የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ /2ኛ/

ተከባበሩ “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” /ሮሜ. 12፡10/ 
የሁለት አገር አምባሳደሮች ምንም ቢቀራረቡ በመጀመሪያ ክቡር አምባሳደር ተባብለው ክብርን ይለዋወጣሉ። ሁለቱም የሚኖሩት ራሳቸውን ወክለው ሳይሆን መንግሥታቸውን ወክለው ነውና መከባበር ግዳቸው ነው። ለራሱ የሚኖር አምባሳደር የለም። እኛም የክርስቶስ አምባሳደሮች ነን። ከእኛ መካከል እንኳን ለራሱ የሚኖር ለራሱ የሚሞት የለም። ስለዚህ ልንከባበር ግድ ይላል። አንድን ሰው ማክበር እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያለውን ዓላማ ማክበር ነው። ስንፈጠር እንድንሰጥ ብቻ ሳይሆን እንድንቀበልም ሆነን ተፈጥረናል። ለዚህም መናገሪያ አንደበት ብቻ ሳይሆን መስሚያ ጆሮም ተሰጥቶናል። ዛሬ በእጁ የሚቸር ባለጠጋ ትላንት ከእናቱ ጡት የሚለምን ሕጻን ነበረ። አንዱ ባንዱ ውስጥ ያለውን ውድ ነገር ለማግኘት መከባበር ግድ ነው። ማክበር ክቡር ብቻ ሳይሆን አዋቂም ያደርገናል። ሁልጊዜ መናገር ሞኝነት ነው። ሁልጊዜ መናገር ከምናውቀው ውጭ እንዳናውቅ ያደርገናል። ሊቅ ለመሆን መንገዱ ሁሉን ሳይንቁ መስማት ነው። ሰው ሁሉ የራሱን ክብር ይፈልጋል። እንደ ራሱ የሚወደውንም ያከብራል። እውነተኛ ፍቅር ክብር አለው። የፍቅር ዕድሜም የሚረዝመው በመከባበር ነው። እግዚአብሔር አክባሪ ነው። በመልኩ በምሳሌው ሲፈጥረንም ስላከበረን ነው። በደሙ ዋጋ ሲገዛንም ምን ያህል እንዳከበረን እንረዳለን። ሰውን ማክበር በሰው ላይ ያለውን የእግዚአብሔር መልክ እንዲሁም ዓላማውን ማክበር ነው። ክብር ባለበት እውነተኛ ምሪት አለ። ክብር በሌለበት በግድ መገዛት አለ። መሪ የሚኖረን ክብር ሲኖረን ነው። ክብር በሌለበት አለቃ ይኖራል። መሪ ሠርቶ የሚያሠራ፣ ከፊት ቀድሞ የሚያስከትል ነው። አለቃ ደግሞ እየገረፈ የሚነዳ ነው። ወደፊት የሚሄድ ሕዝብ መሪ ያለው ነው፣ ወደኋላ የሚመለስ አለቃ ያለው ነው። መሪን እኛ እንሾማለን፣ አለቃን ክፋታችን ይሾምብናል። ቁመት የሚለካካ ሕዝብ፣ ቅባትን የሚንቅ ወገን መሪን እየገደለ አለቃን ይጎትታል። “አህያ ተማልላ ጅብ አወረደች” እንዲሉ። 



የክፉ ዘመን አንዱ መገለጫ ክብር ሲርቅ ነው። የአገር፣ የቤተ ክርስቲያን፣ የሃይማኖት፣ የአባቶች ክብር ሲርቅ ዘመኑን አክፍተነዋል ማለት ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ የክብር መገለጫ ሊሆን ይገባዋል። እኛ እርስ በርሳችን ስንከባበር ዓለሙ ያከብረናል። ክርስቲያን ከማያምኑ ጋር ሆኖ ወንድሙን ካማ የሚከተለን እናጣለን። ስብከታችን የሳበውን ወገን መናናቃችን እንዳያርቀው መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አንዱ የክብር መገኛ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢሯን መጠበቋ ነው። መንግሥት እንደ መንግሥት የሚቀጥለው ምሥጢር ሲኖረው ነው። ምሥጢር የሌለው መንግሥት ዕድሜ የለውም። መንፈሳውያን መሪዎችም የመንግሥቱ ምሥጢር ጠባቂ ሊሆኑ ይገባል። መከባበር መደማመጥን ያስገኛል። ተዋረድ ያለውን ምሪት ያመጣል። ሁሉም በሚናገርበት መደማመጥ፣ ሁሉም በሚያዝበት ሥራ የለም። እናት ክብሯ ያለው አባትን አክብራ ስታስከብር ነው። አባቶችም እርስ በርስ ሲከባበሩ ምእመናን ማክበርን ይለማመዳሉ። የዘመናዊነት ግልጽነት እብድ ያደረጋቸውን ባለጌዎች እንዳናይ መድኃኒቱ ሁሉም በድርሻውና በመጠኑ መቀመጡ ነው። ገና ንስሐቸውን ያልጨረሱ ምእመናን አገልጋዮችን ተቺ የሚያደርጋቸው ይህን ክብር ስላልተለማመዱ ነው። መከባበር ማለት መፈራራትና መጠባበቅ ማለት አይደለም። ሌላውን እንደ ራስ የማየት ፍቅር ነው። የምንወደው ሰው ከእኛ የተሻለ አስተሳሰብ እንዳለው ስናስብ አምነን እንለቀዋለን። የበለጠ እንደሚሠራም ተማምነን እንለቅለታለን። ራሱን ችሎ እንዲቆም እናደፋፍረዋለን። ልክ የሌለው መከባበር መፈራራት እንዳይሆን ክብር የሌለው ፍቅርም መታገል እንዳያመጣ እንደ ቃሉ መከባበር ይገባናል። የክብር መንፈስ ከእኛ ጋር ይሁን!

 እርስ በርሳችሁ
 (4ኛ) የሌላው ናችሁ በዲ/ን አሸናፊ መኮንን “እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን” (ሮሜ. 12፡5) አካል አንድ ሲሆን ብዙ ክፍሎች ወይም ብልቶች አሉት። ብልቶቹ በአካሉ ላይ የተገጠሙ ናቸው። ልዩነታቸው አካልን አይከፍልም። አንድ አካል ይባላሉ። ብልቶችን አንድ የሚያደርጋቸው ሌላው አንድ ራስ አንድ ዕዝ መኖሩ ነው። አንድ አካል የቤተ ክርስቲያን ፣ አንድ ራስ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። የተለያዩ ብልቶች አንድ አካል የተባሉት በአካሉ ላይ ስለተገጠሙ ነው፣ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ያሉ ከተለያየ ኑሮና ወገን የተጠሩ የአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን አባል ናቸውና አንድ ናቸው። ብልቶች በአካል አንድ የሚሆኑት ለራሳቸው ስለማይኖሩ ነው። የአንድነት መሠረትም ለራስ አለመኖር ነው። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የምናገኛቸው ወገኖች በየትኛውም የኑሮ መስመር የማናገኛቸው ነበሩ። ለዚህ ነው ከቤተ ክርስቲያን ሲቀሩ በመንገድ እንኳ አናያቸውም። ያገናኘን ክርስቶስ ነው። ብልቶችን አንድ የሚያደርግ ራስ ነው። የአካሏ ራስም ክርስቶስ ነው። ብልቶች ያለመዛነፍ ተግባራቸውን የሚያከናውኑት ለአንድ ራስ ስለሚገዙ ነው። ለአንድ ራስ አለመገዛት አደጋ ያመጣል። እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን አንድ የሚያደርገን ትልቁ ነገር ለጌታ መገዛታችን ነው። ከጋራ አመለካከቶችና ውሳኔዎች በላይ ለክርስቶስ ደስታ መኖር አንድ ያደርጋል። የሚለያየን የገዛ ምኞታችን ነውና። እኔ ለራሴ አልኖርም ማለት ትልቁ የመሥዋዕትነት ሕግ ነው። ትልቁ የፍቅርም መገኛ ነው። በአካል ዓለም እጅ፣ እጅ የሆነው ለራሱ አይደለም። እጅ ጫማን የሚያነሣው ለእግር እንጂ ለራሱ አይደለም። ሌላውን አካል ሲያለብስ ለራሱ ግን ብዙ ጊዜ አይለብስም። ዓይንም ራሷን የምትከላከለው ከስንት ጊዜ አንዴ ነው። ያለ ማቋረጥ የምታየው ግን ለሌላው ብልት ነው። በአካል ዓለም አንዱ ላንዱ ይኖራል። እኛም አካል ነንና አንዳችን ለአንዳችን መኖር ይገባናል። እኛ ለማንጠቀምበት ወገናችን ግን ለሚጠቀምበት ነገር ከልብ መሮጥ አለብን። እኔ የራሴ አይደለሁም፣ እኔ የወገኔ አገልጋይ ነኝ የሚል አሳብ ይግዛን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ