አታጉረምርሙ
“ወንድሞች ሆይ እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ” (ያዕ. 5፡9)።
ማጉረምረም የልብና የአንደበት ድምፅ ነው። ማጉረምረም በሌላው ላይ ክስና ፍርድ፣ ትችትና አለመርካትን ማስተጋባት ነው። ማጉረምረም በጠላት ላይ ሳይሆን በወዳጅ ላይ አለመደሰትን መግለጫ ነው። ማጉረምረም አልማዙ እንዳለቀ ቴፕ መነፋነፍ ነው። ጣዕምን ያሳጣል። የእኔ ነገር እያሉ በራሳቸውና በዕድላቸው የሚያጉረመርሙ ሰዎች አሉ። የእኛ ዕድል ፈንታ ግን እግዚአብሔር ነው። ዕድላችን እርሱ ከሆነ ዕድላችን መልካም ነው። ድርሻችንም እርሱ ከሆነ ዋጋችን የላቀ ነው(መዝ. 15፡5)።
ማጉረምረም አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ ያሰሙት ድምፅ ነው። አዳም ራሱን ነጻ ለማድረግ በሔዋን፣ ሔዋንም በእባብ አሳበቡ። ትዳርን የሚንጠው ለእኔ አለማደግና አለመደሰት ምክንያቱ እገሌ ነው የሚለው ድምዳሜ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በትዳር ውስጥ እርሷ ነች እርሱ ማለት የማይቆም ሆኗል። እርሷ ነች እርሱ በማለት ግን ማዕበሉ ሊቆም አይችልም። እኔ ነኝ በማለት ግን ጸጋን መቀበል ይቻላል። ማጉረምረም እየባሰ ሲመጣ በተፈጥሮ በአየር ንብረቱ ሳይቀር መከፋት ይጀምራል። በወጣው ፀሐይ፣ በዘነበው ዝናብ ከመደነቅ ብሶተኛ መሆን ይጀምራል። ሁሉም ነገር ሕይወት ያለውና የሌለው እርሱን ለማጥቃት ያደመ ይመስለዋል።
በሙሴና በአሮን ላይ እስራኤል ያንጎራጉሩ እንደ ነበር በአገልጋዮችም የሚያጉረመርሙ አሉ። ሌሎች ስላጎደሉት ስናስብ እኛስ ምን ፈጽመናል? ብሎ ማሰብ ይገባል።
ውሻ በፍቅር ውሎ አጥንት ሲይዝ በሚወደው ላይ ሳይቀር እንደሚያጉረመርም ማጉረምረም የረሀብ ሳይሆን ያለመርካት ችግር ነው። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች አቅርቦትን ሊያፋጥኑ ይችላሉ፣ማርካት ግን አይችሉም። እርስ በርስ ማጉረምረም አንዱ በአንዱ እንዲፈርድ፣ እንከን እንዲያወጣ፣ አሳልፎ እንዲሰጥ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ፍርድን ያመጣል። እግዚአብሔር ስለ ሌላው እንድንጸልይ እንጂ እንድንፈርድ ፈቃዱ አይደለም። እኛ ማን ነንና? በሌላው ስህተት ውስጥ መደበቅ ከፍርድ አያድንም። ከፍርድ የሚያድነው በክርስቶስ ደም ውስጥ መደበቅ ነው። የሌሎችን እንኳን በደላቸውን መልካምነታቸው አትኩረን ማየት አይገባም።
እንከንን ከመፈለግ መልካሙን እያጎላን እንድንመራረቅ እግዚአብሔር ይርዳን!