የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 8/ 2007 ዓ.ም.
ታላቅ የሚለው ቃል ለጆሮአችን በድምፅ፣ ለዓይናችን በማስታወቂያ የለመድነው ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ባለፉት ዘመናት ታላቅ ስብሰባ፣ ታላቅ ቅናሽ … የሚሉ የግነት ድምፆችን እንሰማ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ‹‹ታላቅ ጉባዔ›› ‹‹ታላቅ ኮንፈረንስ›› ‹‹ታላቅ የፈውስ ፕሮግራም›› የሚሉ ማስታወቂያዎችን በጆሮአችን እየጠገብን፣ በዓይናችን እያነበብን ነው፡፡ “ታላቅ ጉባዔ” የሚለውን ቃል ስናይ የጉባዔ ታናሽ እንደሌለው እንድናስብ ያደርገናል፡፡ በክርስቶስ ቅዱስ ስም የሚደረግ ጉባዔ ታላቅ ነው፡፡ የተጠራውን ያንን ጉባዔ ታላቅ ያደረገውን ምክንያት ቀጥሎ ሲዘረዝሩ መምህር እገሌ፣ ዘማሪ እገሌ … ይገኛሉ የሚል ማስታወቂያ እንሰማለን፣ እናነባለን፡፡ የጉባዔው ታላቅነት የተለካው በእግዚአብሔር መገኘት፣ በቃሉ ክቡርነት ሳይሆን በሰዎች በመሆኑ ያሳዝናል፡፡ ታላቅ የሚለው ቃል የግነት ሎሌ ነው፡፡ ግነት ደግሞ ውሸት አያጣውም፡፡ ታላቅ ብንለው ገና ያልገለጥነው እንኳን ከቃላችን ከአሳባችንም ከፍ ያለው እግዚአብሔር ነው፡፡
እግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎችን በታላላቅ ጉባዔዎች ሠርቶ አያውቅም፡፡ እርሱ ከአደባባይ ይልቅ በእልፍኝ፣ ከሁከት ይልቅ በፀጥታ ይገኛል፡፡ እስራኤል እስከ ዛሬ ተጠብቀው የሚኖሩት ከአንዱ ከአብርሃም ጋር እግዚአብሔር በገባላቸው ቃል ኪዳን ነው (ዘፍ. 12፡1-3)፡፡ ብሉይ ኪዳንም የተሰጠው በአንዱ በሙሴ በኩል ነው (ዘፀ. 19፡20፤24፡2)፡፡ እግዚአብሔር ብሔራዊ ጉዳይን ያማከረው ለካህናቱ ሳይሆን ለሦስት ዓመቱ ሕፃን ለሳሙኤል ነው(1ሳሙ. 3፡1-21)፡፡ ኢየሱስ ዓለምን ለማዳን በሥጋ እንግድነት ሲመጣ መላውን ዓለም ወክላ የተቀበለችው አንዲት ንጽሕት ቡርክት ድንግል ናት(ሉቃ. 1፡26-38)፡፡ በበረት ሲወለድም የተገለጸው ለእረኞች ሲሆን ትንሣኤውንም ለአንዲት ሴት ለመግደላዊት ማርያም ገልጿል(ሉቃ. 2፡8-20፤ ዮሐ. 20፡1-18)፡፡ እግዚአብሔር ጋ ተከበን መቅረብ፣ ከነምድራዊ ማዕረጋችንም መምጣት እንፈልጋለን፤ እርሱ ግን በሌጣነታችን ሊያናግረን፣ በልጅነትም ብቻ ሊያውቀን ይፈልጋል፡፡ አንድ ብቻዬን ነኝ ምን ማድረግ እችላለሁ? እንላለን፡፡ እግዚአብሔር ግን በአንዱ እልፍ ጠላት እንዳሳደደ አላነበብንምን? (ዘዳ. 32፡30)፡፡
የጽሑፉ ዓላማ ጉባዔን ለመንቀፍ አይደለም፡፡ ለአንድ አባት የመጨረሻ ደስታው ልጆቹ ተሰብስበውለት ማየት ነው፡፡ እግዚአብሔርም ተሰብስበን ሲያየን እጅግ ደስ ይለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚለውም ቃል ‹‹የአማንያን አንድነት›› ማለት ነው፡፡ አንድነታችን፣ የአንድነት ጸሎታችንም ለጠላታችን የሚያደቀው ክንድ፣ ለእኛም የምንሞላው ኃይል ነው፡፡ የጽሑፉ ዓላማ ከታላቅ ክንውኖች በኋላ ስለሚመጡ ታላላቅ ተግዳሮቶች መግለጽ ነው፡፡
ልባችን በደስታ ተነቃቅቶ የእግዚአብሔርንም ክብር በገሀድ ተመልክተን፣ የማይታጠፍ ተስፋውን በመሐላ ተቀብለን፣ የከፍታችንን ቅብዐት በናቁን ፊት ተቀብተን … ቀጥሎ ታላቅ በረከት፣ ታላቅ መዳን ይሆናል ስንል ታላቅ ማዕበል ገጥሞን ይሆን? ለደቀቁት የምደርስበት ዘመን መጣ፣ አሁን ታስቤአለሁ እኔም ለተቆጨሁላቸው ላስብ ጊዜው ደረሰ ስንል ታላቅ ስብራት፣ ጆሮንም ጭው የሚያደርግ ክፉ ዜና ገጥሞን ይሆን? የመጣው ደስታ ከመንፈስ ቅዱስ፣ ተስፋው ከሰማይ አምላክ አልነበረምን? ተቀብቶ መሰደድ፣ ተሻግረሃል ከሚል ድምፅ በኋላ እንደገና መዋጋት ትክክለኛ ሂደት ነውን? እያልን በመደናገር እንጠይቃለን፡፡ እግዚአብሔርም ዝም ይለናል፡፡ በዙሪያችን ያሉትን እንዳንጠይቅ ስንቀባ እልል ያሉ፣ የከፍታችንን ዝማሬ አብረውን እንዲዘመሩ ጠርተናቸው ስለነበር ይሉኝታ ይዞን ዝም እንላለን፡፡
እንኳን ለሰዎች ለራሳችን ልንነግረው፣ ለኅሊናችን ልናሳምነው የሚያቅተን ነገር ከታላቅ ተስፋ በኋላ ያለውን ታላቅ ማዕበል ነው፡፡ ማዕበሉ ከራሳችን፣ ከአካባቢያችን፣ ከሰይጣን ሊነሣ ይችላል፡፡ ማዕበሉ ካለፉት ዘመናት የሚከፋ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጨረስኩ ስንል መጀመር፣ ወደብ ላይ ደረስኩ ሲባል ገና ከባሕሩ እምብርት ላይ መሆን ልብን ያዝላል፡፡ ይህ ሁሉ ግን በጥበበ ሥላሴ ተቀምሯል፡፡
ተማሪ ክፍሉ ሲያድግ ፈተናው አይቀርም፡፡ እንደውም ፈተናው ከበድ እያለ ይመጣል፡፡ ፈተናው ግን ደረጃን የሚጨምር በመሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ከማዕበል የምንገላገለው ከሰማዩ ወደብ ስንደርስ ነው፡፡ ችግሩ ላይለወጥ ይችላል፣ እኛ ከተለወጥን ግን የችግሩ ኃይል በግማሽ ይቀንሳል፡፡ ከድንጋጤ፣ ከፍርሃት፣ እጅ ከመስጠት፣ ከመደነቅ ከተላቀቅንና ችግሩን በችግርነቱ ብቻ ማየት ከቻልን ይቀልልናል፡፡ እግዚአብሔር ግን የእፎይታ ጊዜ ይሰጣል፡፡ ሁልጊዜ እያለቀስን አንኖርም፡፡
መከራ ላሸካሚዎቹ አይከብዳቸውም፣ ለተሸካሚዎቹ ግን ይከብዳቸዋል፡፡ መከራ የሚያሸክሙን አንዳንድ ጊዜ ቻለው፣ ክርስትና ፈተና ነው ብለው ይነግሩናል፡፡ እነርሱ አሳምመውን እግዚአብሔር ይማርህ እያሉ ያላግጡብናል፡፡ ከማቊሰላቸው የአፋቸው ጥዝጣዜ ይጎዳናል፡፡ ዓለም ግን ጽዋ ነውና ለእኛ ያሸከሙትን አንድ ቀን ይሸከሙታል፡፡
አዎ ከታላቅ ተስፋ በኋላ የሚመጣ ታላቅ ማዕበል አለ፡፡ ትልልቅ የንግድ ተቋማት ተዘርግተው፣ ከፍተኛ ጨረታ አሸንፈው ወደ ቤታቸው በደስታ ሲገቡ ትዳራቸው የሚሰናበታቸውን ወገኖች አስበን እናውቅ ይሆን? ታላቅ ሥልጣንን ተቀብለው ለውዳቸው ክብራቸውን ለማሳየት ሲገሰግሱ የገዛ ባሎቻቸው ለሞት ስለከጀሏቸው ሚስቶችስ ምን እንላለን? ታላቅ የትምህርት ደረጃ ላይ ደርሰው እገሌ ነው ለዚህ ያበቃኝ ብለው ለምስጋና ሲመጡ መርዝ የተበጠበጠባቸው ሰዎችን ለማሰብ እንፈቅዳለን? ታላቅ የአገልግሎት በር ተከፍቶላቸው ለማገልገልና ብዙ ሠራዊትን ለማሰለፍ ሲሰናዱ የገዛ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ስለወጓቸው አገልጋዮች ምን ይሰማን ይሆን? ትልልቅ ፕሮጀክቶች ፀድቀው፣ ፈንዱ በበረከት ተለቅቆ ወደ ሥራ ሲራወጡ የገዛ ሠራተኞቻቸው ስለሚከሷቸው ባለራእዮች ምን እንላለን? የችግር ዘመናቸው አልፎ ለምስጋና ሲዘጋጁ ልጆቻቸው በሽተኛ ሆነው እቤት ስለቀሩባቸው ወገኖች ምን ብለን ይሆን?
ከትልልቅ ተስፋ በኋላ ትልቅ መከራ ይመጣል፡፡ እስከ አሁን የነበሩት እንቅፋቶች በርምጃ የምናልፋቸው ነበሩ፤ አሁን ግን በመዝለል የምናልፈው እንቅፋት ይመጣል፡፡ እስከ አሁን በዓላማ የሚዋጉን ባላጋሮች ነበሩ፣ አሁን ደግሞ ያለዓላማ የሚዋጉን የወዳጅ ጠላቶች ይመጣሉ፡፡ እስከ አሁን እንደሳትን በማሰብ የሚቃወሙን ጽንፈኞች ነበሩ፣ አሁን ግን ማዕዳችንን የበሉ በቅንዓት ተረከዛቸውን ያነሡብናል፡፡ ቆመን መሟገት አይገባንም፣ ለሁሉም መልስ መስጠትም አይቻልም፡፡ የታየንን ለመንካት መፍጠን አለብን፡፡ በእኛ የሆነው በሌሎች ሲሆን ያየነው፣ እኛ ጋ አይመጣም ብለን የናቅነው ነው፡፡ ትንሣኤያችን ከእግዚአብሔር ከሆነ ማንም አያጠፋንም፤ ያለ እግዚአብሔር ከተነሣን ግን እልፎች ደግፈውንም እንወድቃለን፡፡
ከታላቅ ተስፋ በኋላ የሚመጣው ማዕበል እንደ ክረምት አግቢ የበረከቱ ዘመን መቃረቡን የሚያስታውቅ እንጂ መጨረሻ አይደለም፡፡ በትልልቅ በዓላት ላይ ትልልቅ የእሳት አደጋ መኪናዎች በተጠንቀቅ ቆመው ይጠብቃሉ፡፡ ትልቁን ደስታ የሚያበላሸውን እሳት ለማጥፋት በዝግጅት ይቆማሉ፡፡ እኛ የደነገጥነው ስለ ደስታው እንጂ ስለ እሳቱ ስላላሰብን ነው፡፡ የሆነው ሲሆን የነበረ፣ የሚደረገው ከዚህ በፊት የተፈጸመ ነው፤ አዲስ ነገር የለም፣ እኛ የምናሟሸው ችግርም የለም፡፡ እየተጓዝን ያለነው የሚሊዮኖች የእግር ዱካ ባረፈበት በሕይወት መንገድ ላይ ነውና ብዙ ምስክሮችና መካሮች አሉን፡፡ ከእነዚያም አንዱ አብርሃም ነው፡፡
ከታላቅ ተስፋ በኋላ ታላቅ ቀቢፀ ተስፋ
በአብርሃም ሕይወት
እግዚአብሔር አብርሃምን ወደ መንግሥቱ የጠራው ዓለም ጡረታ በምታወጣበትና በማይፈለግበት በሰባ አምስት ዓመት ዕድሜ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ለምን አደረገ ስንል አብርሃም የሚመካበት ጉብዝና እስኪደክም፣ ተፈላጊነቱም እስኪያከትም ነው፡፡ እግዚአብሔር ከድካም ጋር ሊሠራ ይችላል፣ ከትምክሕት ጋር ግን አይሠራም፡፡ ስለዚህ አብርሃም አለኝ በሚለው ነገር ልቡ እስኪደክም ጠበቀው አለኝ የሚለውን ሲያጣ እግዚአብሔር አለኝታ ሆነለት፡፡ ሰው የጣለውን የሚያነሣ እግዚአብሔር ነው፡፡ ራሳችን ያልተቀበልነውን ማንነታችንን ተቀብሎ ለጥቅም የሚሠራው ከእኛ ይልቅ እኛን የሚፈልገን እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቤት እስከ ሞት ማገልገል እንጂ ጡረታ የለም፡፡ አብርሃም በሠርክ የተጠራ ቢሆንም የማታው መብራት እግዚአብሔር በማለዳ ከገቡት ጋር ዋጋውን እኩል አደረገለት፡፡ በመጨረሻ ሰዓት ተጠርቶ ትልቅ አባት አደረገው፡፡ ፈያታዊ ዘየማን በመጨረሻ ሰዓት ንስሐ ገብቶ የገነትን ደጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ረገጠ፡፡ እግዚአብሔር ሲሠራ በጠዋት የገቡ ይወጣሉ፣ በሠርክ የገቡ ይጸድቃሉ፡፡
ይህ አብርሃም ከእግዚአብሔር ተለይቶ ለሰባ አምስት ዓመታት በጣኦት ምድር ኖረ፡፡ እግዚአብሔር ግን አዘነለት፡፡ እስከ ሰባ አምስት ዓመቱ ልጅ አልነበረውም፡፡ ልጅ አልባነትን ተቀብሎ በደስታ ሲኖር ሳለ እግዚአብሔር የሞተውን ተስፋውን ቀስቅሶ ልጅ እሰጥሃለሁ ብሎ በሰባ አምስት ዓመቱ ቃል ሰጠው፡፡ ባለጠጋ በሀብቱ፣ ምሁር በወረቀቱ ይያዛል፣ እግዚአብሔር ግን በቃሉ ይያዛልና አብርሃም ይህን ቃል ይዞ ለዐሥር ዓመታት ጠበቀ፡፡ የተወውን፣ የረሳውን፣ የተቀበለውን ልጅ አልባነት እንደገና ቀስቅሶበት ለዐሥር ዓመታት ሲዘገይበት አብርሃም ደከመው፡፡ አብርሃም አሁን ባይችልም እግዚአብሔር እንደሚችል መቻሉንም በእርሱ ኑሮ እንደሚገልጥ አመነ፡፡ የልጅ ችግሩ ዕድሜ ብቻ ሳይሆን መሐንነትም የነበረበት ቢሆንም እግዚአብሔር ግን በሁሉን ቻይነቱ ድርቡን ሰንሰለት እንደሚቆርጥ አመነ፡፡
ከዐሥር ዓመታት በኋላ የአብርሃም ልቡ ደከመ፡፡ ሀብቱ እየበዛ ሲሄድ ደግሞ ይበልጥ አዘነ፡፡ ይህን ሁሉ ሀብት ማን ይወርሳል በማለት ደነገጠ፡፡ ዘመድ እንዳይወርሰው ከዘመድ ርቋል፡፡ እግዚአብሔር የዓይን ማረፊያዎቹን ሁሉ አንሥቶበታል፡፡ ወደ እርሱ ብቻ እንዲመለከት ዙሪያውን አጽድቶለታል፡፡ አብርሃም የሚወርሰኝ ልጅ ቀርቷል፣ የማየው ባሪያዩ ግን ይወርሰኛል ብሎ አመነ፡፡
አንድ ቀን፣ አንድ ምሽት ላይ አብርሃም ሁሉም አሸልቦ ሳለ በድንኳኑ ውስጥ በትካዜ ለራሱ ማዘን ጀመረ፡፡ የጎደለውን ነገር ደጋግሞ በማሰብ ልቡ በዕንባ ረጠበ፡፡ እግዚአብሔር ያለው ዘግይቷል፣ የምጠረጥረው ግን ይሆናል፤ እግዚአብሔር ያለው ልጅ ቀርቷል፣ የቤቴ ባሪያ እንደሚወርሰኝ ያለኝ ጥርጣሬ ግን እውን ሆኗል አለ፡፡ ይህንንም ለእግዚአብሔር ነገረው፡፡ እግዚአብሔር የመጨረሻይቱን ሰዓት ያውቃል፤ መሸነፍን ያያል፣ ሊረዳንም ይመጣል፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል ኪዳኑን አደሰለት፡፡ ዘሩን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚያበዛለት፣ ዘሩም ለአራት መቶ ዓመታት በግብፅ ባሪያ እንደሚሆን በአጉሊ መነጽር እያሳያ ነገረው (ዘፍ.15)፡፡
አብርሃምም ታላቅን ተስፋ፣ የማይቆጠር ትውልድን እንደሚያገኝ በልቡ አመነ፡፡ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት፡፡ የአብርሃም ደስታው ወደር የሌለው፣ ተስፋው ዕብለት የማይገጥመው፣ እስከ አራት መቶ ዓመታት ድረስ ስለ ትውልዱ መረጃ የተቀበለበት ነው፡፡ ይህን ተስፋ በተቀበለበት ዓመት ግን ትልቅ ፈተና ገጠመው፡፡ ፈተናው ከኑሮ የሚያፈናቅል ቢሆን ምንም አልነበረም ነበር፤ ፈተናው ግን ከእግዚአብሔር ተስፋ የሚያፈናቅል ነበረ፡፡ ዐሥር ዓመታት የታገሠውን እግዚአብሔር ለአንድ ዓመት መታገሥ አቃተው፡፡ ዓይነ ሥውር ሆኖ ለሰባት ዓመት የኖረ ሰው “ነገ ዓይንህ ይበራል” ቢሉት “ዛሬን እንዴት አድሬ?” አለ ይባላል፡፡ አብርሃም ዛሬን ማደር ከበደው፡፡ ሰው ነኝና ሰው የሚሄድበትን መንገድ ልሂድ ብሎ የሚያስብበት ፈተና በሚስቱ በሣራ በኩል መጣበት፡፡ ሣራ ገረዷን አጋርን ጋበዘችው፡፡ አብርሃምም ተፋውን ከመጠበቅ አቋራጩን መንገድ መጠቀም ፈለገ (ዘፍ.16)፡፡ ወደ አጋር ገባ አጋርም ፀነሰች፡፡ በአብርሃም ቤት ግን ሰላም ጠፋ፡፡ ክፉውን መንገድ የመራችው ሣራ መልሳ አብርሃምንና አጋርን ማማረር ጀመረች፡፡
አብርሃም ልጅ ፈለገ፣ ልጅ አገኘ፡፡ ነገር ግን ልቡ አልረካም፡፡ ምንም እስማኤል ልጅ ቢሆንም እግዚአብሔር ያየለት ልጅ ስላልነበረ አብርሃም አሁንም ሌጣነቱ ያሰቃየው ጀመር፡፡ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠን ነገር ሲዘገይ በእኛ መንገድ ያንን የሚመስል ነገር እናገኛለን፡፡ ልዩነቱ ግን የእግዚአብሔር ስጦታ ልብን ሲያሳርፍ የአቋራጭ ትርፍ ግን መልሶ ያሳምማል፡፡ አብርሃም እግዚአብሔርን ባለመጠበቁ ምክንያት የሦስት ሺህ ዓመት ጦርነት በትውልዱ ላይ ከፈተ፡፡ ዛሬ ድረስ የሚዋጉት ዐረቦችና እስራኤል የእስማኤልና የይስሐቅ ዘሮች ናቸው፡፡
ከታላቅ ተስፋ በኋላ ታላቅ ማዕበል አለ፡፡ አብርሃም ታላቅን ተስፋ ተቀበለ፣ ሰይጣን ደግሞ በሚስቱ በኩል ባዶነቱን አስቆጠረው፡፡ አብርሃም በተስፋ ተፍነከነከ፤ በሚስቱ በኩል ግን ሳይጨብጡ መዝለል እብደት መሆኑ ተነገረው፡፡ የሥጋ መፍትሔም ቀረበለት፡፡ ውጤቱ ግን ሰላምና እርካታ ማጣት ሆነ፡፡
አማርኛን ረግጠው የሚተረጉሙ መተርጉማን ቃልቻ የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ ‹‹ቃል ብቻ›› በማለት ይፈቱታል፡፡ በሰይጣን መንፈስ የሚታገዙና ሰይጣን የሚያናግራቸው ሰዎች ብዙ ተስፋዎችን ይሰጣሉ፡፡ በእጃችን የያዝነውን እስክንጥል በተስፋ ድምፅ ያራቁቱናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ‹‹ቃል ብቻ›› ሳይሆን ቃሉ ራሱ የሚሠራለት፣ በቃሉ መፍጠር የሚችል፣ ቃሉን ከሚያጥፍ ሰማይና ምድር ቢያልፉ የሚቀልለት አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ቃል ብቻ አይደለም፡፡
እግዚአብሔር በቃሉ ተናግሮኛል፣ ታላቅ ተስፋም ሰጥቶኛል ብለን ስንናገር ታላቅ ተስፋ መቁረጥ የእኛ ከምንላቸው ወገኖች ይነሣብናል፡፡ ያንተ እምነት፣ ያንቺ ተስፋ ማለቂያ የለውም፤ ይልቁንስ እርሱ ‹እርዱኝ እረዳችኋለሁ› ነው ያለው በማለት ከመጽሐፈ ባልቴት እየጠቀሱ ያረፈውን ልባችንን ያናውጡታል፡፡ የራሳቸውንም መፍትሔ በማቅረብ ሕገ ወጥ ነገር ውስጥ እንድንገባ፣ ሃይማኖት ከሌላቸው ጋር እንድንጋባ፣ ኃጢአትም በንስሐ ይጸዳል ሁሉም ያለፈለት በዚህ መንገድ ሄዶ ነው፤ ደግሞም አንዱ ጉሮሮ ላይ ካልቆምህ አትበላም በማለት በጠባብ መንገድ ላይ አቁመው ያፋጥጡናል፡፡ ከንግግሩ ባሻገር ይህን እምቢ ካላችሁ በቃ እንቆራረጣለን፣ መቃብራችሁም ላይ አንቆምም፣ የመጨረሻችን ነው በማለት ከተስፋችን ሊያፈናቅሉን የኃጢአትን ትርፍ ያቀርቡልናል፡፡ እግዚአብሔር ያቀረበልን ገና የሚፈጸም፣ እነርሱ ያቀረቡት ግን ተጨባጭ ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር ያቀረበልን የማይታይ እነርሱ የሚሉት ግን ለዓይን የጎላ ይመስላል፡፡ አብርሃም ሣራን እምቢ ቢል ኖሮ፡-
1- አጋር መጫወቻ ዕቃቸው፣ የግፍ ማርኪያቸው፣ ያለማመናቸውም መጣያ አትሆንም ነበር፡፡
2- ኑሮአቸው በሰላምና በጸጥታ ይቀጥል ነበር፡፡ እምቢ ቢል ለአንድ ቀን ይጨቃጨቃሉ፣ ድሮም አንተ የእኔ ነገር አይጣፍጥህም ይባባላሉ፤ ለዘለቄታው ግን ሰላም ይሆናል፡፡ ሐሰተኛው ሰላም እውነተኛ ጠብ አመጣ፡፡
3- ዘራቸው ያለባላጋራ ይኖር ነበር፡፡
አቋራጭ መንገድ ከዋናው ጎዳና ይልቅ የሚርቅ ነው፡፡ አብርሃም ከዚያ በኋላ ቢጠብቅ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው፡፡ መታገሥ ስላቃተው ሦስት ሺህ ዓመት ተጉዞም የማያልቅ ጦስ አመጣ፡፡ አቋራጭ ጊዜአዊ ፀጥታ፣ ዘላቂ ሁከትን ተዝቆ የማያልቅ መዓትን ያመጣል፡፡ እንኳን ጠብቁ ብሎን እግዚአብሔር ከልክያለሁ ቢለንም ዓለም ከምትሰጠን ይበልጣል፡፡ በአቋራጭ የምናገኘው ቁሳቁስን እንጂ እርካታን አይደለም፡፡ ብዙዎች ትዳራቸውን እምቢ ላለማለት እግዚአብሔርን አሳዝነዋል፡፡ እግዚአብሔርን አሳዝነው የተከተሏቸው ግን ዘመድ አልሆኗቸውም፡፡ እውነተኛው ፍቅር እግዚአብሔርን እየታዘዙ እንጂ እግዚአብሔርን እያሳዘኑ አይደለም፡፡ ብዙዎች ትዳራቸውን እምቢ ከማለት እግዚአብሔርን እምቢ በማለት ረክሰዋል፡፡ ሚስቶቻቸውን ለባለጠጋ ያከራዩ፣ ባሎቻቸውን ለወኅኒ የዳረጉ ስንቶች ናቸው፡፡ ከነአምላኩ ያገኘችውን ባሏን ከእኔና ከጌታህ ምረጥ ያለች በላይዋ ላይ ከሃዲ ሾማ በገዛ እጇ ትሰቃያለች፡፡ እግዚአብሔር የለሾች እንኳ የሚፈሩት ሃይማኖት የሌለውን ሰው ነው፡፡ የብዙ ከሃዲዎች መጋቢና ምሥጢረኛ ሃይማኖተኞች ናቸው፡፡ ከነሃይማኖት ውበቷ ያገኛትን ሴት ሃይማኖት አልባ አድርጓት አብሮ መኖር ያቃተው ነፋስ ዘርቶ ዐውሎ ነፍስ እያጨደ ያለ ስንቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቤን ልቀቅ የሚል አዋጁን ያሰማ ቀን እኛ የያዝናቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ካሉ በፈርዖን እንደሆነው መጀመሪያ በመቅሰፍት እምቢ ካልን በሞት አስወግዶ ልጆቹን ነጻ ያወጣል፡፡ የአንበሳን ልጅ ሰርቆ ማን በሰላም ያድራል! በእግዚአብሔር ሳይሆን በእኛ እመኑ ለሚሉ ትዳሮች ወዮላቸው!
እግዚአብሔር የነገረንና እየሆነ ያለው ቢለያይ እንኳ መደንገጥ አይገባንም፡፡ ዛሬ የሚታየው ነገ ይሰወራል፤ የማይታየው የእግዚአብሔር ተስፋ ግን እየገዘፈ ይመጣል፡፡ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል!
-ይቀጥላል-