አዛኝቱ ማርያም ሆይ ! የልደቱንና የጠቢባንን ስግደት አሁንም እንመረምራለን ። የጥንት ጠቢባን የተወለደውን ክርስቶስ ይፈልጋሉ ። የዛሬ ጠቢባን ሀልወተ እግዚአብሔርን ይክዳሉ ። የጥንት ጠቢባን ዓለምን የናቁ መናንያን ናቸው ። የዛሬ ጠቢባን በበሽተኞችና በዓለም ድሆች የሚነግዱ ናቸው ። የጥንት ጠቢባን ዝቅ ብለው የድሀውን ኑሮ ያያሉ ። የዛሬ ጠቢባን ከነገሥታት ጋር ግብር ይበላሉ ። ልጅሽ ያልተጠበቁ እረኞችን በልደቱ ጋበዘ ። ባልተጠበቀ ስፍራም በበረት ተወለደ ። ለልደቱ ሮምን ፣ አንጾኪያን ፣ ቍስጥንጥንያን ፣ አቴናን ሳይሆን ታናሽዋን ቤተ ልሔምን መረጠ ። ዓለሙ የራሱ ገንዘቡ ሳለ ትንሽ ማደሪያ አጣ ። እኛ ፣ የእኛ ያልሆነውን ዓለም ስናጣ እንደነቃለን ። ልጅሽ ግን በገዛ ዓለሙ ስደተኛ ሲሆን አልተከፋም ። ሰብአ ሰገል በዋሻ የተወለደውን ሕፃን ለማግኘት ዝቅ ብለው ገቡ ። ዋሻ በግድ ዝቅ ያደርጋልና ። የተወለደው ሕፃን የሚገኘው ዝቅ ሲሉ ነው ። የዋኆች እንጂ እንደ ሄሮድስ ያሉ ተንኮለኞች አያዩትም ። እርሱን የሚፈልጉት መላ ያጡ ብቻ ሳይሆኑ የባለጠጋ ድሆችም ይፈልጉታል ። ጥንት ሰማይን ለማየት ቀና ማለት ግድ ነበረ ፣ አሁን ግን ሰማይ በቤተ ልሔም ተወልዷልና ዝቅ ማለት አስፈለገ ። ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰው ፍኖተ ሃይማኖት ትሕትና ነው ። እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ፣ እኔን ሊያድን ክርስቶስ ሰው ሁኗል የሚል ትሕትና ያስፈልጋል ። ትሕትና ከፍቅርና ከእምነት ጋር የተቀመመ ሰማያዊ መዓዛ ነው ።
አዛኝቱ ሆይ ! ድንግልናን ከእናትነት ጋር ያስተባበርሽ አንቺ ብቻ ነሽ ። ድንግል ከሆኑ እናት ፣ እናት ከሆኑ ድንግል መባል የለምና ። ዛሬ የልጅሽ ልደት በወርቃማ መንበር ፣ በጌጠኛ መቅደስ ፣ በሐር መነሳንስ ፣ በመለከት ድምፅ ፣ በታላቅ ነጋሪት ይከበራል ። እርሱ ግን በበረት ተወልዷል ። ከበረት ያልተናነሰ ኑሮ የሚገፉትን እንድናይ ይህን አደረገ ። እኛ ግን ልደቱን በልደቱ ዓላማ ለማክበር ገና አልበሰልንም ። ቤተ ልሔም ማለት የእንጀራ ቤት ማለት ነው ። የስምዋን ትርጓሜ ዛሬ አገኘች ። ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስ ተወልዶባታልና ። የአብ ልጅ ፣ የማርያም ልጅ ተባለ ። ሁለት ልደትን አስተባበረ ። ለእኛም ዳግም ልደትን ሰጠን ። ቤተ ልሔም የወልድ ትልቅ አስተርእዮ/መገለጥ እንጂ መነሻ አይደለችም ። ልጅሽን ከመንበሩ እስከ ቤተ ልሔም የሚያስሱ አሁንም ወደ መንበሩ ይሄዳሉ ። ከቤተ ልሔም የሚነሡ ግን አምላክነቱን የታላቅነቱን አድማስ መረዳት ይቸገራሉ ። ፀሐይ ያለ ብርሃን እንደማትገኝ አብም ያለ ወልድ አልነበረም ። ድንቅ ልጅ ዛሬ ተወለደ ። በዓለም ላይ ከአባቱ ጋር የዘመን እኩያ የሆነ ልጅ የለም ። አባቱ ያልቀደመው ልጅ ፣ እናቱን የፈጠረ ልጅ ዛሬ ተወለደ ። እስከ ዛሬ ልጅ እናቱን ይመስላል ይባል ነበረ ፣ ልጅዋን የመሰለች እናት ዛሬ ታየች ። ሃሌ ሉያ!
አዛኝቱ ሆይ ! ልጅሽ ኢየሱስ የተወለደበት ከተማ ይታወቃል ። የተወለደው ግን ቤት ቍጥር በሌለው አነስተኛ ስፍራ ነው ። የሮማው ወኪል ሲመዘግበው የቤት ቍጥር የለውም ብሎ መዝግቦታል ። በዚህም የቤት ቍጥር እንኳ የለኝም የሚሉትን ልባቸውን ጠገነ ። ያለ ቤት ተወልዶ ፣ ያለ ቤት ኖረ ። ለመቃብሩ ግን ጥሩ ቤት አገኘ ። ሦስት ቀን ኖሮበት እንቢ ብሎ ወጣ ። ወትሮም ድህነት ተስማምቶታልና ። በበረት መከራ የጀመረውን የሥጋዌ ጉዞ መስቀል ላይ ደመደመው ። ከበረት እስከ መስቀል ክርስቶስ በዓለም ላይ ያገኘው ነጻ ስፍራ ነው ። በረትና ቀራንዮ ማዶ ለማዶ ሁነው ያወራሉ ። ኢየሱስን የሚወድዱ ክርስቶስን የሚሰብኩ በወርቃማ አትሮኖንስ ካልሰበክን ብለው ያለቅሳሉ ። የእውነተኛው ክርስቶስ ምልክቱ መስቀል ነው ፣ መገፋት ነው።
አዛኝቱ ሆይ ! ሄሮድስ ሊገድለው ፈልጎ እንድሰግድለት ቦታውን ጠቁሙኝ አለ ። ቃሉ ስለ ስግደት ፣ ልቡ ስለ መግደል ያወራል ። ላያቸው ትሑታን ፣ ውስጣቸው ነጣቂ የሆኑ የሄሮድስን ክፉ አሟሟት ይቀምሳሉ ። ካህናቱም የሰብአ ሰገልን መምጣት በሰሙ ጊዜ ለሄሮድስ ትንቢቱን ጠቅሰው ወደ መቅደሱ ተመለሱ ። እኛን አልፎ አሕዛብን ለልደቱ አይጠራቸውም ብለው አስበው ነበርና ። እግዚአብሔርን በኢየሩሳሌም ያሰሩት መስሎ ይሰማቸው ነበር ። ትልቁ የሰው ስህተት የአጽናፈ ዓለሙን ንጉሥ ፣ የአጥቢያው ብቻ ጌታ ሊያደርገው መፈለጉ ነው ። ለሕዝብ ሁሉ ወይም ለዓለም ሁሉ የምሥራች ሊሆን ተወለደ (ሉቃ. 2 ፡ 10) ። ለዓለሙ ተወለደ ፣ ለዓለሙ ሞተ ። ከሰማይ ወደ ምድር የወረደው እስራኤልን ብቻ ሳይሆን ዓለምን አፍቅሮ ነው (ዮሐ. 3 ፡ 16) ። በእስራኤል በኩል መጣ እንጂ ለእስራኤል ብቻ አልመጣም ።
አዛኝቱ ማርያም ሆይ ! በልጅሽ መከራ አዝነሻል ። ኀዘንሽም ትንቢት ተነግሮለታል (ሉቃ. 2 ፡ 35) ። ዛሬም የሰው ልጅ በዋጋ ተፈጥሮና ድኖ ያለ ዋጋ እየጠፋ ነውና የተቀደሰ ኀዘንሽ ፣ የፈሰሰ ዕንባሽ መማጸኛ ይሁነን ! አሜን ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም.