መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » መጽሐፍ ቅዱስ » መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል አራት

የትምህርቱ ርዕስ | መጽሐፍ ቅዱስ / ክፍል አራት

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ

                                                         
                                                                                   ሐሙስ  ሐምሌ  10/2006 ዓ.ም.
የእግዚአብሔር ቃል

ሰውዬው ሌባ ኖሯል፣ ሊሰርቅ ሲሄድ መንገድ ላይ አንድ ግርማዊ መጽሐፍ ወድቆ ያያል፡፡ “እንዴት ያለው ከርፋፋ ሰው ነው ይህን ጥሎ የሄደው” ብሎ ብድግ አድርጎ ሲገልጠው ልክ ዘፀ.20 ላይ ይከፍተዋል፡፡ ዓይኑም በቀጥታ ቊጥር 15 ላይ ሲያርፍ “አትስረቅ” የሚል ቃል አየና በጣም ተናደደ፡፡ “ድሮም በዚህ አመልህ ነው የተጣልከው” ብሎ ወርውሮት ጉዞውን ቀጠለ፡፡ እልፍ እንዳለም ጓደኞቹን ያገኝና፡- “እናንተ ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ መንገድ ላይ ወድቆ አግኝቼ ጥዬው መጣሁ” ይላቸዋል፡፡ እነርሱም፡- “ለምን ጣልከው? አታነበውም ነበር ወይ?” ቢሉት እርሱም፡- “ምን አነበዋለሁ እርሱ ቀድሞ አነበበኝ እንጂ” አለ ይባላል፡፡
መጽሐፍ ሐቀኛ ጓደኛ ነው ቢባልም ሐሰተኛ ጓደኛ እንዳለ ሁሉ ሐሰተኛ መጽሐፍም አለ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ቃሉ የማይለውጥ በዘመናት የሰው ልጅ ወዳጅ ነው፡፡ ሰዎች በሕይወታቸው ድራማ እየሠሩ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መስማትም ሆነ ማወቅ አይፈልጉም፡፡ እውነቱን መሸሻቸው ስህተታቸውን ማወቃቸው ነውና ከፍርድ አያመልጡም፡፡ የሚሠሩትን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚቃወም ካወቁ መጽሐፍ ቅዱስን ያውቃሉ ማለት ነው፡፡ ከራሱ ጋር መገናኘት ለሚፈልገውና የጭንብል ኑሮ ለሰለቸው ሰው መጽሐፍ ቅዱስ መልስ ነው፡፡ በክርስቶስ ካመንን ሊኖረን የሚችለው ትልቁ ሀብት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሕያው በሆነው በክርስቲያኖች ሰውነት /መቅደስ/ ያድራል (1ቆሮ.3÷6-17፤ 6፥19-20)፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራ መንፈስ በመሆኑ ተሠርተን የማናልቀውን እኛን በቃሉ እየጠረበ እየቀረጸ ክርስቶስን ወደ መምሰል ያደርሰናል፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ መንፈስ ቅዱስ በአማንያን ሕይወት ስለሚሠራው ሕያው ተግባር ሲገልጽ፡-
         ያጽናናል (ዮሐ.14፥16-17)፣
         ያስተምራል (ዮሐ.14፥26)፣
         ይወቅሳል (ዮሐ.16፥8)፡፡
መንፈስ ቅዱስ የሚያጽናናው፣ የሚያስተምረው፣ የሚወቅሰው በቃሉ አማካይነት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል አጽናኝ ነው (ሮሜ. 15፥4)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል አስታዋሽ ነው፡፡ የመርከቡ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ መርከቡ በምን ያህል የባሕር ጥልቀት፣ በምን ያህል የጉዞ ርቀት ላይ እንዳለ እንዲሁም ለወደቡ ምን ያህል እንደ ቀረው ለመሪው እንደሚያሳይ ቃሉም እንዲሁ ነው (የሐዋ.ሥራ. 27፥25)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ወቃሽ ነው (2ጢሞ. 3፥16-17)፡፡ የዕብራውያን ፀሐፊ፡- “በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ” መሆኑን ይናገራል (ዕብ. 4፥12)፡፡ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ለማንም አይመችም፡፡ ቃሉም ይወቅሳል እንጂ አያዳልልም፡፡

መንፈስ ቅዱስ ያለ ቃሉ አይናገርም፣ ቃሉ ያለ መንፈስ ቅዱስ አይሠራም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር ታላቅ መጽናናትና ራስን ማየት ይገኛል፡፡ መንፈስ ቅዱስም የሚናገረው በቃሉ ስለሆነ የቃሉ ሙላት ያስፈልገናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ከተጠራቀመው ቃል ላለንበት ሁኔታ መልስ የሚሆነውን ቃል በማስታወስ ያጽናናናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ እውቀቱ ፍጹም ቢሆንም የሚናገረን እኛ ቃሉን ባወቅነው መጠን እንጂ በእርሱ መጠን አይደለም፡፡ ይህ ሥነ ሥርዓት ቋሚ ነውና ቃሉን ማጥናት፣ በቃል መያዝ ይገባል፡፡ አንድ ሊቅ በዘጠና ዓመታቸው ከአንድ አባት ጋር ተገናኙና “አለቃ አሁንስ ምን እየሠሩ ነው?” ቢሏቸው፡- “አሁን ዓይኔ እየደከመ ስለሆነ የሚያነብልኝ ልጅ ስለሌለኝ ለቀሪው ዘመኔ ትንቢተ ኢሳይያስን በቃሌ እያጠናሁ ነው” ብለዋል፡፡ በእውነትም የቃሉ ረሀባቸው ሲደንቀን ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም ስለ ክርስቶስ አብዝቶ የሚናገረውን “የብሉይ ኪዳን ወንጌል” የሚል ስያሜ ያገኘውን የኢሳይያስ መጽሐፍ መምረጣቸው በእርግጥም አዋቂ ያሰኛቸዋል፡፡ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፡- “ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ የክርስቶስን መምጣት ስም ጠርቶ መከራውንም ገልጦ ተናግሯል፤ ጽፏልም፡፡ የእርሱም ትንቢት ከ500 ዓመተ ዓለም በፊት የተጻፈ ሲሆን ከክርስቶስ በኋላ የተጻፉትን ወንጌላት ይመስላል፤” ብለዋል (ትምህርተ ክርስትና ፣ 1979 ዓ.ም፤ ገጽ 75)።
የእግዚአብሔር ቃል
እግዚአብሔር የሚናገር አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመናገር ክብሩን ይገልጣል፡፡ እርሱ በአንድም በሌላም መንገድ ይናገራል፡፡ አለማስተዋል ግን ሰውን ይበድላል፡፡ እግዚአብሔር ሲናገር ምሪት ይገኛል፡፡ እግዚአብሔር ያልተናገረው ሰው የት እንደሚሄድ አያውቅም፡፡ ካርታውን እንደ ጣለ መንገደኛ ከርታታ ነው፡፡ እግዚአብሔር በገርነት ለሚሰሙት በዘመናት ሁሉ ይናገራል፡፡ የሰው ልጆች እግዚአብሔር ዝም ባለበት ዘመን ይጨነቃሉ፡፡ አንድ ታላቅ ወዳጅ ዝም ሲል መልመድ እንደሚከብድ ሁሉ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ቃል እንዲናገረው ያልፈቀደ ሰውም ወዳጁ የኮረፈበትን ሰው ይመስላል (1ሳሙ. 3፥21)፡፡ እግዚአብሔር በእስራኤል ዙሪያ ከነበሩት የአሕዛብ አማልክት ጋር የተነጻጸረበት አንዱ ክብር የሚናገር አምላክ መሆኑ ነው (መዝ.115 በዕብራይስጥ ቊጥር 3-7)፡፡
ነቢዩ ዳዊት፡- “ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ የለም፤ እስከ መቼ እንዲኖር የሚያውቅ በእኛ ዘንድ የለም” ብሏል (መዝ. 73(74)፥ 9)፡፡ ነቢይ ቃሉን ተናጋሪ (ሰባኪ) ነው፡፡ ቃሉ ሲነገር ምልክት ይታያል፣ የዘመን ልክ እንኳን ይሰፈራል፡ እስከ መቼ እንደምንኖር ይታወቃል ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም (ሰቆቃወ ኤር.2፥9፤ ሕዝ.7፥ 26 ፤ አሞጽ 8፥11)ን አንብቡ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ወይም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት አማንያን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ እግዚአብሔር ቃል ለመቀበል ቢያንስ ሦስት ነገሮችን ተጠቅመዋል፡-
1.       የታሪክ ማስረጃ
የሥጋና የእምነት አባቶቻቸው የሆኑት ርእሳነ አበው፣ ነቢያትና ፀሐፍት በእውነት አንዱን እግዚአብሔር እንዳገለገሉ በታሪክም በዘመናቸውም አይተዋል፡፡ ዓለምን በመናቅ፣ የወንድምን ፍቅር ከገንዘብ ፍቅር በማስበለጥ የኖሩ አገልጋዮች ናቸው፡፡ በጎነት ሥራ ነው፡፡ ሥራ ደግሞ አሠሪ አለው፡፡ ስለዚህ ከበጎነታቸው ጀርባ የቆመው ምንድነው? ሲሉ እግዚአብሔርና ቃሉ ሆኖ ስላገኙት መጽሐፍ ቅዱስን እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀብለውታል፡፡
  
2.      ተአምራት
መጽሐፍ ቅዱስ በተአምራት ዜና የበለፀገ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተአምራት ተአምራት የሚለው ግን የሰውን መለወጥ ነው፡፡ መጽሐፉ የተጠቀሱት ተስፋዎችን በእምነት ሲጠቀሙ ጉድለታቸው ስለሞላ ቃሉን እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀብለውታል፡፡
  
3.     ሕሊና
የሰዎችን ሕሊና መዋሸት ቢቻልም የራስን ሕሊና መዋሸት ግን አይቻልም፡፡ ሕሊና በኃጢአት ምክንያት ሊሞት ይችላል (ዕብ. 9፥14)፡፡ በክርስቶስ ስናምን ግን ይድናል፡፡ ስለዚህ በስህተታችን ዝም አይለንም፡፡ የብሉይ ኪዳን አማንያን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ እግዚአብሔር ቃል የተቀበሉት እንዳሳረፋቸው ውስጣቸው ስለሚመሰክርላቸው ነው፡፡ ሌሎች ወገኖች አያሳርፍም ቢሏቸው እንኳ ሕሊና ከሁሉ ቀድሞ ያረጋግጥላቸዋል፡፡
የአዲስ ኪዳን ዘመን አባቶች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ቊጥር ለመወሰን ብዙ ጥረዋል፡፡ ምክንያቱም ከእውነተኞቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር የሚመሳሰሉ የስህተት ወንጌሎች በደቀ መዛሙርቱ ስም ተጽፈው ስለነበር ነው፡፡ ወንጌላቱም የተሰየሙት እንደነቶማስ እንደነበርናባስ ባሉ መልእክት ባልጻፉ ደቀ መዛሙርት ስም ነው፡፡ ይህን ሐሰተኛ ጽሑፍ ለመለየትና እውነተኞችን በቀኖና ለመወሰን የተጠቀሙበት ዘዴ ቢኖር፡-
         ከታወቁት ሐዋርያት መጻሕፍት ጋር የአሳብ አንድነት እንዳላቸው በማዛመድ፤
         ከብሉይ ኪዳን ፍሰት ጋር በትክክል መቀጠሉን በመገምገም፤
         የኢየሱስ ክርስቶስን የቅድስና አኗኗርና አዳኝነት ማዕከል ማድረጋቸውን መፈተን ናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃልነቱን ያረጋገጠው ራሱን ለፈተና በማቅረብ መሆኑን ሲገልጽ ነቢዩ ዳዊት፡- “በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው” (መዝ.11(12)፥6) በማለት ተናግሯል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጠበቃ የሚሻ መጽሐፍ ሳይሆን ምስክሮች ያሉት መጽሐፍ ነው፡፡ ምስክሩ ሕይወታቸውና ኑሮአቸው ነው፡፡ ጠበቃ ውሸትን እውነት ለማድረግ ሊታገል ይችላል፡፡ ምስክር ግን ሕይወቱን ዋቢ አድርጎ ይጠቅሳል፡፡ ይህንን ማን ሐሰተኛ ይለዋል? አርፌአለሁ የሚልን አላረፍክም በማለት የትኛው አንቀጽ ይጠቀስበታል?
እኛም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ የምንናገረው አለን፡-
         የቃሉን እውነትነት በተመለከተ የሚገድሉ ሳይሆን የሚሞቱለት ሠራዊት እንዳሉት በታሪክ አይተናል፡፡ እውነት ላልሆነ ነገር ሰው እንዴት ውድ ነፍሱን ይሰጣል?
         ትምህርቱ ተግባራዊ ሲደረግ ፍቅር የሰፈነበት ማኅበራዊ ግንኙት ታይቷል፡፡ ታዲያ መልካም ያልሆነ ነገር እንዴት መልካም ያደርጋል?
         እኛን ሲያሳርፈን አይተናል፡፡ ንጹሕ፣ ምቹ፣ ሰላማዊ ያልሆነ ነገር እንዴትያሳርፋል?
እግዚአብሔር እንደ ቃሉና እንደ ስሙ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ታሪክ አደራውን ለእግዚአብሔር ሲያስረክብ “ምን ታዘብክ?” ተብሎ ከተጠየቀ “እግዚአብሔር ሆይ ሰው ያለው እንደማይሆን አንተ ያልከው ብቻ እንደሚሆን ታዘብኩ” ሳይል አይቀርም፡፡ ቃል ረቂቅ ነው፡፡ ረቂቁ ቃል በጽሑፍ እንደሚታይ ረቂቁ የእግዚአብሔር ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ገዝፏል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የእግዚአብሔር ቃል ሲል ሦስት ነገሮችን ያመለክታል፡፡ አማርኛችን ተለዋጭ መጠሪያ ስለሌለው ሁሉንም የእግዚአብሔር ቃል ቢለውም አዲስ ኪዳን የተጻፈበት የግሪኩ ቋንቋ ግን የተለያየ መጠሪያ በመስጠት ይለየዋል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ሲባል ሦስት ነገሮችን ይገልጻል፡፡

                                                     ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም