይቻል መንፈሳዊ ማዕድ ነው፡፡ “ረሀብ የጤንነት ስሜት ነው” እንደሚባል ቃሉን መፈለግ የመንፈሳዊ ጤንነት መገለጫ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋችን ከመተርጎሙ በፊት በዕብራይስጥና በግሪክ ቋንቋዎች የተጻፈ ነበር፡፡ የእያንዳንዱ ምእመን ንብረት ከመሆኑም በፊት የምኩራብና የቤተ ክርስቲያን ንብረት ነበር፡፡ ማንበብ መጻፍም የሊቅነት መገለጫ የነበረበት ዘመን አልፎ ማንበብና መጻፍ ዕለታዊ መግባቢያ ቋንቋ ሆኗል፡፡ ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ በቋንቋችን ተተርጉሞ፣ የእያንዳንዳችን ግላዊ ንብረት ሆኖ፣ ደግሞም  ማንበብ የምንችል ሆነን መጽሐፍ ቅዱስን አለማንበብ ራስን መበደል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የግላቸው ንብረት ለማድረግና በሚያድሰው ኃይሉ ለመጽናናት ብዙዎች ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ብርቱ ዕንባ አፍስሰዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራትን የመሠረተም ይህ ለቃሉ መገኘት የፈሰሰው ዕንባና የተደረገው ብርቱ ጥረት ነው፡፡ 
መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያን ዓለም ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሕዝቦች አንድነት መገለጫ፣ የነጻነት ሰንደቅ ዓላማ፣ የሕግጋት መሠረት፣ የሥነ ምግባር ምንጭ ነው፡፡ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በመላው ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖችን የሚያገናኝ መንፈሳዊ ድልድይ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ነጻ ለወጡ ሕዝቦች የሰጠው መጽሐፍ ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ከግብጽ ባርነት ነጻ ለወጡ እስራኤላውያን ብሉይ ኪዳንን፣ ከነፍስ ባርነት ነጻ ለወጡ ክርስቲያኖች አዲስ ኪዳንን ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የነጻነት ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ በዓለም ላይ ለሚገኙ ሕግጋት መሠረት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መልካም ሆኖም ብዙዎችን ለመልካምነት የወለደ ታላቁ የሞራል አናጢ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ 

ይህንን የነፍሶች ሁሉ ጥማት መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግእዝ ቀጥሎም ወደ አማርኛ በመተርጎም ለኢትዮጵያውያን ባለ ውለታ የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያናችንም መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋቸው ተርጉመው የራሳቸው ካደረጉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናትም አንዷ ሆናለች፡፡ ዛሬ በምድሪቱ ላይ ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱስን ጠብቃ ያቆየች ባለ ውለታ ቤተ ክርስቲያንም ነች፡፡
        በ4ተኛው ክፍለ ዘመን በቀዳማዊ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንዲሁም በ5ኛው ክፍለ ዘመን በተሰዓቱ ቅዱሳን መጽሐፍ ቅዱስ ከግሪክ ወደ ግእዝ ተተረጎመ፡፡ በ14ኛ ክፍለ ዘመንም በዳግማዊ ሰላማ ብርሃነ አዜብ ከዐረብኛ ወደ ግእዝ ለሁለተኛ ጊዜ ተተረጎመ፡፡ የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛ በሆነም ጊዜ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በጎንደር የአንድምታ ትርጓሜዎች ተጀመሩ፡፡ በዋናነት ግን የነጠላ ትርጓሜ ሥራ የተሠራው ትውልዳቸው ጎጃም በሆነው በአባ አብርሃም ነው፡፡ በአባ አብርሃም የተሠራው ብሉይና አዲስ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በ1832 ዓ.ም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ታተመ፡፡ ዳግመኛም በ191ዐ ዓ.ም  በአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኰንን በተቋቋመ የሊቃውንት ጉባዔ ከግእዝ ወደ አማርኛ 15 ዓመት ፈጅቶ ተተረጎመ፡፡ ይህም ትርጉም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስደት ሳሉ በ193ዐ ዓ.ም በለንደን ታተመ፡፡ ከጣልያን ወረራ በኋላም ከመሠረታውያን ቋንቋዎች ከዕብራይስጥና ግሪክ ጋር ተመሳክሮ እንደገና ተሠራ፡፡ ይህም በ1944  ሥራው ተጠናቆ ቀረበ፡፡ መላው መጽሐፍ ቅዱስም በ1953 ዓ.ም በብርሃንና ሠላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማተሚያ ቤት ታተመ፡፡ ይህን ትርጉም በአገራችን የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ስለ ወደዱት በ1954 ዓ.ም 66ቱን መጻሕፍት ነጥለው በማውጣት አትመዋል፡፡ ዛሬ በስፋት የምንጠቀምበት የ1954ቱ እትም መጽሐፍ ቅዱስም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥረት የተሠራ ተወዳጅ ትርጉም ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን የመጀመሪያውን ቋንቋ ዕብራይስጥን፤ አዲስ ኪዳንም የመጀመሪያውን ቋንቋ ግሪክን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ 
ይህን ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ መጽሐፍ ቅዱስ መታተሙ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ልትኖርና የአማኞችዋን መንፈሳዊ ደኅንነትን ጠብቃ መቆየት ስለማትችል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እንዳይበረዝና እንዳይከለስ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ልዩ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር መጽሐፉን እየጠበቀ ለእኛ አድርሶልናል፡፡ ይህ አጭር ጽሑፍም ለመጽሐፍ ቅዱስ እንደ መግቢያ የሚሆን እንጂ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊባል የሚገባውን ሁሉ አሟልቶ የያዘ አይደለም፡፡ የትርጓሜ መመሪያ የሚሰጥም አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብ የሚቀሰቅስ ደወል ብቻ ነው፡፡ 
እኛ ኢትዮጵያውያን የዘወትር ምግባችን እንጀራ ነው፡፡ እንጀራ ካልበላን የበላን እስከማይመስለን ቅር ይለናል፡፡ እንጀራም ዘወትር ብንመገበውም ስለ እንጀራ ግን ተመራምረን ጠይቀን አናውቅ ይሆናል፡፡ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገራቸው ብዙ ቃሎች እያወጣን እራሱን መጽሐፍ ቅዱስን ግን መርምረን አናውቅ ይሆናል፡፡ በዚህ ጽሑፋችን ስለ ራሱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማየት እንሞክራለን፡፡
በዚህ ከንቱ ዓለም ላይ የሕይወትን ዋጋ ከፍ ያደረገ፣ የተለያዩትን ወገኖች ያገናኘ ፣ መርዶ በበዛበት ዘመን የምሥራችን የሰበከ  መጽሐፍ ቅዱስ ነውና እኛም በጸሎትና በጽሞና ሆነን ልናነበው ይገባናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም፡- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ& የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” (2ጢሞ. 3 &16-17) ብሏል፡፡
    

v   ለበጎ ሥራ የተኛውን ልብ የሚቀሰቅስ ደውል
v   ለመንፈሳዊ አካለ መጠን ለመብቃት ለሚጓጓ ምእመን ሙሉ ሰው የሚያደርግ ምግብ
v   በድንቁርና ጨለማ ለሚኖረው ሰው ወደ ብርሃን የሚያወጣ
v   በክፉ ሥራው ለሚዝናና ፍርድን የሚገልጥ
v   አስተሳሰቡ ለዛገ ራእይ የሚሰጥ
v   በምድር ለሚኖረው ሰው ሰማይን የሚያሳይ የእምነት መነጽር መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡   ከዚህ ሁሉ በላይ ፡-
v   ከሰማያዊ አባት ለምድራዊ ልጆቹ የተላከ የፍቅር መልእክት ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡  ደግሞም፡-
v   ተነቦ የማያልቅ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡
                                                                                         ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም