መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » በጌታ መተያየት / 2

የትምህርቱ ርዕስ | በጌታ መተያየት / 2

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ

                                                                  ማክሰኞ ጥቅምት  11/  2007 ዓ/ም
    የእግዚአብሔር ቃል ሰው በፈጣሪው መልክና ምሳሌ እንደተበጀ ይነግረናል፡፡ ሰው ለእግዚአብሔር የትዕዛዝ ቃል ያለመታዘዝን ምላሽ ባሳየ ጊዜ የኃጢአት ደመወዝ የሆነው ሞት ወደቀበት፡፡ በደልም በአንድ ሰው ምክንያት ወደ ዓለም ገባ፡፡ የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔር ክብር ጐሎታል ተባለለት፣ እንደ እግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረው ስብእና (ጥንተ ተፈጥሮ) በኃጢአት ምክንያት ረገፈ፡፡ ከዚህም የተነሣ ሰው ከበደል በፊት በነበረው ክብርና ደረጃ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት መቅረብ አልተቻለውም፡፡ ለዘመናትም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የጠብ ግድግዳ ሰለጠነ፡፡ 
    ኃጢአት በእንስሳት መስዋዕት እየተዳፈነ፣ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ የማግኘት መሻታቸው በጣዖት እየተደለለ፣ የሰው ጽድቅ እንደ መርገም ጨርቅ እየተቆጠረ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ሞት ገዛ፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ምንኛ ልብን የሚነካ፤ አእምሮንስ የሚያልፍ ነው? አባት የሚወደውን አንድያ ልጁን ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ አድርጐ ላከ፣ አብ በልጁ የሚያምኑትን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጁን በወደደበት ፍቅር ወደደን፣ ልጆች እንጂ ዲቃላ፤ ራስ እንጂ ጅራት አይደላችሁም ብሎ ቃል ኪዳኑን አተመ፡፡ ሰውም ወደ እግዚአብሔር አባቱ የሚቀርብበትን ብቃት፣ የሚታይበትን መልክ፣ ተቀባይነት የሚያገኝበትን ጽድቅ አገኘ፡፡ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱሱ ነው!

    ሕይወት በሆነው ክርስቶስ የዘላለም ኑሮ፣ እውነት በሆነው ክርስቶስ የዘላለም እውቀት፣ መንገድ በሆነው ክርስቶስ የዘላለም ዕረፍት ለሚያምኑ ሁሉ የተዘጋጀ ብድራት ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ በእኛነታችን ሲያየን ሞት የተፈረደብን ኃጢአተኞች እንደሆንን ያውቃል፡፡ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያይ ደግሞ ለሰዎች ኃጢአት ብሎ ደዌን የተቀበለ፣ ሕመማችንን የተሸከመ፣ እስከ መስቀል ሞትም የታዘዘ ጻድቅ እንደሆነ ይመለከታል፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር በማን በኩል ይየን? 
    እስቲ እግዚአብሔር ለአፍታ በጐረቤታችሁ በኩል እንደሚያያችሁ አስቡ፡፡ እግዚአበሔር በሥራ ባልደረባዬ፣ በመንደር ጓደኛዬ፣ በአደባባይ ባልንጀራዬ በኩል ቢያየኝ ምን ይሆናል? ብላችሁ ጠይቁ፡፡ ሰው እንደሚያይ ያላየን እግዚአብሔር ይባረክ፡፡ ሰው እንደሚሰማ ያልሰማን፤ እንደሰው መረዳት ያልተረዳን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ የምንከፍለው ለሌለን በተከፈለው በኩል፣ የምናቀርበው ለሌለን ያለ ነውር በዘላለም መንፈስ በቀረበው መስዋዕት በኩል መታየት ዕድል ፈንታችን ነው፡፡ ምክንያቱም በአብ ፊት መታወቃችን ፣ በጸጋው ዙፋን ፊት መቆማችን፣ ከዘላለም የእግዚአብሔር ቁጣ ማምለጣችን በቀራንዮ ከሆነው ቤዛነት የተነሣ ነው፡፡ የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ ፡- “ ክርስቶስ በእጅ ወደተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡” (ዕብ.9÷ 24) ይላል፡፡ 

በጌታ መተያየት፡-
1.   አቅምን ማወቅ ነው፡- ትልቁ ነቀፋ “አቅሙን አያውቅ” የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ ለእኛና ለሌሎች ሊሠራ ያለውን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ረጅም ጊዜ የሚወስደው አቅማችንን እንድንረዳው በማድረግ ነው፡፡ ድካሙን ያልተረዳ ብርታትን ሊናፍቅ አይችልም፡፡ ጉድለቱን ያላመነ ሙላቱን ማስተዋል አይሆንለትም፡፡ አለመቻልን መገንዘብ ከሚያስችለው ጋር ለመገናኘት ጉዞን የማጋመስ ያህል ነው፡፡ 
   አዳምና ሔዋን ተማክረው የሆኑት ኃጢአተኛ ነው፡፡ የሰው ምክር የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያቆምም፡፡ የሰውም መቻል የተብራራው “ሁሉ ኃጢትን ሠርተዋል” (ሮሜ.3÷11-18) በሚል ነው፡፡ በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን እንደነበርን ስንረዳ ባለጠጋ የሆነው እግዚአብሔር ከልጁ ጋር የሰጠንን ሕይወት እናከብረዋለን፡፡ በሚያስፈልገንም ሁሉ የሚረዳንን ጸጋ እናገኝ ዘንድ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቀርባለን፡፡ (ዕብ.4 ÷16) 
2.  ውለታን መዘከር ነው፡- አንድ ልጅ የእናቱን የሻከረ እጅ፣ የጠቆረ ፊት፣ የኮሰመነ ሰውነት፣ የሳሳ ጠጉር፣ ያደፈ ልብስ ሲመለከት የእርሱ እዚህ መድረስ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ይረዳል፡፡ አስተዋይም ከሆነ ዘመኑን ሁሉ ሲዘክረው ይኖራል፡፡ እርሱ ባማረ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሲሠራ ጉሊት ተቀምጣ ድንጋይ ከስር ፀሐይ ከላይ የቆረቆራትን፣ እርሱ በለሰለሱ እጆቹ ብዕርን ከወረቀት ሲያገናኝ እጇ እስኪላጥ ልብስ አጥባ ያለበሰችውን እናቱን ይዘክራል፡፡ ለሰጪው ትልቁ ምላሽ ስጦታውን እያሰላሰሉ መኖር ነው፡፡ 
    እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን እንኳን እንደ ሸማኔ መወርወሪያ በሚፈጥነው የምድር ዘመናችን ቀርቶ ከሞት በኋላ ባለው የዘላለም ኑሮም ተርከን አንዘልቀውም፡፡ በጌታ መተያየት ስንችል ብቻ የተደረገልንን እናስተውላለን፡፡ በጌታ መተዋወቅን ኑሮ ስናደርግ ብቻ የቀራንዮ ፍቅር ኩልል ብሎ ይገባናል፡፡ በዚህ ጌታ እየተያዩ መኖር እግዚአብሔር ለዓለሙ ሁሉ እንዲሁ ያደረገውን ድንቅ መዘከር ነው፡፡ (መዝ.51÷ 9)
3.  ወደ ፊት መዘርጋት ነው፡- ክርስትና ባሉበት የመርገጥ ኑሮ ሳይሆን ከዕለት ወደ ዕለት የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ዘንድ ወደሚሆን ክርስቶስ ኢየሱ የማደግ ሕይወት ነየማለሐስ የማደግ ሕይወት ነው፡፡ (ኤፌ.4÷ 15) በጦርነት መሐል ያለ አንድ ወታደር በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከዓላማው አንጻር እንጂ ዕቅዱን ከሰዎቹ አንጻር አይመለከትም፡፡  ይህንን ካረገ ግን ወደፊት መዘርጋት ያከትምለታል፡፡ ለጀግናውም “እጅ ወደላይ” ይባልለታል፡፡ በክርስትናም በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት እያስተዋሉ መጓዝ ባለራዕይነት ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ በጌታ መተያየ ድላችንን ያሮጠዋልና በዚህ ትጉ!
 
4.  ሕብረትን ማጠንከር ነው፡– አብዛኛውን ጊዜ ሕብረት ላለማድረግ ቋሚ ፈተናችን የሰውን ጉድለት መመልከትና ድካምን መቁጠር ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የተሻለ የምንለው ሰብእናችን የባሰ ከምንለው ማንነት ጋር መተባበር ጭንቁ ነው፡፡ በጉድለት ውስጥ ሆኖ ያለ ጉድለት የሆነን ነገር ማሰስም የሰው ግብዝነት ነው፡፡ እግዚአብሔር በልጁ በኩል ያደሰው ከእርሱ ጋር ያለንን ሕብረት ብቻ አይደለም፡፡ ከሌሎች ጋር ያለንንም ግንኙነት አዲስ አድርጓል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ልበሱት በተባለለት አዲሱ ሰው መድኃኒዓለም ነው፡፡፡ (ኤፌ.4÷24) በጌታ መተያየት ለሕብረት ጤናማነት ዋስትና ነው፡፡ 
    ዛሬ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የሚበጠበጡት ሰዎች የእግዚአበሔርን አሳብ ትተው በአሳባቸው በኩል፣ የእግዚአብሔርን ዓላማ ወደ ጐን አድርገው በግል ራዕያቸው በኩል መተያየት በመጀመራቸው ነው፡፡ ሰላማችን በሆነው በአንዱ ጌታ በኩል መተያየት ግን ከብዙ ኪሳራ ያድናል፡፡ እርሱ እንደሚያይ የማየትም ጸጋ ይበዛልናል፡፡ በወንድሞች መካከል የተገለጠ ድካም ቢኖር እንኳን የኃጢአትን ብዛት በሚሸፍን ፍቅር የመክደንን አቅም እናገኛለን፡፡
    አካል በአካሉ ላይ ሊፈርድ፤ በጉድለቱስ ሊያጥላላው ይቻለዋልን? አፍንጫ በእግር ማንከስ፣ እጅ በዓይን መሸውረር ይስቃልን? ይልቁንም አንዱ ሌላውን ተክቶ ድካሙን ይሸፍናል እንጂ፡፡ በጌታ ስንተያይ ከምናስተውለው እንከን በላይ በክርስቶስ የምንቆጥረው በረከት የበዛ ነው፡፡
5.  ፍትሐዊ መሆን ነው፡- ምድራችን ላይ ከምናስተውላቸው ትልልቅ ችግሮች አንዱ የፍትህ መዛባት ነው፡፡ የሰዎችም የማያቋርጥ ሙግት የፍትሐዊነት መከበር ነው፡፡ በየዕለቱ የምናስተውለው ፍትህን ያላዘሉ አምባገነናዊ ንግግሮች፣ ደሀን የረገጡ የሀብት ክፍፍሎች፣ እውነትን የማያፍሩ የውሸት ዳኝነቶች ናቸው፡፡ ፍትሐዊ ዳኛ የሆነው ጌታ ግን ለዚህ አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሔ ነው፡፡ 
    ሰዎችን በእኔነት ውስጥ ሆነን ስናያቸው ፍትህና መልካምነትን በመስፈርት የሚታደል፤ በጐነትና ፍቅርን በወረፋ የሚከፋፍል እናደርገዋለን፡፡ ከባሰ እስከ ተሻለ፤ ካነሰ እስከ በለጠ ሠንጠረዥ እናወጣለን፡፡ ፍቅራችንም የሥጋና የደም ይሆናል፡፡ ነገር ግን በእውነተኛው ጌታ በኩል ስናይ ለእውነት፣ በሚራራው ጌታ በኩል ስናይ በርኅራሄ፣ ቸር በሆነው በእርሱ በኩል ስናይ ለልግስና እንሸነፋለን፡፡ ፍትህም በልባችን ዙፋን ላይ ያለ ንጉሥ ይሆናል፡፡ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም