አትናደዱ
“…ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ” (1ጢሞ. 6፡3,4)።
ክርስትናው ትምህርቱም ሆነ አርአያነቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተሠርቷል። እርሱ የመጨረሻው አስተርእዮ ወይም መገለጥ ሆኖ መጥቷል። ለዘመናት በመናገር ራሱን የገለጠው እግዚአብሔር ሰው በመሆን እንደ ተናገረው አልተናገረንም። ስለዚህ ክርስትና ክርስቶስን ቤዛ በማድረግ በሞት ላይ መፎከር ነው። ክርስትና ክርስቶስን አርአያ በማድረግ በቅድስና መኖር ነው። የክርስቶስን ትምህርት አስተውሎ ለሌሎች ማወጅ ነው። ሰው የራሱን ቤዛ ማዘጋጀት ቢችል ኖሮ ክርስቶስ ቤዛ ኩሉ ዓለም ሆኖ መምጣት ባላስፈለገው ነበር። አገልጋዮቹን አርአያ ማድረግ ቢገባውም ፍጹም አርአያ ክርስቶስ ነው። ክርስትና ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት ነው። ክርስቶስን መቼም በሙሉነት ስለማንመስለው ክርስትና የማያቋርጥ ዕድገት ነው። በተለየ ቃል ልንገልጥ እንችላለን እንጂ ስለ ክርስቶስ ከሐዋርያት የተለየ መገለጥ ይዘን ልንመጣ አንችልም። ስለዚህ ክርስትና በተጻፈው ላይ ደርቦ መጻፍ፣ በእግር ፈለጉ ላይ ደርቦ መርገጥ ነው።
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ መድኃኒት አለ ብሎ ማስተማር ልዩ ወንጌል ነው(ገላ. 1፡6-9፤1ጢሞ. 6፡3)። ሞቱን ከንቱ ማድረግ ነው። ይህም ርግማንን ያስከትላል። ይህ ብቻ አይደለም ክርስትና እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ነው። ቡድንተኝነት አይደለም። ለእግዚአብሔር ቀንቻለሁ ብሎ መሳደብም አይደለም። በኑሮአችን እርሱን ማክበር ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና በኃጢአት አይከብርም። የእግዚአብሔር ቃል የተሰጠን እንድንጽናናበት እንጂ እንድንሳደብበት አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል ለራስ አሳብ ማስፈጸሚያ ማድረግ አይገባም። “ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል” እንደሚል በሃይማኖት ስም የስድብ አምሮትን መወጣት አይገባም። ያልጨረሱትን ዓለም በቤተ ክርስቲያን ለመጨረስ የሚፈልጉ አሉ። ኃጢአት ግን ካልወሰኑ አያልቅም። በቃሉ መናቆር ቅንዓትን ክርክርን ስድብን ክፉ አሳብን እርስ በርስ መናደድን ይወልዳል።
ዛሬ አብዛኛው ሕዝብ የተጣደበት ነገር ትላንት ይፎካከሩ የነበሩ ባልንጀሮችን ስድድብ ነው። ግለሰቦችን ብሔራዊ ጉዳይ አድርገን እኛም በማናውቀው እንተራመሳለን። ስለ ራሳችን ብዙ ያልገባን ነገር እያለ ስለ ሰው በድፍረት አስተያየት እንሰጣለን። ራስን የመዘንጋት ዘመን ነው።ሰው ራሱን ከዘነጋ ለንስሐ አይበቃም። በሌሎች ኃጢአት ውስጥ መደበቅ አይቻልም። በክርስቶስ ደም ውስጥ ብቻ እንደበቃለን።
ጤናማ ትምህርት አለመያዝ የተበላሸ ሕይወትን ይወልዳል። በትክክል ያልሰማ በትክክል አይታዘዝምና። የሕይወት ብልሽትም ቃሉን ለሙግት ይጠቀማል። ይህም ቅንዓትንና እርስ በርስ መናደድን ይወልዳል። ንዴትም ስድብን እየወለደ ይመጣል። መፍትሔው ከመጀመሪያው መጀመር፣ መሠረትን በቃሉ ላይ መመሥረት ነው። እግዚአብሔር የማስተዋል ዘመንን ያምጣልን!