የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በክርስቶስ ፍቅር ዓለምን ስለመናቅ

ዓለምን በመናቅ ክርስቶስን ማወቅ አትችልም ፡፡ ያለ ክርስቶስ ፍቅር ዓለምን በመናቅህ ተስፋ ቢስና ተጨናቂ ሰው ትሆናለህ ፡፡ ሁሉም ነገር ከንቱና ፍጻሜ የሌለው ሁኖ ይታይሃል ፡፡ በክርስቶስ ፍቅር ዓለምን ስትንቅ ግን ከፀሐይ በላይ ላለው ዓለም ፍቅርህ ይጨምራል ፡፡  በክርስቶስ ፍቅር ውስጥ የሰዎችን ንቀትና ትችት ማለቂያ የሌለውን መሰናክል ትረሳለህ ፡፡ ፍቅሩ ከሺህ ሠራዊት ይልቅ እየከበበህ ፣ ከምቹ ትራስ ይልቅ እያሳረፈህ ፣ የሌሊት ብርሃን የቀትር ጥላ ይሆንልሃል ፡፡ አዎ በክርስቶስ ፍቅር ሁነህ ዓለምን ስትንቅ ቸርና ሌሎችን ሸፋኝ ትሆናለህ ፡፡ ክርስቶስ የሌለበትን ከፍታ እንደ እንጦሮጦስ እንደ ጥልቀት መሠረት ፣ ኢየሱስ ያልከበረበትን ኅብረት በዱር እንደ መቀመጥ ትቆጥረዋለህ ፡፡ ዓለምን ስትንቅ ገንዘብን ሳይሆን ወዳጆችን ፣ ክብርን ሳይሆን አገልግሎትን ፣ ዙሪያህን ሳይሆን ሰማይ ማየት ትጀምራለህ ፡፡ በሥጋዊ ዓይንህ ሰማይን እያየህ ብትራመድ ትደናቀፋለህ ፡፡ እንዲሁም ለምድራዊ ጥቅም ብቻ ሰማይን መፈለግ የሁለት ዓለም ስደተኛ ያደርግሃል ፡፡ ብዙዎች በእግዚአብሔር ቤት የሚኖሩት ለምድራዊ ቤት ነው ፡፡ ለዚህ ነው በሰላም አደባባይ ጠበኞች ፣ በፍቅር ቤት ነገረኞች የሚሆኑት ፡፡ የክርስቶስ ፍቅር ለሁሉ ነው ፡፡ ፍቅሩ እንኳን ሰውን እንስሳንም አያገልልም ፡፡ ለእጽዋትና ለአእባን እንኳ ይህ ፍቅር ከለላ ይሰጣል ፡፡ ፍቅሩን ግን ማጣጣምና ምላሽ መስጠት ላንተ ተሰጥቷል ፡፡ ወዳጄ ሆይ ንግድህ ሲከስር ፣ ወዳጆችህ ሲርቁ ፣ ኢኮኖሚህ ሲናጋ ዓለምን ወደ መናቅ ትመጣለህ ፡፡ ዓለምን መናቅ ግን ውስጡ ብስጭትና የበቀል ስሜት ደግሞም ያለመፈለግ ስሜት ካለው ይህ መናቅ ከክርስቶስ ፍቅር የሚነሣ አይደለም ፡፡ የክርስቶስ ፍቅር ውስጥህን ሲገዛው በድህነትህ የምትኮራ ፣ ስለ አምላክህ የሚደርስብህን ግርፋት እንደ ሽልማት የምትቆጥር ትሆናለህ ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ