የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ /16/


በጸሎት ተሳሰቡ
“እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ፣ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” /ያዕ. 5፡16/፡፡
ኑዛዜ በገዛ አንደበት ኃጢአትን ማመን ማለት ነው፡፡ ኑዛዜ የትልቅ ትሕትና መገለጫ ነው፡፡ እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ብሎ ኃጢአቱን ሲናዘዝ እግዚአብሔር ትሕትናውን አይቶ ከሚፈትነው ከኃጢአት ኃይል ያድነዋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለትሑታን ጸጋን ያለብሳልና /1ዮጥ. 5፡5/፡፡ ኑዛዜ ላለፈው ኃጢአት ስርየት፣ ለሚመጣው ንጹሕ ልቡና የምንቀበልበት መንገድ ነው /ምሳ. 28፡13/፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ይቅር ለማለት በደሉን ከማመን የበለጠ ምክንያት አልፈለገበትም፡፡ ይቅርታንም የሚሰጠው በኑዛዜው ብቻ አይደለም፡፡ ስለ ኃጢአታችን በተከፈለው በክርስቶስ ደም አማካይነትም ነው፡፡ “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል” ይላልና /1ዮሐ. 1፡7/፡፡ የክርስቶስ ደም የሚያነጻው አንዳንዱን ኃጢአት አይደለም፡፡ ከኃጢአት ሁሉ ይላል፡፡ ስለዚህ የእኔ ኃጢአት ይቅርታ የለውም ብሎ ማሰብ ከክርስትና አስተሳሰብ ውጭ ነው፡፡ ኃጢአትን ከክርስቶስ ደም በላይ ማየት ደሙን ማቃለል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚፈታተን ኃጢአት ሊኖር አይችልም፡፡ መፍራት ያለብን ለንስሐ መዘግየትን እንጂ የእኔ ኃጢአት ንስሐ የለውም ብለን አይደለም፡፡ አባቶች እንደ ነገሩን የእኛ ኃጢአት ማለት የቤት ጥራጊን ወስዶ ውቅያኖስ ላይ እንደ መጨመር ነው፡፡ በቤት ጥራጊው ውቅያኖስ አይቆሽሽም፡፡ ምሕረቱ ብዙ ደግሞም ለዘላለም ነው፡፡ የእነ ዳዊት መውደቅ የተጻፈልን ለኃጢአት ሳይሆን ለንስሐ እንድንደፍር ነው፡፡
እርስ በርስ የመናዘዝ ዓላማ የጸሎት ርእስ ለመለዋወጥ ነው፡፡ አንዱ ስለ አንዱ በመጸለዩ የራሱን ልብ ከስህተትና ከመፍረድ ይጠብቃል፡፡ ወገኑንም ያተርፋል፡፡ የጻድቅ ሰው ጸሎት ይላል፡፡ የአዲስ ኪዳን ጽድቅ የሰውን ኃጢአት መሸፈን ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ጽድቅ መግለጥ ሲሆን የአዲሱ ግን መሸፈን ነው፡፡ ይህ ሰው ቢጸልይ ሌላውን የማትረፍ አቅም አለው፡፡
ጸልዩልኝ ማለት ትልቅ ብልሃት ነው፡፡ ጳውሎስም ብዙ ጊዜ የሌሎችን የጸሎት ድጋፍ ፈልጓል /ኤፌ. 6፡19/፡፡ ስለ ሌሎች መጸለይም ግዴታ ነው፡፡ ስለሌሎች አለመጸለይ በደል ነው /1ሳሙ.12፡23/፡፡ የምንሰማው እያንዳንዱ ክፍተት የወሬ ሳይሆን የጸሎት ርእስ ነው፡፡ እርስ በርሳችን ግልጽ ልንሆን ይገባል፡፡ ይበልጥ ለእውነተኛ አገልጋዮች ግልጽ መሆን መፍትሔውን ሊያፋጥን ይችላል፡፡ መፍትሔው ያለውም በጋራ በመጸለይ ነው፡፡ ኑዛዜ ደግሞም ጸሎት የክርስትና ትልቅ አቅም ናቸው፡፡ እርስ በርሳችን እንድንተሳሰብ እግዚአብሔር ይርዳን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ