መግቢያ » መጽሐፍ ቅዱስ » ብሉይ ኪዳን » መዝሙረ ዳዊት » ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ

የትምህርቱ ርዕስ | ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ

“እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው ።”
መዝ. 33 ፡ 8 ።

በጣም ደግ የሆኑ ሰዎችን እናውቃለን ። ሰው በልቶ የጠገበ የማይመስላቸው ፣ ያንተ እጅ አያጠግብህም በእኔ እጅ ጉረስ እያሉ በላይ በላዩ የሚያበሉ ሰዎች በዙሪያችን አሉ ። ሰለጠኑ የሚባሉት እንኳን በሰው እጅ ሊጎርሱ የራሳቸውንም እጅ ማመን አቅቷቸው ምግባቸውን ወደ አፋቸው የሚያደርሱት በማንኪያ ፣ በሹካና በቢላዋ ነው ። እንብላ ማለትንም እየረሱ ነው ። ሁሉንም ነገር ስሌት ውስጥ እየከተቱት ነው ። ባልና ሚስትም የየግላቸውን ይከፍሉ ይሆናል እንጂ አንዱ ባንዱ ገንዘብ ማዘዝ አይችልም ። በኅብረት ውስጥ ያለ ግለኝነት እንደ መሰልጠን እየታየ ነው ። ኅብረቱም አይቅርብኝ ፣ ግለኝነቱም አይቅርብኝ እየተባለ ነው ። ቀኑን ሙሉ ጋጋሪ አቁመው እንጀራ የሚያስጋግሩ ፣ የጋገሩትን እንጀራ መንገደኛ በልቶ ካልጨረሰው የሚያዝኑ ፣ እንግዳ መቀበል አገልግሎታቸው የሆኑ ሰዎችን እናውቃለን ። ከቤታቸው ደጃፍ አንድ ጎላ ንፍሮ ቀቅለው መንገደኛ ሁሉ ይበላው ዘንድ በየሰንበቱ የሚያስቀምጡ ቸሮችን አይተናል ። እያዘከሩ ሰው የሚሰበስቡ ፣ ማኅበራዊነትና መንፈሳዊነት እንዳይጠፋ የሚታገሉ ብዙዎች ናቸው ። “እኔ ቤት መጥቶ ሳይበላ ነው የሄደው” በማለት ተቀይመው የሚቀሩ ፣ እንደ እናቱ ባያየኝ ነው ብለው አዝነው የሚጎዱ የዋሃንን በትክክል እናውቃለን ። እነዚህ ደጎች ሳይጎድልባቸው እንደ ሰጡ አልፈዋል ። ስጡ ላለው አምላክ ታዘዋልና ተሰጥቶአቸዋል ። በብዛት ሳይሆን በበረከት መኖር ችለዋል ። ዛሬ ብዙ ገንዘብ አለ ፣ በረከት ግን የለም ። ለድሀ አንሰጥም ፣ ለማንድንበት መድኃኒት ግን ብዙ እናወጣለን ። እግዚአብሔር ስንሰጥ በጤና እንደሚከፍለን አናውቅም ። እናውቃለን ብለን ሞኝ ሆንን ። የሌሎች የረሀብ ሕመም ሲሰማን የእኛ ሕመም እየተፈወሰ ይመጣል ።

ቸሮች በታኞች አይደሉም ። ሰውን የሚያሰክር መጠጥ ፣ ሱስ የሚጋብዙ እነዚህ ጥይት የሚመጸውቱ ናቸው ። ቸሮች የሚዘሩ ናቸው ። ዘሪ መሬቱን ያውቀዋል ፣ ከርሞ ይመለስበታል ። ዛሬ ይዘራል ፣ ነገ እዚያው ያጭዳል ። ቸሮች አንድን ሰው ካለበት ሁኔታ እልፍ ማድረግ ፣ ከግብ ማድረስ ዓላማቸው ነው ። ቸር ሰው በበረሃ እንደ ተገኘ ውኃ ነው ፣ ያረካል ። ቸሮች ውስጣቸው ሕያው ነው ፣ እንቅስቃሴ ላይ ሲሆን ሊወጣ የሚታገላቸው ኃይል አለ ። ራሳቸውን በጣም ስለማያዩት ፣ የሌሎች ጉድለት ስለሚታያቸው ደስተኞች ናቸው ። ፍቅር ተግባራዊ ሲሆን ቸር ያደርጋል ። ስስታም ፣ ንፉግ ሰው አፍቃሪ አይደለም ። እነዚህ ሁሉ ቸሮች ክፉ ቀንን ያለፍንባቸው ፣ ጨለማችን ላይ ብርሃን ያወጁ ናቸው ። ያለ ደጎች ድጋፍ እዚህ አልደረስንም ። ተቀብለን እንዳልተቀበለ መካድ አይገባንም ። እነዚያን ቸሮች ማመስገን ፣ ዛሬ ተራው የእኛ ከሆነ በችግራቸው መርዳት ይገባናል ።

ቸሮች የእግዚአብሔርን ጠባይ የተካፈሉ ናቸው ። እግዚአብሔርን የሚመስሉ ፣ የሚንሰፈሰፉልን ፣ በረከትን በተርታ የሚያቀርቡልን ፣ ልባቸውም እጃቸውም የተከፈተልን ስጦታዎቻችን ናቸው ። እግዚአብሔርን የምናየው በቸሮች ውስጥ ነው ። ሰው ቅባትና የውበት ዕቃ ሲሸምት ይውላል ፤ እውነተኛ ውበት ግን ቸርነት ነው ። እግዚአብሔር በባሕርይው ቸር ነው ። ቸርነቱን በቃላት መግለጥ ፣ በእውቀት ማስረዳት አይቻልም ። የእግዚአብሔር ቸርነት ከሞት መንጋጋ ያስመልጣል ። ይህን ቸርነት ያልተካፈለ ሰው ፣ እንስሳና እጽዋት የለም ። ቸር አንድ ቀን ከሰዎች ብልጠት የተነሣ ቢስ ይሆናል ። “ቸር ሲያጠቁት ቢስ ይሆናል” እንዲሉ ። እግዚአብሔር ግን እያጠቃነው አሁንም ቸር ነው ።

ነቢዩ በመዝሙሩ፡- “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው” ይላል ። እግዚአብሔርን ወደ ቤታችን መጋበዝ ፣ እግዚአብሔርን ተሸክሞ ወደ ሰዎች ቤት መሄድ ተገቢ ነው ። መቅመስ ማጣጣም ፣ ለመብላት መዘጋጀት ፣ መሞከር ፣ መለማመድ ነው ። የእግዚአብሔርን ቸርነት መቅመስ አለብን ። ቸርነቱን የሚቀምሱ ቸር ይሆናሉ ። ቀጥሎ፡- “በእርሱ የሚታመን ምስጉን ነው” አለ ። ቸር የማንሆነው ቢጎድልብኝ ብለን ነው ። ቸርነት ግን በእግዚአብሔር በመታመን የሚገኝ ነው ። ስጡ ላለው ቃል ታዝዤ አይጎድልብኝም ብሎ ማመን ይፈልጋል ። እምነት ልምምድ ነው ። መቅመስ ፣ ማየት ይገባል ። የቸርነት ሕይወት ደስ ያሰኛል ። የተቆለፉ ትልልቅ ቤቶች ፣ ምግብ እየተበላሸ የሚደፋባቸው የባለጠጋ ሳሎኖች ይህን ቸርነት ቢለማመዱ የሞት ጥላ ይገፈፍላቸዋል ። እንዴ በየምሽት በሚሊየን እያወጡ ይጋብዙ የለም ወይ? ቢባል እርሱ ንግድና ጉራ እንጂ ቸርነት አይደለም ። ቸርነት የባለጠጎች ዕዳ ሳይሆን ሁሉም የሰው ልጅ የሚለማመደው ሀብት ነው ። በእጃችን ማጉረስ ባንችል በእጃችን የቆሸሸውን ምስኪን ማጠብ እንችላለን ። የሰውነት ክፍሎቻችን የቸርነት መሣሪያ ናቸው ። ቸርነቱን የምንቀምሰው በጸሎት ነው ። የሚለምኑ ይቀበላሉ ፣ ቸርነቱንም ያያሉ ።

እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠን ሕይወትን ነው ። የሕይወት ዋጋዋ ስንት ነው ? ያኖረን ቸርነቱ ነው ። እስትንፋሳችን በአፍንጫችን ላይ የተንጠለጠለች ፣ ለመሄድ የተዘጋጀች ናት ። እስትንፋሳችንን በአፍንጫችን ያሳደረልን ፣ ያዋለልን ጌታ ቸር ነው ። ይህን ቸርነቱን ማጣጣም ፣ ማመስገን ፣ መመስከር ይገባል ። በእግዚአብሔር የሚታመን ሰው ቸር ነው ።

እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም