አንቀጸ ብፁዓን የተባለው ትምህርት ከተራራው ስብከት የመጀመሪያውን ክፍል ይዞ የሚገኝ ፣ ጌታችን ስለ ስምንት ብጽዕናዎች የተናገረበት ፣ ከማቴዎስ 5፡3-16 ያለው ክፍል ነው ፡፡ ጌታችን ይህንን ትምህርት ያስተማረው በተራራ ላይ ነው ፡፡ የትምህርቱ ጠባይም ስለ ከፍታ ሕይወት የሚናገር ነው ፡፡ እግዚአብሔር ያሰበልን የከፍታ ሕይወት የመሆን ሕይወት ነው ፡፡ ይህም የንብረት የበላይነት ሳይሆን የሕይወት ለውጥ ነው ፡፡ ይህም አዲስ ነገር ሳይሆን ሰው አስቀድሞ ሲፈጠር በእግዚአብሔር የታሰበለት የኑሮ መልክ ነው ፡፡ የተራራው ስብከት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ አስፈላጊ ነው ፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን አስቀምጠው ጊዜና ገንዘባቸውን ለእግዚአብሔር ስለሚሰጡ ፣ ከመሆን ይልቅ ይሆንልኛል በሚል ተስፋ ስለ ተሞሉ ፣ በፍሬ ከመታወቅ ይልቅ በጸጋ ለመታወቅ ስለሚሽቀዳደሙ ትምህርቱ ትኩስ ርእስ ነው ፡፡ ብዙ ሰው የራሱን ኃጢአት ሳይሆን የሌላውን ኃጢአት እየተናዘዘ ፣ ተነሣሂ ከመሆን ሐሜተኛ ወደ መሆን ስላደገ ፤ በእግዚአብሔር ምሕረት ከሚጽናና በጎረቤቱ ስህተት የሚጽናና ስለበዛ ትምህርቱ የጊዜው ደወል ነው ፡፡ ሰው ፣ ሰውነት ሲጠፋው የሚያስታውሰው እግዚአብሔር ብቻ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የሚያስፈልገን መንፈሳዊ ሁኖ ለመኖር ብቻ ሳይሆን ሰው ሁኖም ለመገለጥ ነው ፡፡ ዛሬ ምከሩኝ ብንልም በእውነት የሚመክር ካጣን ትምህርቱ አስፈላጊያችን ነው ፡፡ በስምንተኛ ሺህ መግቢያ ላይ በ1499 ዓ.ም ነሐሴ 7 ቀን ያረፉት ዐፄ ናዖድ ተናገሩ የተባለውን እናስታውስ፡-
“…በእንዲህ ያለ ጊዜ አይቼም አላውቅ
ሲገናኙ መውደድ ሲለዩ ቦጨቅ
በእንዲህ ያለ ጊዜ ምግባር በሌለበት
ታላቁ ታናሹን ሰውን በበላበት
በስምንተኛው ሺህ ጉድ ነው መሰንበት
አዛባ መዛቅ ነው እሾህ ያለበት
በስምንተኛው ሺህ ባለው ተንካ ተንካ
እባክህ ወንድሜ እከከኝም ቢልህ ራሱን አትንካ
የነቢያት ትንቢት ተፈጸመ ለካ፡፡”
አዎ በዛሬው ዘመን እከከኝ ብሎ ፈቃድ ቢሰጠንም ማንንም ሰው ለማከክ ፈቃደኛ አይደለንም ፡፡ እኛም በሌሎች ለመገሰጽ አቅማችን አናሳ ሁኗል ፡፡ ስለዚህ የብፁዓን ትምህርት ቅያሜ የሌለውን ምክር ይሰጠናል ፡፡ በርግጥም በእግዚአብሔር የተማሩ ሰላማቸው ይበዛል ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር መፍትሔውን አስቀድሞ ፣ ችግሩን ይገልጣል ፡፡ ነገን እያየልን ዛሬ ላይ ያበረታናል ፡፡ ሰዎች ሲገስጹን በራሳችን ያለንን ተስፋ እንጥላለን ፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ አልተረዱንም ፡፡ ስለዚህ በመቀጠል አይረዱንም /አያግዙንም/፡፡ እግዚአብሔር ግን ስሜታችንን የሚረዳና በኃይሉ የሚረዳን አምላክ ነው ፡፡
ብፁዕ ማለት የተባረከ ፣ ምስጉን ፣ የሕይወት ምስክርነት ያለው ማለት ነው፡፡ በጌታ ብፁዕ መባል ከሁሉም በላይ የሚያስደስት ነው ፡፡ ሰው እንኳ ሲያመሰግነን ደስ ይለናል ፡፡ ደስታችንም ኃይልን ይጨምርልናል ፡፡ ውዳሴ ከንቱንና ማመስገንን ብዙ ጊዜ አንለይም ፡፡ ውዳሴ ከንቱ አመስጋኙ አስብቶ ለማረድ የሚናገረው ሙገሳ ወይም የሚፈልገውን ለማግኘት ምስጋናውን እንደ እንደ ሥራ መጠየቂያ ወረቀት ሲያየው ነው ፡፡ ተቀባዩም ሲፈልገውና እንዲህ ብለህ አመስግነኝ ብሎ ሲጋብዝ እርሱ ውዳሴ ከንቱ ነው ፡፡ የሰውን መልካምነት ማጉላትና ያንንም ማመስገን የእግዚአብሔር ልጆች ጠባይ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ትንሹን መልካምነታችንን አብዝቶ ፣ ብዙውን ኃጢአታችንን አሳንሶ ያየዋል /ኢዮ. 11፡6/ ፡፡ ተራራ ለማፍረስ የተመደበው የሰናፍጭ ቅንጣት እምነት ፣ የነቢይን ዋጋ ለመውሰድም አንዲት ጽዋ ውኃ ነው /ማቴ. 17፡20፤ 10፡42/ ፡፡ እግዚአብሔር ግን መልካምነትን ያጎላል ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ጥቂት መልካምነታችን ብዙ ስህተታችንን ትሸፍናለች ፡፡ በሰው ፊት ደግሞ ጥቂት ስህተታችን ብዙ መልካምነታችንን ትሸፍናለች ፡፡ በሠርክ ለገባው ሠራተኛ የሙሉ ቀን ዋጋ ይከፍላል /ማቴ.20፡1-16/፡፡ ፈያታዊ ዘየማንን ከአብርሃም ቀድሞ ገነት እንዲገባ ያደርጋል ፡፡ ለእግዚአብሔር የማድረግን ያህል ያደረግንበትን መናዘዝም ክብር አለው፡፡ እግዚአብሔር የጌዴዎንን ጥቂት መልካምነት ሲያገንን እናነባለን /መሳ. 6፡11-12/ ፡፡
አንድ ልጅ የሌለውን አብራምን የብዙዎች አባት ብሎ የሚጠራ እግዚአብሔር ብቻ ነው ፡፡ ሸምበቆ የነበረውን ስምዖንን ጴጥሮስ ብሎ የሚጠራ እግዚአብሔር ብቻ ነው ፡፡ አብርሃምን አበ ብዙኃን ፣ ዳዊትን ልበ አምላክ ፣ ጴጥሮስን ዓለት ሲል እየሸነገለ አይደለም ፡፡ ከዛሬው ትንሽነት የነገውን ትልቅነት ስለሚያይ ነው ፡፡ እኛ ሰው ምንም መልካም ቢሆን የሚታየን ጥቂት ክፋቱ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ግን የእኔ ብሎ ሰውን ሲጠራ አያፍርበትም ፡፡ ኃጢአተኛውንም በምሕረቱ ሲያጸድቅ ከልካይ የለበትም ፡፡ እግዚአብሔር ነገን ያያል ፡፡ ስለ ልጆቹም መልካም መናገር ያስደስተዋል ፡፡ ሕዝቡ በበደል እያለ እንኳ ቃል ኪዳኑን የማይረሳ አምላክ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች ነን ካልን ስለ ሰዎች መልካምነት መናገር ፣ ጥቂቱን መልካምነት ማጉላት ይገባናል ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በፈጠረ ቀን “እጅግ መልካም እንደሆነ አየ” ይላል ፡፡ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ተባብረን ሰው እጅግ መልካም ነው ስንል እንደ ቃሉ ለመኖር አቅም እናገኛለን /ዘፍ. 1፡31/፡፡
ሰው ድብልቅ ነው ፡፡ ሰርገኛ ጤፍ እንደምንለው ነጭ ብቻ ወይም ጥቁር ብቻም አይደለም ፡፡ መንፈሳውያን እንደ መሆናችን መልካምነቱን ብቻ እያየን መልካም ነው ማለት አለብን ፡፡ ከአባታችን ተምረን የሰውን መልካምነት የምናጎላ መሆን ያስፈልገናል ፡፡ ያለንን ጥቂት መልካምነት ሌሎችን ለመክሰስ መጠቀማችን አሳዛኝ ምርጫችን ነው ፡፡ የማንሰርቅ ከሆነ ሌባውን እንጸየፋለን ፣ የማናመነዝር ከሆነ አመንዝራውን እንሳደባለን ፡፡ ነገር ግን ውሸታም ፣ ሐሜተኞች ልንሆን እንችላለን ፡፡ በአንዱ የሳተ በሁሉ የሳተ መሆኑን ማስተዋል አለብን /ያዕ. 2፡10/ ፡፡ በርትተን ከሆነ ያበረታን እግዚአብሔር ነውና ለእርሱ ክብርን ልንሰጥ ይገባናል ፡፡ እኛን ያበረታም እነርሱን እንደሚያበረታ ልናምንና ልንጸልይም ይገባናል ፡፡ የምናመልከው አምላካችን እኛን በሰው ፊት ጎበዝ ለማለት ይቸኩላል ፡፡ እርሱ በናይን የመበለቷ ልጅ ሞቶ ባገኘው ጊዜ “አንተ ጎበዝ እልሃለሁ ተነሥ” ያለ ነው ፡፡ ሬሳን በስም እንኳ የሚጠራ የለም ፡፡ ጌታችን ግን አንተ ጎበዝ አለው /ሉቃ. 7፡14/፡፡ ሬሳን አንተ ጎበዝ የሚል ጌታ ብቻ ነው፡፡ አንተ ጎበዝ ስንልም ብዙ ሬሳዎች ይነሣሉ ፡፡ አምላካችን የገዛ ቅዱስ መንፈሱ አግዞን በሠራናት ጥቂት መልካም ነገር ፣ መልካሞች ሊለን ይፈልጋል ፡፡ ምን ዓይነት አምላክ ነው !
ርቀን ሳንሄድ የሐዋርያውን ቃል እናስታውስና “ከእኔ የሆነ ምንም ነገር የለም” ብለን ምስጋና እንጀምር ፡- “ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና” /ፊልጵ. 2፡13/፡፡
የብፅዕና ዓመት ሁንልን !
ይቀጥላል