ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 26/2004 ዓ.ም.
በዛሬው ዘመን የሰው ልጆች ዓይናቸው የሚያየውን መልካም ነገር ፣ ጆሮአቸው የሚሰማውን መልካም ዜና በመፈለግ ከአገር አገር፣ ከሰው ሰው፣ ከአንዱ የዜና አውታር ወደ ሌላው ይባዝናሉ፡፡ ዓይን አበባን ለማየት የምትመኘው ለጊዜው እንጂ ለዘለቄታው አይደለም፤ ጆሮም የሠርግ ድምጽ መስማት የምትፈልገው ለጊዜው እንጂ ለዘለቄታው አይደለም፡፡ ከአበባ ይልቅ የሚታይ ውበት አለ፣ ከሠርግ ዜማ ይልቅ የሚጣፍጥ ማኅሌት አለ፡፡ ሆዳችን ብቻ ሳይሆን ዓይናችንም ረሀብተኛ ነው፣ ከዓይናችን ይልቅ መንፈሳችን ረሀብተኛ ናት፡፡ እግዚአብሔርን ስናይ ያን ጊዜ ደስተኞች እንሆናለን፡፡ ድምፁንም ስንሰማ ከአሸለብንበት እንነቃለን፡፡ ከደስታዎች ሁሉ የሚልቀው ደስታ ገበሬ በመኸሩ፣ ወታደር በምርኮው ደስ የሚለው ደስታ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ የቤተ ልሔሙ ሕፃን የድንግል ልጅ ኢየሱስ የልብ ደስታ ነው (ኢሳ. 9÷3-7)፡፡ ድምፁም ሙታንን የሚቀሰቅስ ነው (ዮሐ. 5÷25)፡፡
በሐይቲ ግዛት በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሦስት መቶ ሺህ ሕዝብ በላይ ረግፏል፡፡ አንዲት እናት አንድ ልጇ ከጠፋባት አንድ ሳምንት ሆኖታል፡፡ አሳሾችን ይዛ በፈራረሱ ፎቆች ሥር ልጇን መፈለግ ጀመረች፡፡ “አንድ ልጄ ነው፣ ሃያ ሁለት ዓመት በሙሉ ጓደኛዬ እርሱ ነው፤ አይሞትም” እያለች የአደጋ ሠራተኞቹን ትማፀናለች፡፡ እርግጠኛ ቦታው ላይ ሲደርሱ አንድ ሳምንት በሙሉ ሕንፃ ተንዶበት መውጪያ አጥቶ በረሀብ ወደ ሞት እያዘገመ ያለው ልጅ ከነትንፋሹ ተገኘ፡፡ ያ ልጅም ሲናገር፡-“ወደ ሞት እየሄድኩ ነበር፡፡ ‹ልጄ› እያለች እናቴ ስትናገር እንደገና ነቃሁ፡፡ የሞት መንገዴን ያቋረጥኩት በእናቴ ድምፅ ነው” አለ፡፡ የፍቅር ድምፅ የሞት መንገድን ይሰብራል፡፡ ወደ ሞት እየሄዱ ያሉትን የምንመልሳቸው በፍቅር ድምፅ ብቻ ነው፡፡ የእኛ የፍቅር ድምፃችን ወዶን ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መልአኩ ገብርኤል ይዞት የመጣው ብሥራት የፍቅር ድምፅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር አዋጅ፣ የመዳን ብይን ነው፡፡ በሞት ባሕር ሰጥሞ፣ ለሲኦልም ገብሮ፣ የአጋንንትም ተገዢ ሆኖ የኖረውን የሰው ልጅ ከሞት የሚመልስ፣ መቃብር ይደፈን፣ ሲኦል ትዘጋ፣ ሰይጣን ይረገጥ፣ ገነት ትከፈት፣ ትንሣኤ ይታወጅ፣ ሕይወት ታብራ የሚል ብሥራት ነበረ፡፡
ጆሮአችን በየዕለቱ አዳዲስ መከራዎችን ይሰማል፡፡ በአንዱ ጉድ ብለን ሳንጨርስ ሌላ ጉድ ይመጣል፡፡ መከራን ከመልመዳችን የተነሣ የምንጽናናው በጉዳቱ አነስተኛነት ነው፡፡ የምናዝነውም በሞተው ሰው መጠን ነው፡፡ በጎርፍ አደጋ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ ስለ ሞቱ አንድ ሺህ ሰዎች ማዘን ካቆምን ሰንብተናል፡፡ በሱናሚና በሐይቲ ግዛት በደረሰው ርእደ መሬት በእያንዳንዳቸው ከሦስት መቶ ሺህ ሰዎች በላይ ማለቃቸውን ሰምተናል፡፡ የምናዝነው በአደጋው ሳይሆን አደጋው ባደረሰው ጥፋት ከፍተኛነት ነው፡፡ የትላንቱን ጥፋት ካልበለጠ አናዝንም፡፡ በጉድ እየተወዳደርን ያለንበት ዘመን ነው፡፡ በአገራችን እንኳ የምናዝነው በወዳጃችን መሞት ሳይሆን የቀብሩ ቦታ ሩቅ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሥልጣኔ ነው ወይስ ራስ ወዳድነት? መልካም ዜናን ከመጠበቅ ከክፉና ክፉ እያወዳደርን፣ ባነሰው ክፉ እየተጽናናን ነው፡፡ የዓለም መንግሥታት ሁሉ ሰላምን ለማምጣት እየጣሩበት ያለው መንገድ እዚያ ጋ አንዱን ገድሎ እዚህ ጋ ሌሎችን ማሳረፍ ነው፡፡ ዓለም በመልካም ነገር መምጣት ተስፋ የቆረጠች ትመስላለች፡፡ መልአኩ ገብርኤል ይዞት የመጣው የምሥራች ግን ይህን ሁሉ ቅዝቃዜ የሚሽር ነው፡፡
የሰው ልጆች ትካዜን የሚሽር አጽናኝ ቃል፣ ጨለማን የሚገፍ ጽኑ ብርሃን፣ ፍርሃትን ድል የሚነሣ የብሥራት ድምፅ፣ ጠብን የሚገድል የእርቅ ዜና ተርበዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት፡- “በጎውን ማን ያሳየናል የሚሉ ብዙ ናቸው” እንዳለ (መዝ. 4÷6)፡፡ በጎውን ለማየት ሁሉም ናፍቋል፡፡ “ሁሉ በሽተኛ ሁሉ ራሴን ባይ፤ ከቤታችን ደህና መጥፋቱ ነው ወይ?” እንደተባለ በዚህች ዓለም ያላዘነ፣ ያልደከመ የለም፡፡ ባለጠጎችና ድሆች በሆድ ሙላት ቢለያዩም፣ ሁሉም ግን አንድ የሆኑበት ረሀብ አለ፡፡ እርሱም የብሥራት ድምፅ ነው፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የብሥራት ቃል ይዞ ወደ ምድር ሲመጣ የሰው ልጆች በሥጋ ሞት ላይ የነፍስ ሞት፣ በመቃብር ላይ ሲኦል ተጭኗቸው ይማቅቁ ነበር፡፡ ሰማይና ምድር፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ የአዳም ዘርና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ ተጣልተው ነበር፡፡ የሥጋ መከራ፣ የነፍስ ኲነኔ የሰው ልጆችን አስጨንቆ፣ ሞተው እየኖሩ ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት የዘመናትን ጨለማ የሚገፍ፣ የዘመናትን ፍርሃት የሚንድ ብሥራት ይዞ መልአኩ ገብርኤል መጣ፡፡ ብሥራቱ የተላከው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ መልእክተኛው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ዓለምን ወክላ፣ ዘመናትን ወክላ መልእክቱን የተቀበለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡
ብሥራት ትንቢት አይደለም፤ ከዚያ በፊት ብዙ ነቢያት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ወደፊት ስለሚሆነው መልካም ነገር ተናግረዋል፡፡ ብሥራት ግን የቀጠሮ ደስታ ሳይሆን የደስታውን መገኘት የሚያውጅ ነው፡፡ “በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ÷ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ÷ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ” (ሉቃ. 1÷26 -27)፡፡
ይቀጥላል…