የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ችሎታ አይደለም

“ክፉ መናገርና ቂጣ መጋገር አያቅትም።”

“ጮኻ የማታውቅ ወፍ የጮኸች ዕለት ፣ ዕለቁ ዕለቁ ትላለች” ይባላል ። አንደበትን ዘወትር በልኩ መጠቀም ቃላትን ለመምረጥ ፣ አሳብን ለመግለጥ ፣ ፍሰትን ለመጠበቅ ፣ ጣዕምን ለማምጣት ፣ ጆሮን ለማስከፈት ፣ ልብን ለመማረክ ፣ መልካምን ነገር ለማወጅ ይጠቅማል ። ዝም ብለው ተቀምጠው ድንገት የሚናገሩ ሰዎች የድምፃቸው ነጎድጓድ ጆሮን ይገርፋል ። ከማስረዳት መቆጣት ፣ ከማስረጽ እልህ ውስጥ መክተት ፣ ከመማረክ መገፍተር ይቀናቸዋል ። የተናገሩት መልካም ቢሆን እንኳ ያወጡበት ድምፀት ፣ የተናገሩበት ቃና ፣ የመጠኑት ድምፅ መልእክታቸውን ይገድለዋል ። ሰዎች ቃላችንን ብቻ ሳይሆን ድምፃችንን ይለኩታል ። በድምፃችን ውስጥ ያለው ልኬት ቍጣን ፣ ትዕቢትን ፣ ልግመኛነትን ፣ በእሺታ ውስጥ ያለውን እንቢታ ይናገራል ። እንዲሁም የድምፃችን ልኬት ትሑት ልባችንን ፣ የፍቅር ቅላፄአችንን ፣ የመታዘዝ ጉልበታችንን ያሳያል ። ሰዎች ቀጥሎ የሚያዩት ተግባራችንን ነው ። ተግባር የልብ ወደብ ነው ። ተግባር ሰዎች እኛን የሚለኩበት የመጨረሻው ሚዛን ነው ። እግዚአብሔር ከምኞታችን እስከ ተግባራችን ያለውን ያያል ። በልቡ የተመኘ አመነዘረ ያለው ጌታ የልባችንን ንጹሕነት ፣ የምኞታችንን ቅድስና ፣ የምንጩን ጥራት እንደሚፈልግ ያሳያል ። ሰው በምኞትም መቀደስ የተፈቀደለት በመሆኑ ደካማ ነኝ ብሎ መቀመጥ የለበትም ። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሊፈጸም የማይችል ትእዛዝ አልሰጠውምና ። እግዚአብሔር የልባችንን አሳብ ያደምጣል ፣ በመጨረሻ ተግባራችንን ይፈልገዋል ። የመጨረሻ ቀን ጥያቄ ስለ በጎ አድራጎት ድርጅት የነበረን እቅድ የሚጠየቅበት ሳይሆን ብራብ አብልታችሁኛል የሚል መጠይቅ ያለበት ነው ። ሰዎችም የልባችንን ማወቅ ባይችሉም ፣ ልብ በተግባር ይጎላልና በተግባራችን ልባችንን ያዩታል ። ድምፅ ፣ ቃል ፣ ተግባር ተናባቢ ናቸው ።

የንግግር ችሎታ ተፈጥሮ ሳይሆን ልምምድ ነው ። አፍ የፈታነው የሚያለማምዱን ሰዎች ስለነበሩ ነው ። እነርሱ ቋንቋን ሲያሳውቁን ከአደጋ የሚጠብቁ የጥንቃቄ እውቀቶችንም አስጨብጠውናል ። ምግቡን ብቻ ሳይሆን የቀረበበትን ሰሐን ማየት ግዳችን ነው ። እንዲሁም ቋንቋ ፣ የንግግር ጥበብ አሳብን የምናቀርብበት ገበታ ወይም ሰደቃ ነው ። በየዕለቱ በልኩ መናገር ፣ ተገቢና ገንቢ አሳቦችን መሰንዘር አስፈላጊ ነው ። አንደበት ለመናገር ተፈጥሮአልና ካልተናገሩበት ተፈጥሮ ባክኗል ማለት ነው ። ጨዋነት ዝምታ ሳይሆን የሚናገሩትንና የሚናገሩበትን ቦታ ማወቅ ነው ። ከንግግር የሚሻል ዝምታ እንዳለ ሁሉ ከዝምታ የሚሻልም ንግግር አለ ። ሁሉም በቦታው ሲሆን ዝምታም ጌጥ ፣ ንግግርም ወርቅ ይሆናል ።

ንግግር ዘር ነው ። የተዘራ ነገር መብቀሉና መታጨዱ አይቀርም ። አንደበት የፍርድ ምክንያት ነው ። ሰዎች ፍርድ ቤት ሲከስሱን ሰድቦኛል ፣ ዝቶብኛል ፣ ክብሬንና ማንነቴን አዋርዷል ብለው ነው ። ክፉ አንደበት ያስከስሳል ። ነቢዩ ለአፌ ጠባቂ አኑር ብሎ መጸለዩ ተገቢ ነው ። ንጉሥ ሳለ ሁሉን ገዝቷል ፣ አንደበቱ ግን አልገዛ እያለው ተቸግሯል ። በአንደበቱ ላይ የበላይ የሆነ ሌሎች ኃጢአቶች አያሸንፉትም ። አንደበት ኃጢአት የሚወጣበት ብቻ ሳይሆን የሚገባበትም ነው ። የፈረድነው ፣ የሳቅንበት ነገር መልሶ ፈተናችን የሚሆነው አንደበት የኃጢአት መግቢያ ስለሆነም ነው ። ። በአንደበቱ መልካም የዘራ መልካም ፍሬ ያጭዳል ። መልካም መናገር አሳብን ማላቅ ፣ ቃላትን መምረጥ ፣ ስፍራውን መለየት ፣ ቆራጥና ትሑት መሆን ይፈልጋል ። ክፉ መናገር ግን ማፍረስ በመሆኑ ሙያ አይጠይቅም ። አንድ ቤት ሲሠራ ብዙ ሊቃውንቶች ይተባበሩበታል ። ንድፉ ፣ ግንባታው ፣ ውበቱ በተለያዩ የመስኩ ባለሙያዎች ይጠናል ። ሲፈርስ ግን ባለሙያዎች አያስፈልጉትም ። በብዙ ሺህ የመዶሻ ምቶች የተሠራው ቤት በአንድ የቦምብ ፍንዳታ ይፈርሳል ።

ሴትዬዋ ራሱዋን ለማሞገስ “ተናድጄ ጮክ ብዬ ከተናገርሁ በኋላ ውስጤ ባዶ ነው” አለች ። ሰባኪውም ሲመልስላት፡- “ጥይትም ከተተኮሰ በኋላ ቀለሃው ባዶ ነው ፣ ነገር ግን ሰው ገድሏል” አላት ይባላል ። እኛ ተናግረን አርፈን ይሆናል ፣ በእኛ ንግግር ግን ሰዎች እንቅልፍ ያጣሉ ። እኛ ተናግረን ይቅር ብለን ይሆናል ፣ ሰዎቹ ግን ለቀጣይ ጊዜያት ውስጣቸው በቂም ተመርዟል ። ክፉ መናገር እውቀት ፣ ቂጣ መጋገር ችሎታ አይጠይቅም ።

ቆጥበን መናገር ፣ ቆጥበን መጣላት አልቻልንም ። የምንናገረው እስከ መጨረሻው ፣ የምንጣላውም ለእርቅ እንዲያስቸግር አድርገን ነው ። የተሰማንን ሁሉ እንዳንናገር ሕሊና የሚባል ማንጠሪያ አለ ። ብስጭታችንን ሁሉ እንዳናፈስሰው ልቡና የሚባል መርሕ ተሰጥቶናል ። ለሚያልፍ ስሜታችን የማያልፍ ንግግር መናገር ተገቢ አይደለም ። ትላንት የነበረው እንደተለወጠ የዛሬውም ይለወጣል ። ዓለም በተለዋዋጭ ሕግ ውስጥ ናት ። ለስሜታችን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ይገባናል ። ምንም ነገር ከመናገራችን በፊት “ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ ቢሆን ምን ይናገር ነበረ” ብለን ማሰብ ይገባናል ። ራሳችንን ወክለን አንኖርምና የምንናገረው ነገር የክርስቶስ እንደራሴነታችንን የጠበቀ ሊሆን ይገባዋል ።

ትችትን መሰንዘር ፣ ሰውዬው ለዓመታት የደከመበትን ነገር በአንዲት ቃል ለመጣል መነሣሣት ፣ ማድነቅን አለመልመድ ፣ ሁሉንም ነገር በጥቁር መነጽር ማየት ፣ ጨለምተኛነት ፣ ስለ ሰው ሁሉ የምንናገረው ክፉ አለማጣት ይህ እውቀት አይደለም ። ከዚያ ይልቅ ያ ሰው እኔ ብሆን የማልሠራውን በመሥራቱ ፣ ይህን ያህል ጊዜ ለዚያ ነገር በመድከሙ ፣ ያልሠራውን ሳይሆን የሠራውን አትኩሮ በማየት ማድነቅ ይገባናል ። በጉዞው አንድ ደረጃ እየወጣ ከሆነ ስናደንቀው ሦስት ደረጃ በአንድ ጊዜ ይወጣል ። ትላንት ክፉ ይናገሩ የነበሩ ዛሬ ተጸጽተዋል ። እኛም ለነገ ጸጸት እንዳናኖር ጠንቃቃ መሆን ይገባናል ። ደጉን ምክራችንን ያልሰሙ ሰዎች ክፉ ንግግራችንን ግን ሊሰሙት ይችላሉና ክፋትና አረም በሚለማበት በዚህች ምድር ለአፌ ጠባቂ አኑር ብለን መጸለይ ያሻናል ። “ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው ፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል ፤” ተብሏል ። 1ጴጥ. 3 ፡ 10 ።

ልዑል አምላክ ሆይ ፣ በደግ ቃል እየባረክህ ባርከን !

የብርሃን ጠብታ 19
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 28ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ