ቤተጳውሎስ፤ እሁድ ሚያዚያ 21 2004 ዓ.ም.
አታመንታ ቀኝ ግራ
በሞተልህ ልትኮራ
ክርስቶስን ልትጠራ
አትደንግጥ አትሸበር
ተወልደሀልና ከማይጠፋ ዘር
ምንድር ነው መርበትበት
ጭንቀትና ሥጋት?
አይከፈል አቅልህ ፅና በክንዶቹ
ልብህ አይናወጥ ታይተሃል በአይኖቹ
በመንፈስ ተቃጥለህ በትክክል ጥራው
ምስጋና አምልኮ ለርሱ ብቻ ስጠው
ማንም አይችልህም ተዋጊህ እርሱ ነው
የሌጌዎን ጭፍራ ሞገዱን አትፍራ
ለእርሱ በመኖርህ መቶ እጥፍ እንጂ የለውም ኪሣራ
ከፍ አድርገው ስሙን ጮኽህ ተናገረው
ያለ የነበረ የሚኖር ሕያው ነው
አትፍራ አትደንግጥ ሩጥ በብዙ ትምክህት
አይቀርቡም ወዳንተ የአጋንንት ሠራዊት
ከብረት ጋሻ ይልቅ ይመክታል ስሙ
ተግተህ ተዋጋ እንጂ አታስብ ለድሉ
በክብር መሞቱ ሞገስ ነው አትፍራ
ነብስ የሚቀጣውን እርሱን ብቻ ፍራ
ተጓደድ በስሙ አትታወክ በርታ
የቆምክባት ዓለት ነውና አለኝታ
አትፈር አትፍራ ኢየሱስ ነው ጌታ