የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …? /2/

“ዕድሜዬንና ፍላጎቴን ስመዝነው ትዳር ብይዝ መልካም ነው ፤ ነገር ግን ስለ ትዳር የምሰማው ክፉ ታሪክ ወደ ኋላ ያዘገየኛል ። ትዳር ያልገቡ ልግባ ፣ ልግባ የሚሉበት የገቡ ልውጣ ልውጣ የሚሉበት ይመስለኛል ። ወደ ትዳር ከገባሁ በኋላ የትዳር ጓደኛዬ ጠባይ ቢለወጥስ ?” እያልህ ይሆን ? ትዳር ሁለት ደካሞች የሚመሠርቱት ጠንካራ ኅብረት ነው ። አንድ ምንጭ ከሰፈሩ አይርቅም ፣ ከሌላ ምንጭ ጋር ሲደባለቅ ግን ወንዝ ሁኖ አገር ያቋርጣል ። ፈትል ብቻውን ይበጠሳል ፣ ከሌላ ፈትል ጋር ሲያብር ግን አንበሳ ያስራል ።ልምጭ ብቻውን የሚጤስ ነው ፣ ከሌሎች ልምጮች ጋር ሲሆን ግን የሚነድ ችቦ ነው ። አንድ በትር በጎበዝ ሰው ይሰበራል ፣ የታሰረ ሁለት በትር ግን ጎበዝ አይሰብረውም ። ሁለት በሬዎች አንገታቸውን ዝቅ አድርገው ለመጠመድ ከፈቀዱ ማረስ ይችላሉ።
ይልቁንም በሁለት ከተገመደ በሦስት የተሸረበ ገመድ አይበጠስም ። ትዳርም እግዚአብሔር ፣ ወንድና ሴት አብረው ሲሸረቡበት የማይበጠስ ይሆናል ።በሁለት የተገመደ ይተረተራል ፣ አለቀ ሲባል ወደ መነሻው ይሄዳል ፤ በሦስት የተሸረበ ግን አይፈታም ። ሰዎች ደህና ቁርስ ስለበሉ ትዳር ገነት ነው ቢሉህ፣ በወጪ ምክንያት ተጨቃጭቀው ትዳር እስር ቤት ነው ቢሉህ አትመናቸው ። ስለ ትዳር የሚናገር መሥራቹ ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ትዳር ብዙ መልክ ያለው ቢሆንም የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ማመን አለብህ ። ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ምንም ክፉ ነገር የለም ።
በትዳራቸው ሰላም ያልነበራቸው ብዙ ታላላቅ ሰዎች በዓለም ላይ አልፈዋል ። ሶቅራጥስ ትዳሩ ጭቅጭቅ የነበረበት ሲሆን ፣ ነገር ግን እንደ ትምህርት ቤት ይወስደው ነበር ። የእንግሊዙ ጆን ዌስሊ ጭቅጭቁን በመፍራት ሲሰብክ ያመሽ ነበርና ሳያስበው እንግሊዝን በወንጌል አዳረሳት ። አብርሃም ሊንከን ግልፍተኛ ትዳር ነበረው ። ነገር ግን አሜሪካንን አንድ ከማድረግ አላገደውም። እንኳን ከሌላው ሰው ጋር ይቅርና ከራስህ ጋርም እየተጣላህ እንደምትኖር እወቅ ። እውነተኛ ሰላም የፍጭት ውጤት እንጂ የመጨፍለቅ ውጤት አይደለም ። የአንተን ድምፅ በሙሉነት የሚቀበል መቅረጸ ድምፅ ብቻ ነው ። ትዳር ያስፈለገህ የሚቃወምህን ለማግኘትም ነው ። የአንድን ነገር ምንነት ለማወቅ ሁለት ዓይን ብቻ አይረዳም ። ትዳር ሌላኛው ዓይን ነው ።
ለትዳር የሚያስፈልግህ ነገር የአካል ፣ የአእምሮና የአቅም ብቃት ነው ። ክፍተትህን የሚሞላልህ ሰው ብቻ ሳይሆን የእርሱን ክፍተት የምትሞላለት ሰው መፈለግ ያስፈልግሃል ። ትዳር መቀበል ሳይሆን መስጠት ፣ ሽርሽር ሳይሆን መሥዋዕትነት ነው ። ከትዳርህ በላይ ሀብትህን ፣ ከሚስትህም በላይ ልጆችን አትውደድ ። ትዳርን መዳረሻ አታድርገው ። ያለ ሀብትም ያለ ልጅም በፍቅር የሚቀጥል ተቋም ነው ። ትዳር የሕይወት ዘመን ቃል ኪዳን ነውና መውረጃ ፌርማታ አትፈልግ ። በሚስትህ ላይ የምታየው ጉድለት አንተ እንድትሸፍንላት እግዚአብሔር የሰጠህ አደራ ነው ። ክፉ ባሎች ደግ ሚስት ያገኛሉ በሚል ስሌት ትዳርህን የጭካኔ ቦታ አታድርገው ። የትዳር የበላይ ጠባቂ እግዚአብሔር እንደሆነ እወቅ ።
ትዳርህን በቃል ኪዳን ፣ ቤተሰቦችህን በማሳወቅ ፣ በእውቀትና በጸሎት ጀምረው ። ትዳር በእውነት ለሚገቡበት የራሱ የሆነ በረከት አለው ። ከትዳር በፊት ሁለት ዓይንን ገልጦ ማየት ፣ ከገቡ በኋላ አንዱን መጨፈን ግዴታ ነው። “ትዳርህን በዓይንህ ብቻ ሳይሆን በጆሮህም ምረጠው” የሚባለውን አትርሳ። ጤናማ ትዳርን የሚያመጣው እግዚአብሔርን መፍራት ፣ ምሥጢርን መጠበቅ ፣ መንፈሳዊ አማካሪዎችን መያዝና ይቅርታ እንደሆነ እወቅ ። የአንዱ ልምድ ላንዱ አይረዳምና በሰዎች ልምድ ቤትህን አትምራ። የእግዚአብሔር ቃል ግን ለሁሉ ብርሃንን የሚሰጥ ነው ።
እየፈራህ የምትጓዝ ከሆነ ሜዳው ሰፊ ቢሆንም መውደቅህ አይቀርም ። ወደ ትዳር ለመግባትም ቃለ እግዚአብሔር ፣ ጸሎትና እምነት ያስፈልግሃል ። ኑሮህን በጣፋጭነቱ ብቻ ሳይሆን በምሬቱም ተማርበት ። ከምቾት የሚገኘው እውቀት አናሳ ነው ። ፍቅርም እውነተኛነቱ የሚታወቀው ለበደል ይቅርታ ፣ ለችግር ጽናት ሲኖረው ነው ። በደልና ፈተና እስኪነሣ ሁሉም ፍቅር ይመስላል ።
ወደ እግዚአብሔር ቤት የምትመጣበት ዓላማም መልካም የትዳር ጓደኛ ለማግኘትና ይዞ ለመጥፋት አይሁን ። እግዚአብሔርን ያስወጣህበት ኑሮ የሚደመደመው በጥፋት ነው ። አንተ ዓይንህን ገልጠህ ተመልከት እንጂ ትዳር የሚያገናኙ አገልጋዮችን አትፈልግ ። አሳብ ይዘህ እንጂ ውሳኔን ይዘህ አገልጋዮችን አታማክር ። ያለ መስፈርት ውደድ እንጂ ወደ ኑሮ ከገባህ በኋላ አትኩረህ አትመልከት ። የሚያጣራ ዓይን ፣ የሚያበጥር ጆሮ ለትዳር ተገቢ አይደለም ። ቤትን የሚጠብቅ እምነት ነው ። ደግሞ አንተ አትክዳ እንጂ በሌሎች መከዳት ካሣው ከእግዚአብሔር ነው ። ሰዎች አንተ እግዚአብሔርን የበደልከውን ያህል አልበደሉህምና ይቅር በላቸው ። በመታገሥ ቤትህን ታተርፋለህ ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 7
ተጻፈ አዲስ አበባ
መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ