የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወልደ ማርያም – የማርያም ልጅ

የክርስቶስ መወለድ በቤተ እስራአል ብቻ ሳይሆን በቤተ አሕዛብም ሲጠበቅ የኖረ ነው ። ሮማውያን አንድ አይሁዳዊ ወንድ ልጅ እንደሚወለድ ይጠብቁ ነበር ። የዚህም መነሻው ታሲቱስ የሚባል የጥንት ፀሐፊ “የዓለም ገዥና ጌታ ከይሁዳ እንደሚመጣ” ትንቢት አለ ብሎ ተናግሮ ስለ ነበር ነው። የቤተ ልሔም ሕፃናት ሲገደሉ የሮማ ዓለም አቀፍ ሥልጣንም ከዚህ ንግርት የተነሣ ስጋት ስለነበረው ነው ። ቻይናም በምሥራቅ የምትገኝ አገር እንደ መሆንዋ በምዕራብ አንድ ብርሃን ወይም አዋቂ እንደሚወለድ ታምን ነበረ ። በአራተኛው ጨረቃ በስምንተኛው ቀን አስደናቂ ብርሃን በንጉሡ ቤተ መንግሥት ደቡብ ምዕራብ ታይቶ ቤቱን በሙሉ አበራ ። ንጉሡም በነገሩ ተደንቆ አዋቂዎችን ሲጠይቅ በምዕራብ ትልቅ ቅዱስ እንደሚነሣና ሃይማኖቱ በአገራቸው እንደሚሰበክ መጻሕፍት ጠቅሰው ነገሩት ። ግሪኮችም ከክርስቶስ ልደት ስድስት መቶ ዓመት በፊት በነበረው አስክለስ በሚባል ጸሐፊ እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን ይጠብቁ ነበር፡- “ስለ ኃጢአትህ በራሱ ላይ ስቃይ ለመቀበል እግዚአብሔር እስኪገለጥ ድረስ ከርግማን ለመውጣት ሌላ ግብ አትፈልግ።”

በለዓም የአሕዛብ ፈላስፋ ነበር ። ስለ ክርስቶስ መምጣት ፣ ስለ ኮከቡ መገለጥ ትንቢት ተናግሮ ነበር (ዘኁ 24 ፡ 17።) አይሁድም በባቢሎን ምርኮ ለሰባ ዓመታት የመሢሑን መምጣት ለአሕዛብ ሲናገሩ ኖረዋል ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው ክፍለ ዘመን የሰባ ሊቃናት የብሉይ ኪዳን ትርጉም ማለትም ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ቋንቋ መተርጎም መላው ዓለም ስለ መሢሑ የተነገረውን ትንቢት እንዲያውቅ ረድቶታል ። ሰብአ ሰገል ወደ ቤተ ልሔም መምጣታቸው ይህን ሁሉ ያገናዘበ ነው ። ነገር ግን በክርስቶስ መወለድ በአገራቸው ታላቅ ብርሃን አይተዋል ። የምርምር መጻሕፍቶቻቸውን ሲገልጡ ታላቁ ሕፃን እንደ ተወለደ ተረዱ ። በኮከብም እየተመሩ ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ለሕፃኑ ሰገዱ ፣ ገበሩ ። ክርስቶስ መላው ዓለም የሚጠብቀው ናፍቆት ነው ። ክርስቶስ የማርያም ልጅ ነው ።

ድንግል ሆይ ! ሰብአ ሰገል ከሩቅ አገር ሊሰግዱለት መጡ ፣ የቅርቡ ሄሮድስ ሊገድለው ፈለገ ። ሄሮድስ ቢሰጋ ጠባዩ ነው ። ወንድ ልጆቹን ፣ ሚስቱን ፣ የሚስቱን እናት በሥልጣኑ ሰግቶ አስገድሏቸዋል ። ንጉሥ ተወለደ ተብሎ የዓለም ልዑላን ወደ አገሩ ቢመጡ መደንገጡ እውነት ነው ። ስለ ሥልጣኑ ስስት ብዙ ጭካኔ ሠርቷልና በዘግናኝ ሁኔታ ታሞ ፣ ተልቶ ሳለ “ስሞት ማንም አያለቅስልኝም ፣ ቀባሪ አላገኝም” ብሎ ጣር ሲይዘው የአይሁድን ታላላቅ ሰዎች አሰረ ። “ነፍሴ ስትወጣ እነዚህን ሰዎች ግደሏቸው” ብሎ አዘዘ ። “ለእነርሱ ሲለቀስ ለእኔም አብሮ ይለቀስልኛል” ብሎ ነው ። ነፍሱ ስትወጣ ግን እኅቱ እነዚህን የአይሁድ ታላላቅ ሰዎች ከእስር ቤት አስወጣች ። እንዳሰበውም አይደለም በታላቅ ልቅሶ ሕዝቡ ቀበረው ። ድንግል ሆይ ! በዚህ በሄሮድስ ዘመን ስለ ተወለደው ሕፃን ንጉሥነት ሲነገር ልጅሽን እያሰብሽ ትጨነቂ ነበር ። ገና በጠዋቱ የባለ መስቀሉ እናት መስቀል ተሸክመሽ ነበር ። የእርሱ መስቀል የቤዛነቱ ፣ የአንቺ የሰማዕትነትሽ ምልክት ነው ።

ሰብአ ሰገል የጥበብ ሰዎች ፣ ጥበባቸው ቢያሳርፋቸው ሊፈልጉት አይመጡም ነበር ። በብዙ የክርክር መድረክ የሚውሉ አፍ ያልፈታውን ሕፃን ሊያዩ መጡ ። አንደበትን የፈጠረ ፣ ለአእዋፋት ዝማሬን የሰጠ እርሱ ግን የማይናገር ሕፃን ሁኖ ተገለጠ ። ነገሥታት ሥልጣናቸው ቢያሳርፋቸው የቤተ ልሔሙን ሕፃን ሊፈልጉት ባልመጡ ነበር ። ባለጠጎች ናቸውና ሀብት ክርስቶስን ተክቶ ቢያስደስት ክርስቶስን ፍለጋ ባልመጡ ነበር ። ያለ ክርስቶስ የዚህ ዓለም ክቡር ነገር ሁሉ ጥያቄ ነው ። ድንግል ሆይ ! በእቅፍሽ ያለው ለዓለም ጥያቄ መልስ ነው ። ሰብአ ሰገል የልጅሽን ሞት ነገሩሽ ። በልደቱ ቀን ሞቱ የተወራው የክርስቶስ ብቻ ነው ። ወርቅ ፣ ዕጣን ፣ ከርቤ ገበሩለት። ከርቤው ሞቱን የሚገልጥ ነው ። ወርቅ ንጉሥነቱን ፣ ዕጣን ክህነቱን የሚያሳይ ነው ። ይህን ስትሰሚ የእናትነት አንጀትሽ ያዝናል ። ነገሥታት ከገበሩለት የነገሥታት ንጉሥ መሆኑ ታወቀ ፤ እርሱ አምላክ ነውና ሰገዱለት ። ስግደቱ የአክብሮት ቢሆን ኖሮ በዕድሜ የሚበልጥ አረጋዊ አለ ። ስግደቱ ግን የአምልኮት ነውና ለሕፃኑ የዘላለም አባትነት ሰገዱ ።

ልጅሽም በየሄደበት ሁሉ “የሰው ልጅ” እያለ ራሱን ይጠራል ። የማርያም ልጅ ነኝ ማለቱ ነው ። የአገሬ ባለ ቅኔም ገርሞት እንዲህ ብሎ ይጠይቀዋል ፣ አንቺም ጠይቂልን፡-

የማርያም ልጅ ነኝ ብለህ ፣
ወልድ በራስህ ተኮራህ ፤
አብ አይበልጥም ወይ አባትህ ፣
ተለማኝ እናትህ ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 7 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ