የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እሾሁን ሳይሆን ጽጌረዳውን

 
“እግዚአብሔር ፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና ።” ዕብ. 6፡10
በዮዲት ጉዲት አርባ ዓመት የወደመውን የክርስትና ቅርስ ፣ የታረዱትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደምናስታውስ ሁሉ በአባ ፍሬምናጦስ የተቋቋመውን የኢትዮጵያ የስብከተ ወንጌል አዝመራም ማሰብ ይገባናል ። በግራኝ መሐመድ አሥራ አምስት ዓመት የተደረገውን ጨካኝ ወረራ እንደምናስብ ሁሉ በጎንደር ዘመነ መንግሥትም የተጻፉትን መጻሕፍት ማሰብ አለብን ። በግብጻውያን የመንበር ጥገኛ ሁነን የማቀቅንበትን ጊዜ እንደምናስብ ሁሉ በተሰዓቱ ቅዱሳን ከፍጻሜ የደረሰውን የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ፣ የተሰበከውን ወንጌል ማሰብ አለብን ። በአድዋ ጦርነት የሞቱትን ብቻ ሳይሆን የተገኘውን ፍሬ ፣ በማይጨው ጦርነት የከዱትን ብቻ ሳይሆን ታምነው የቆሙትን ማሰብ አለብን ። ማሰብ የብዙ ነገሮች መነሻ ነው ። የፍቅርም የጠብም ፣ የሰርግም የጦርነትም መነሻ ማሰብ ነው ። ታሪክን ወደኋላ መልሰን ማስተካከል ባንችልም ታሪክን እንማርበታለን ። ታሪክ በክፋቱም በደግነቱን አስተማሪ ነው ። የታሪክ ትርፉም ትምህርቱ እንጂ ያ ጊዜ አሁን የምንመልሰው መሆኑ አይደለም ። “ከታሪክ የማይማር ስህተትን ለመድገም የተፈረደበት ነው” የሚባለው ለዚህ ነው ።
በጎ የሠሩትን ማሰብ አለብን ። አለማሰብ ብዙ እየጎዳን ነው ። “የሞተን አትርሳ ፣ የወደቀን አንሣ” ይባላል ። የሞተን ማንሣት አንችልም ፣ የወደቀን ማውሳት ጥቅም የለውም ። የሞተን ማውሳት ፣ የወደቀን ማንሣት ግን በረከት አለው ። የሞተን አለመርሳት ትምህርቱ ለትውልድ ሰፊ ስለሆነ ነው ። መልካም ሥራም ከመቃብር በላይ እንደሚኖር የሚያስገነዝብ ነው ። እኔም ስሞት እንዲህ እታሰባለሁ ብሎ ሰውን ለመልካም ነገር የሚያነሣሣ ነው ። “የምትሄድበት እንዳይጠፋህ የመጣህበትን አትርሳ” ይባላል ። ድሆች ባለጠጋ ሲሆኑ መልሰው ድሆችን ያስለቅሳሉ ። ይህ የመጡበትን መርሳት ነው ። ስለ ሕዝብ ጭቆና አውርተው ሥልጣን ላይ የወጡ መልሰው ጨቋኝ  ይሆናሉ ። ይህ የመጡበትን መርሳት ነው ። የመጡበትን መርሳት የሚሄዱበትን ያስጠፋል ። ስለዚህ ደም መቃባት ፣ ሰውን ማስለቀስ ይጀመራል ። ፍጻሜውም ውርደትና መከራ ይሆናል ። መርሳት ከድሀ ጎጆ እስከ ንጉሥ እልፍኝ ዋጋ ያስከፍላል ። “ተው አትርሳ ፣ ተሠርቶልሃል የእሳት ገሳ” ይባላል ። ሊጠብቀን የሚችለውን እንቅፋት ማሰብ ለመጠንቀቅ ያግዛል ። ከዚያ ሁሉ በላይ በነፍስ እንደምንጠየቅ ማሰብ በዘመናችን ሁሉ በቅዱስ ፍርሃት እንድንንቀሳቀስ ያደርጋል ። “ያለህበትን ለማወቅ የመጣህበትን አትርሳ” የሚለውም ድንቅ ንግግር ነው ። እየበላን ፣ እየጠጣን ፣ እየሠራን የምናማርረው ትላንት ይህ ሁሉ እንዳልነበረን ስለምንረሳ ነው ። ዛሬ በእጃችን ብዙ ነገር ካለ ትላንት አልነበረም ማለት ነው ። ዛሬ በእጃችን ምንም ከሌለ ነገ ይኖረናል ማለት ነው ። “የወጣህበትን አትርሳ” ይባላል ። የወጡበትን መሰላል መገፍተር ተሰቅሎ መቅረት ነው ። የወጡበት መሰላል ለመውረድም ያስፈልጋል ።
ክፉ ፣ ክፉ ነገሮችን አልረሳ እያልን እንቸገራለን ። በሕይወታችንም የሠራናቸው ብዙ መልካም ነገሮችን ትተን ያጠፋናቸው ነገሮች ላይ እንተክዛለን ። መልካሙን ስናስብ እንደገና እንነቃቃለን ። በትላንት የታሪክ ስህተት ላይ መቆየት አመድ ላይ መንከባለል ነው ። ከመቆሸሽ ውጭ ምንም ጥቅም የለውም ። ታሪክ የሚመዘነው በተሠራበት ዘመን የእውቀት ልክ ነው ። ማንም ስለ ታሪክ ተጠያቂ መሆን የለበትም ። እኛ ትላንት ያልነበርን ፣ ነገ የማንኖር የዛሬ ሰዎች ነን ። ዛሬ ልንተወዉ ሲገባን ባልተውነው ፣ ልናደርገው ሲገባን ባላደረግነው ነገር እንጠየቃለን ። እግዚአብሔር አምላክ ግን ያለፈውን ዘመን መልካም ነገር የሚያስታውስ አምላክ ነው ። ስለ አብርሃም እንጂ በአብርሃም ዘመን ስለነበረው ዓመፀኛ ንጉሥ ዘመን ተሻግሮ አይናገርም ። ስለ ሙሴ እንጂ ስለ ፈርዖን ተናግሮ አያውቅም ። ስለ ዳዊት እንጂ ዳዊትን ስላስጨነቁት ሰዎች ከዘመናት በኋላ አልተናገረም ። ጴጥሮስና ጳውሎስን የገደለ ፣ ክርስቲያኖችን በጣም ያስጨነቀው ኔሮን ቄሣር ስሙ እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ የለም ። የእግዚአብሔር መዝገብ ዘመናትን ተሻግሮ የሚያነሣው መልካሞችን ነው ። ክፉዎችን ለማስተማሪያነት ቢያነሣ እንኳ ለወቀሳ ግን ጊዜው አልፏል ። በፍርድ ክልል ውስጥ ያለ አይወቀስም ። ፍርዱንም የጨረሰ አይከሰስም ።
በእናቱ ሞት ላይ “እናቴ ሀብታሟ” እያለ ልጅየው ያለቅሳል ። አንዱ ሰውም “የእናትህን ሀብታምነት የምናውቀው የተዝካሯ ዕለት ነው” አለው ይባላል ። ይህ የሲዳምኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ። እናቴ ሀብታሟ እያሉ ማልቀስ ቀላል ነው ። ሀብቷ ግን መታሰቢያዋን ካላጠፋ እውነተኛ ነው ። አገር እናት ናት ። አገሬ ሀብታሟ እያልን ማልቀስ ይቻላል ። የሀብታምነቷ ምልክት ግን በጎ የሠሩትን ስታስብ ነው ። ታሪክ ያላቸው ተቀብረውባት ፣ ልብ ወለድ ታሪክ ያጻፉ ከነገሡባት ሀብታምነቷ ምን ላይ ነው ? ሀብታም የሚባሉ አገሮች ሁሉ ያለፈውን ቅርስና ያለፉትን ባለውለታዎች ያስባሉ ። የባለጠጋ አገር ምልክቱ ለትላንት እውቅና ለዛሬ ፣ የመኖር ነጻነት ሲሰጥ ነው ። ትልቁና እውነተኛው ሀብት የሰዎችን ውለታ ፣ ያለፉትን ባለታሪኮች አለመርሳት ላይ ያረፈ ነው ። ቤተ ክርስቲያን የቅዱስነት መዐርግ መስጠት ስታበዛ የሃይማኖት ተጋዳዮች እየበዙ ይመጣሉ ። አገር የደከሙላትን ማሰብ ስትጀምር ላገር የሚደክሙ ብዙዎች ይበዛሉ ። “አገሬ ለሠራላት አትሆንም” የሚል እሳቤ በትውልድ ላይ ካረፈ ያው ትውልድ አገርን ያጠፋታል ።
ስለ እግዚአብሔር የተነገው ግን ከዚህ ልዩ ነው፡- “እግዚአብሔር ፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና ።”
የእግዚአብሔር ሰዎችን መቀበል እግዚአብሔርን መቀበል ነው ። አምባሳደሩን መቀበል መንግሥቱን መቀበል ነውና ። ስላገለገላችሁ ይልና ስለምታገለግሉአቸውም ይላል ። የቆመ መልካምነት ሳይሆን አሁንም እየቀጠለ ያለ መልካምነት ነው ። መልካምነት “ነበር” የሚል ቃል አይስማማውም ። መልካምነት እንደ እስትንፋስ የማይቆም ነገር ነው ። ለቅዱሳን መልካም ማድረግ ለእግዚአብሔር ስም ክብር መስጠት ነው ። ቅዱሱ ሲጣልና ሲረሳ የማያምነው ዓለም እግዚአብሔርን ማለት ምን ጥቅም አለው ? እያለ ይዘባበታል ። የእግዚአብሔር ስም እንዳይሰደብ የምናደርገው ክርስቲያኖች እንዳይወድቁ በመደገፍ ነው ። ለእግዚአብሔር ሰዎች መልካም ስናደርግ ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር እየገለጥን ነው ። እግዚአብሔርን የት አግኝተን እንጋብዘዋለን ? እርሱ ከአገልጋዮቹ ጋር አለ ። እግዚአብሔር የአንድ ብርጭቆ ውኃን ዋጋ የማይረሳ ታማኝ አምላክ ነው ።
ውለታን መርሳት ዓመፀኝነት ነው ። ዓመፀኛ ገልብጦ የሚሄድ ነው ። ውለታን የሚረሳም ከፊቱ ያለውን ገበታ የሚደፋ ነው ። ሌላውን የሚረሳ እርሱም ይረሳልና ። ታሪክን የሚያጠፋ ታሪኩ ይጠፋል ። ትውልድን የሚያጠፋ ልጆቹን ያጠፋል ። ድሆችን የሚያጠፋ ዘመዶቹን ያጠፋል ። ነገ የሚታወስ ሰው ፣ የትላንቶቹን የሚያስብ ሰው ነው ። ያስተማሩንን ፣ ያገለገሉንን ፣ ያጽናኑንን ፣ አንድ ቀንም “አይዞአችሁ” ያሉንን ፣ አንደበት ሁነው የተሟገቱልንን ፣ ክንድ ሁነው የመከቱልንን አንረሳ ። የምናመልከው አምላክ የማይረሳ ነውና ። ከሰው ምንም አልተቀበልኩም ማለት በዓለም ላይ ትልቅ ውሸት ነው ። ደምሳሽ ትውልድ እንዳንሆን መጠንቀቅ ያስፈልገናል ። የትላንቱን ክፉ ሳይሆን መልካሙን ማሰብ ይገባናል ። ቅዱሳንን ማሰብ ብቻ ሳይሆን መሆንም ያስፈልገናል ። የአንድ አገር ታላቅነት የሚለካው የወደቁላትን ስታከብር ነው ። ክብር የሌለው አገር አያድግም ።
የዓይናችን ብርሃን አንተው ነህ ። ያላንተ ዓይን ጌጥ ብቻ ነው ። የጆሮአችንም የምሥራች የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ አንተ ነህ ። ስለ ጽጌረዳ እሾህ ተናግረን አናውቅም ፣ ብዙ እሾሁን ረስተን አንዷን ጽጌረዳ እንወዳታለን ። የሰዎችን ብዙ ጥፋታቸውን ትተን አንድ መልካምነታቸውን እንድናጎላ እባክህ እርዳን ። ምጡን ረስተን ልጁን እንድናነሣ አግዘን ። ምጡን አልረሳ ብለን በምጡ የተወለዱትን እየረሳን ነውና ። መንፈሳዊ ዓይን ስጠን ። በፊትህ የጸለዩልንን ፣ በጎ ያደረጉልንን ፣ በክፉ ቀን ያልከፉብንን ባርክልን ። ይህ ቀንም ውለታ የማሰቢያና የማመስገኛ ቀን ይሁንልን ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 29
ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ