የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አፈ ማር ክርስቶስ

የክርስቶስ ትምህርት ከመምህራን ትምህርት ሁሉ ይበልጣል ፡፡ እርሱ ልጄ እያለ ፣ ፀጉርን እየዳበሰ ፣ ውርስን እያዘጋጀ እንደሚያስተምር አባት ነው ፡፡ እርሱ ምን አለህ ? ሳይሆን እኔ አለሁልህ እያለ የሚያስተምር ርእሰ መምህራን ነው ፡፡ መምህራን ለጆሮ ሲናገሩ እርሱ ግን ለልብ የሚናገር ነው ፡፡ ደግሞም የልብ አውቃ ነው ፡፡ በመርማሪ ቃሉ መርምሮን ፣ በፈዋሹ ቃሉ የሚያክመን ነው ፡፡ መምህራን ስለ ችግር ይናገሩ ይሆናል ፤ እርሱ ግን ስለ መፍትሔው ይናገራል ፡፡ እርሱ በጥፋታችን ዝም የማይል የሚቆጭልን መምህር ነው ፡፡ በወደቅን ጊዜም ምሳር የማያበዛብን የማይተቸኝ አጽናኝ አስተማሪ ነው ፡፡ እርሱ ብቻ እያንዳንዱን ቀን ሁለተኛ ዕድል አድርጎ የሚሰጠን በእኛ ተስፋ የማይቆርጥ መምህር ነው ፡፡ እኛ ራሳችንን በጠላነው ሰዓት እንኳ የሚወደን ክርስቶስ ብቻ ነው ፡፡ መምህራን ሁሉ በጠባብ ክፍል ያስተምራሉ ፡፡ እርሱ ግን ትልቁን ዓለም የማስተማሪያ ክፍሉ አድርጎ ያስተምራል ፡፡ ባሕርን ቀለም ፣ እጽዋትን ብዕር ፣ ሰማይን ሰሌዳ ፣ ምድርን የመማሪያ ክፍል አድርጎ የሚያስተምር ሊቅ እርሱ ነው ፡፡
እርሱ የሚያስተምረን ሊቃውንት እንድንሆን ፣ ሊቃውንት ተብለን ለመጠራትና ለመጣላት አይደለም ፡፡ ልጆቹ ወዳጆቹ እንድንሆን ያስተምረናል ፡፡ መምህራን ሁሉ እውቀትን ይሰጣሉ ፡፡ እርሱ ግን በሥጋም በነፍስም ይመግበናል ፡፡ መምህራን ሁሉ ከትምህርት ቤት ውጭ አናገኛቸውም ፡፡ እርሱ ግን በሕይወት እርምጃ ውስጥ ሳይለየን ያስተምረናል ፡፡ መምህራን ሁሉ ትምህርታቸውን ጨርሰው ያስመርቁናል ፤ እርሱ ግን እስክንሞት ያስተምረናል ፡፡ መምህራን ሁሉ ድሆች ናቸው ፤ ክርስቶስ ግን ባለጠጋ መምህር ነው ፡፡ መምህራን ሁሉ በመደበኛ ሰዓትና በታወቀ ሥርዓት የሚያስተምሩ ናቸው ፤ ክርስቶስ ግን በጊዜውም ያለ ጊዜውም የሚያስተምረን ነው ፡፡ መምህራን ሁሉ ኃይለኛ ሲሆኑ ያርቃሉ ፣ ለዘብተኛ ሲሆኑ ያሰንፋሉ ፡፡ እርሱ ግን ፍቅርና ፍርድ የተስማሙለት ነው ፡፡ መምህራን ሁሉ የተወሰነ ዕድል ይሰጣሉ እንጂ ሁልጊዜ የሚወድቀውን አይቀበሉም ፤ ክርስቶስ ግን የውዳቂዎች ሰብሳቢ ነው ፡፡ አዎ እርሱ ርእሰ መምህራን ነው ፡፡
መምህራን እውቀትን ያስተምራሉ ፡፡ ክርስቶስ ግን ራሱ ጥበብ ነው ፡፡ መምህራን ሁሉ ባስተማሩ ቁጥር እውቀታቸው ያድጋል ፡፡ ክርስቶስ ግን እውቀቱ ፍጹም ነውና መጉደልና መጨመር የለበትም ፡፡ መምህራን ስለ ነገ ቢናገሩ ነቢይ ተብለው ይፈራሉ ፣ እርሱ ግን ነገን በማወቁ የነገ ድፍረታችን ነው ፡፡ መምህራን ስሜታቸውን ተማሪዎቻቸው አያውቁላቸውም ፣ እኛም ክርስቶስ ምን ያህል እንደሚያስብልን አናውቅም ፡፡ ተማሪነት ትልቁን ልጅ ያደርገዋል ፣ ሽማግሌው ተማሪ ሲሆን መረበሽ መጮህ ያምረዋል ፡፡ እኛም እንደ ልጆች ስንሆን የሚችለን ክርስቶስ ብቻ ነው ፡፡ የመምህራን ትምህርት በአሸዋ ላይ እንደ ተጻፈ ቶሎ ይጠፋል ፣ የክርስቶስ ትምህርት ግን በዓለት ላይ እንደ ተቀረጸ ዘመናትን ይሻገራል ፡፡ በረዶና ዝናብ የማያጠፋው የዓለቱ ጽሑፍም “ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው” የሚለው አዋጅ ነው ፡፡
መምህራን በተማሪው ደረጃ ዝቅ ብለው ያስተምራሉ ፡፡ ክርስቶስም ካለንበት ድረስ መጥቶ በሹክሹክታ ያስተምረናል ፡፡ ወደ እኛ ካልመጣ እኛ ወደ እርሱ መሄድ እንደማንችል እያወቀ ሁልጊዜ ይመጣል ፡፡ መምህራን ሳይታዘቡ ያስተምራሉ ፤ እርሱም ባለማወቃችንና በስህተታችን ይራራልናል ፡፡ መምህራን አጢፊውንና ጎበዙን በአደባባይ ይሸልማሉ ፡፡ ክርስቶስም የፍርድ አምላክ ነው ፡፡ መምህራን ቆላ ወርደው ፣ ደጋ ወጥተው ያስተምራሉ ፤ ክርስቶስም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ በእግሩ ዞሮ ያስተማረ ነው ፡፡ ካለንበት ድረስም በመጽሐፍ የተናገረን ነው ፡፡ እስከ ምጽአት ድረስ ያለው ዘመኑ የመምህርነትና የምሕረት ነው ፡፡ በዕለተ ምጽአት ግን ፍርድ ይሰጣል ፡፡ አባቱ እርሱን ስሙት ያለው አፈ ማር ክርስቶስ ነው ፡፡ ቃሎቹ የሚያጽናኑ የአብ አንድያ ልጅን እርሱን ስሙት ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ