የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቀን ያለው ቀን ሰጠኝ

                                                       ቤተ ጳውሎስ፤ ሚያዚያ 9 2004 ዓ.ም.
                                                               በዳቦ አላስቆረስኩም
ገድሎ ማዳን ሳይሆን ሞቶ ማዳን ማለት
ምን ዓይነት ስሌት ነው ምን ዓይነት ጀግንነት?
ተወልዶ ያደገው በመስቀል የሞተው ደግሞም የተነሳው
የማዳን ክዋኔው ጥበቡ ስውር ነው ምሥጢሩም ጥልቅ ነው
ስለፈሩት አይደል ወይ ስለተወደደ
ስለ ፍቅር ብሎ ከሰማይ ወረደ
ነጻነት ለማወጅ በራሱም ፈረደ
ሰው ሆነና ሞተ ለጥቆም ተነሳ የሚለው ቃላችን
መሠረቱ ይኸ ነው ድኅነተ እምነት በክርስትናችን
አምላክ የወደደን እኛ ስንከዳው
ይህን ያስፈጸመው ምክንያቱ ምንድነው?

ከተከታተልነው ነገሩ እንዲህ ነው
ሁሉን አስተካክሎ ሁሉን አሟልቶለት
በአምሳሉ ፈጥሮ ሲያኖረው በገነት
ህያው እንዲሆንም እስትንፋሱን ሰጥቶት
እባብ አሳመጸው መስሎ ያዘነለት
ተንኰልን አስቦ በጸጋው ቀንቶበት
እንዲያው ለመሆኑ ፈጣሪ ምናለ?
ምንን ፈቀደልክ ምንን ከለከለ ?
እያለ ጠየቀ ያዘነ መሰለ
                  በዓይኑ አባብሎ እየሸነገለ
ሴት በየዋህነቷ አስረዳች በዝርዝር
እንዳልተከለከሉ ካንዲቷ ዛፍ በቀር
ይህችን ዛፍ እኮ አትብሉ ያላችሁ
እንዳታውቁበት ሁሉን ለይታችሁ
ክፉና ደግ ይህ ነው ማለት ከቻላችሁ
እንግዲያውስ ከርሱ በምን ታንሣላችሁ?
አምላክ እንዲሆኑ ፍሬን የበሉ ዕለት
ማለ ተገዘተ ሞልቶት ምቀኝነት
አዳምም እንዳሉት የበለስን ፍሬ በላ እያጣጣመ
በነዚህ ምክንያቶች ትእዛዝ አፈረሰ በደልን ፈጸመ።
አዘነ አለቀሰ ጸጋው ተገፈፈ
ራቁት መሆኑን ለሔዋን ለፈፈ
ቅጠልን ለበሱ ሱባዔ ቆጠሩ
ይቅር እንዲላቸው ጾም ጸሎት ጀመሩ /ስለ ቁም ነገር የታከለ/
እግዜርም ያዳምን መሸሸጉን አውቆ
ሃዘን ከቁጣው ጋር በአንድነት ደባልቆ
አዳም በማጥፋቱ ጣሙን አዝኖበት
ጠባቂ አቆመ ከገነት አባሮት
የሞት አዋጅ ወጣ በይፋ ታወጀ
ለሰው ዕድሜ ሁሉ ገደቡ ተበጀ
ስለ ጸሎታቸው ስለጸጸታቸው ቃሉንም ሰጣቸው
ከልጅ ልጅ ተወልዶ እንደሚያድናቸው
ወድቀው ስለቀሩ በእባብ ተታለው
የዘር ቅራኔውም ተዘራ መሃላቸው
ወደ ዓለም ተጥሎ መከራው በዛበት
ሃሩሩና ቁሩ ረሃብ ከድካም ጋር ተፈራረቁበት
ሁሉንም አሰበ ለማግኘት መድኀኒት
ወደ ጥንት ክብሩ የሚመለስበት
ከፈጠረው አምላክ የሚታረቅበት
ጀግናው እስከሚገኝ ንጉሡ እስኪመጣ ዘመን ሰነበተ
የአዳም ዘር በሙሉ መላን በመፈለግ በእጅጉ ታከተ
ተስፋውን ቆረጠ ራሱን አወቀ አቅም እንደሌለው
ተማጸነ አምላኩን አንዴ እንዲያድነው
ማለ ተገዘተ ሌላም እንዳይለምደው
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ሁነው መከሩ አንድ ሁነው አሰቡ
ፍርድ ሳይቀለበስ ይቅርታን ለማምጣት  እጅግ ተጠበቡ
ገብርኤልን ተልኮ፣ ብሥራት ቀረበ
ቃለ እግዚአብሔር በድንግል አደረ
ወልድ አምላካችንም ከድንግል ተወልዶ እንደኛው ሰው ሆነ
ዓለም የማትበቃው የፍጥረት ፈጣሪ በእቅፍ ተመጠነ
መድኅን እንደሚሆን ቀድመው ስላወቁት
የፊተኛውን ቃል ኢየሱስ ነህ አሉት
ሥጋን በመዋሃድ ፍጹም ሰውን ሆነ
ጥምቀትን ተጠምቆ ጽድቅንም ከወነ
ከቆሮንቶስ ሄደ መከራን ቀመሰ ስለዓለም መነነ
በሥጋ ባህርዩ ደከመ ተጠማ በራብ ተፈተነ
ሥራውን ባረከ መንገዱን ቀደሰ
ህዝብን ለማስተማር ሥርዓትን ቀየሰ
ድውይን ፈወሰ በመንፈስ አከመ
ትንግርትን አሳየ ታምራት ፈጸመ
የጠፋ ወገኑን እንደገና ሊያድስ
የወደቀ አዳምን ዳግመኛ ለማንገስ
በመስቀል ላይ ዋለ ሞትንም ሞተልን
በተስፋው ቃልና በወደደን መጠን
በመስቀል ላይ ሞተ ደሙን አፈሰሰ ድልን ተቀዳጀ
ካሳው ተከፈለ ዳናችሁ ተባልን አዋጁም ታወጀ
ሞት በሞት ተሻረ ኃጢአት ተቀበረ
ገነት ተከፈተች የአዳም ዘር ከበረ
ለልጅ ልጁ ሁላ ብሥራት ተነገረ
ሲዖል ተከፈተ ስሙ ተሰበከ ነፍሳት ተለቀቁ
ሰይጣን ድል ሆኖ ሲታሰር ሲመታ እነሱ ቦረቁ
ከእንግዲህ በኋላ በኢየሱስ ስም አምነን
ትንሣዔ ስላለን እስከ ዘለዓለም እኛም እንድናለን።
ከጥፋቴ በልጦ የታደልኩት ምህረት በብዙው ረድቶኝ
ልብ እንድገዛና አምኜ እንድድን የዛሬን ቀን ሰጥቶኝ
ከገባሁበትም ከድካም አረንቋ በድሉ አወጣኝ፡፡
ስለዚህ ወገኖች አበርቱኝ አጽናኑኝ ፈቃዱን ልፈጽም
ኃጢአቴን ቀብሬ የኔዋም ትንሣዔ ከሱው ጋር ትፈጸም ፡፡
በሞተልኝ ጌታ እምነቴ ይጠንክር ይሄ ቀን ሳይጨልም ፡፡

 ይህ ግጥም፣ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር . . .!!!  ተብሎ ቀርቦ የነበረው ጽሑፍ ላይ ትጉህ አንባቢ እና ግሩም ተሳታፊ በሆኑት፣ የጡመራው ተከታታይ ዳቦ አላስቆረስኩም በአስተያያት መልኩ የቀረበ ሲሆን መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበታል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ