“ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ” /ማቴ. 1፡3/ ።
ይሁዳ ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን የወለደበት መንገድ የኃጢአት ጉዞ ያለበት ነው ። ትዕማር የልጁ ሚስት ስትሆን ልጁ ከሞተ በኋላ ጋለሞታ ሴት መስላ ከይሁዳ ጋር በመተኛቷ መንታ ልጆችን ፋሬስንና ዛራን ወለደች ። /ዘፍ. 38/። ይሁዳ ለንግሥና የተመረጠ ነገድ ነው ። ጌታችን በሥጋ የሚወለድበት ዘር ነው ። የይሁዳ መንገዱ ቀና አልነበረም ። እግዚአብሔር ግን በመጥራቱ የማይጸጸት ፣ በመስጠቱ የማይቆጭ አምላክ ነው ። ስለዚህ ይሁዳን ለዚህ ታላቅ ክብር አጨው ።
የሰው ልጆች በክፋት መጠን እንጂ በፍጹምነት እርስ በርሳቸው ሊወዳደሩ አይችሉም ። ከአዳም ጋር አብረው ስለወደቁ ይብዛም ይነስም ሁሉም የራሱ የሆነ ስህተት አለው ። ታዲያ ሰው በተፈጥሮው ለራሱ ስህተት ፈጥኖ ይቅርታ ሲያደርግ የሌላውን ስህተት ግን በፍርድ መዳኘት እንዳለበት ያምናል ። ይህንን ጠባይ ከይሁዳ ማየት እንችላለን ። ትዕማር መልኳን ቀይራ ፣ ጋለሞታ ሴት መስላ ይሁዳን ጠበቀችው ። እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ በጠየቀ ጊዜ መያዥያ እንዲሆን በትሩን ቀለበቱን አምባሩን ስጠኝ አለችው ። ይህንንም ይዛ ተሰወረች ። ኋላ ትዕማር ወይም ምራትህ ሴሰነች ብለው ሲነግሩት ይሁዳ በእሳት ትቃጠል አውጧት አለ ። ከእርሱ እንደ ፀነሰች አላወቀም ። ለመያዥያ የወሰደችውን ቀለበትና በትር ስታሳይ ይሁዳ መራራት ጀመረ ።
የሰው ጠባይ እርሱ ካለበት ማንኛውንም ስህተት ይቅር ይላል ። እርሱ ከሌለበት ግን ሞት ይፈርዳል ። ይሁዳ የራሱን ማመንዘር እንደ ተፈቀደ ነገር ያያል ፣ የልጁን ሚስት ግን ይጠብቃል ። ዓይኖቹ የሚያዩት ፣ ጆሮዎቹ የሚሰሙት ሌሎችን ነው ። ሌሎችን ሲጠብቅ እርሱ ራሱን ጎድቶ ነበር ። ትዕማር ይሁዳ ይህን እንደሚያመጣ አውቃ ተዘጋጅታበት ነበር ። ሌሎችን የሚያጠምዱ ራሳቸው ይጠመዳሉ ። የሌሎችን መረጃ የሚያሰባስቡ የእነርሱም መረጃ ይሰባሰባል ። ይህችን ዓለም ግን የሚፈውሳት ምሕረት ብቻ ነው ።
ይሁዳ መንገዱን ብዙ ጊዜ አበላሽቷል ። እግዚአብሔር ግን እንደ ገና መንገዱን እያስተካከለ ይታደገዋል ። የእግዚአብሔር ምርጫ ዋስትና ያለው ነው ። ደከሙ ፣ ሰነፉ ፣ መከኑ ብሎ የማይተው አምላክ ነው ።