መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ዋጋ ያለውና ዋጋ የሚያስከፍል ጥሪ

የትምህርቱ ርዕስ | ዋጋ ያለውና ዋጋ የሚያስከፍል ጥሪ

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ          ዓርብ መስከረም 9/2007 ዓ/ም
          “አረም ያለ እንክብካቤ ያድጋል፣ የጓሮ አትክልት ግን ያለ እንክብካቤ አያድግም” የሚለው ምሳሌ የምሳሌዎች አውራ ይመስላል፡፡ መልካም ነገር ሁሉ እንክብካቤ ይፈልጋል፣ መልካም ያልሆነ ነገር ደግሞ ያለ እንክብካቤ ያድጋል፡፡ በዚህ ክፉ ዓለም ላይ ክፉ ፈተና የለበትም፣ በተቃራኒው መልካም ነገር ደግሞ ብዙ ትግል አለበት፡፡ በእውነት ዋጋ የምንከፍለው ዋጋ ላለው ነገር ነው፡፡ በርግጥ፡- “እልህ ምላጭ ያስውጣል” እንደሚባለው ለእልህ ብዙ ዋጋ እንከፍላለን፣ በትክክል ስንኖር ግን ዋጋ የምንከፍለው ዋጋ ላለው ነገር ነው፡፡ ዋጋ ያለው ነገር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ዋጋ የኋላ እሸት፣ የማታ እንጀራ፣ የድል ደስታ፣ የመኖር ክብር፣ የፍጻሜ ድል፣ የመጨረሻ ሽልማት ነው፡፡ መጨረሻውን በትክክል ያላየ አይጀምርም፣ መጨረሻውን ያየም ዋጋ ለመክፈል አይፈራም፡፡ የእግዚአብሔር ጥሪ ዋጋ ያለውና ዋጋ የሚያስከፍል ጥሪ ነው፡፡
ጥሪ ምንድን ነው?
          ጥሪ ከአንድ ባለሥልጣን፣ ከአንድ ደጋሽ፣ ከአንድ ጉዳይ ካለው ወገን የሚመጣ የድረስ ጥያቄ ነው፡፡ ጥሪ ካለንበት ቦታ፣ ሁኔታና አስተሳሰብ የማፈናቀል ባሕርይ አለው፡፡ መሠረታዊው የጥሪ ጠባይም ይህ ነው፡፡ አንድ ባለሥልጣን ለሹመት ሲጠራን ካለንበት አገር ርቀን በአምባሳደርነት ልንሄድ እንችላለን፣ አንድ ደጋሽ ሲጠራንም ካለንበት ረሀብ በነጻ እንጠግባለን፡፡ አንድ ጉዳይ ያለው ወገን ሲጠራንም ካለንበት አስተሳሰብ ወጥተን በዚያ ጉዳይ እንያዛለን፡፡ ጥሪ ካለንበት ቦታ፣ ሁኔታና አስተሳሰብ ያፈናቅላል፡፡ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ የማይሰጡት እስከ ዛሬ ዋጋ የሰጡትንና የኖሩለትን ነገር መጣል ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ሰዎች ካሉበት ፍላጎትና አስተሳሰብ ወጥተው እስከ ዛሬ እውነት ያሉትን ነገር መጣል ያለፈውን ዘመን የሚሰርዝባቸው፣ በከንቱ ኖሬአለሁ የሚያስብላቸው ይመስላቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ጥሪ ግን ዘመንን፣ ወገንን፣ ቤተሰብን፣ ምድራዊ ትርፍን የሚክስ ጥሪ መሆኑን አያስተውሉም፡፡ አብርሃም በጥሪው ዘመኑ ተክሶለታል፣ 75 ዓመት የኖረው በጣዖት አምልኮ ቢሆንም አሁን ግን ዘመንን በሚክሰው ጥሪ ያረጁ ዓመታቶች ልደት አገኙ፡፡ ጴጥሮስ ታንኳውንና ሥራውን ጥሎ ተከተለ፡፡ ዕድሜ ልኩን ዓሣ አጥማጅ ቢሆን ኖሮ ዛሬ አናውቀውም ነበር፡፡ ጥሪው ግን የማይጠፋ ስም ሰጠው፡፡ የዘብድዮስ ልጆች ዮሐንስና ያዕቆብ አባታቸውን ትተው ተከተሉ፡፡ የእግዚአብሔርን አባትነት አተረፉ፡፡ ጥሪው ከተውነው በላይ የሚያሳጭደን ነው፡፡ ቢሆንም ጥሪ ካለንበት ቦታና አስተሳሰብ አድራሻ ያስለውጠናል፡፡ ይህ ራስን መካድ ነው፣ ሰው ደግሞ ራሱን መካድ አይፈልግም፡፡ ስህተተኛ እንደሆነ ቢረዳም እንኳ ብዙ ዘመን የተቀበለውን ነገር መጣል አይፈልግም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገርን ለማመን አንድ ነገርን መካድ ግድ ይላል፡፡ ክርስቶስን ለማመን ራስን መካድ ግዴታ ነው፡፡
          የእግዚአብሔር ጥሪ በምድር ላይ ካሉት ጥሪዎች የተለየ ጥሪ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ የተለያዩ ጥሪዎች አሉ፡፡ የሠርግ፣ የምርቃት፣ የፍርድ ቤት፣ የሞት ጥሪዎች አሉ፡፡ አንዳንዱ ልንቀርበት የምንችለው ጥሪ ነው፡፡ የፍርድ ቤት ጥሪ ግን ድንበር ጥሰን ካልሄድን በአገር ቤት ሆነን የምንቀርበት አይደለም፡፡ አስገዳጅ ጥሪ ነው፡፡ የሞት ጥሪ ደግሞ ከፍርድ ቤት ጥሪ ይበረታል፡፡ ድንበር በመሻገር የማናመልጠው ነው፡፡ ለሞት የራቀ ጥግ በምድር ላይ የለምና፡፡ የእግዚአብሔር ጥሪ ከፍርድ ቤትና ከሞት ጥሪ በላይ የማይቀርለት ጥሪ ነው፡፡

          በር ያለ ቦታው አይገጥምም፣ አያምርም፣ አይቆምም፡፡ ሰውም ያለ ጥሪው ከኖረ ትልቅ የሕይወት ክፍተት ይገጥመዋል፡፡ በምድራዊ ነገሮች ውጤታማ ቢሆን እንኳ በውስጡ አንድ ነገር እንደረሳ የሕይወት ቅሬታ ይሰማዋል፡፡ ቅር የሚለው ሰው ደግሞ የረሳውን ነገር ካላስታወሰ በፍጥነት መጓዝ፣ በደስታ መጫወት፣ በርጋታ መቀመጥ አይችልም፡፡ የሕይወት ቅሬታ የማይደለል ሕመም፣ የማይደነዝዝ ስሜት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለጠራን ነገር መቅረት አይደለም መዘግየትም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ለእግዚአብሔር ጥሪ በሙሉ ፈቃድ ካልተለየን የሚገጥመን ነገር ብርቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ሙሴ ለዚህ ጥሪ ለመለየት ባንገራገረ ጊዜ እግዚአብሔር ሊገድለው ፈለገ፡፡ ለተፈጠረበት ነገር የማይኖር አንሶ የሚኖር፣ ሞቶ የሚኖር ነው፡፡ ደግሞም ለእግዚአብሔር ያልሆነ ዕድሜ ለምንም አይሆንም፡፡ ዮናስ የእግዚአብሔርን ጥሪ ተጋፍቶ በሄደ ጊዜ የጠበቀው የሞት አደጋ ነው፡፡ ለእርሱ የመጣ አደጋ ለሌሎችም ሊተርፍ ነበር፡፡ ከጌታው የኮበለለ የታወከ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መታወክ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይሁዳ ከጥሪው በተፈናቀለ ጊዜ በራሱ ላይ ወሰነ፡፡ ጥሪውን ያላከበረ ሰው የመኖር አቅም እያጣ ይመጣል፡፡ የጥሪው በረከት ለመኖርም ይተርፋልና፡፡
          የእግዚአብሔር ጥሪ ከምድራዊ ጥሪ ልዩ የሚያደርገው፡-
1.     ቅዱስ ነው፡- “ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና” ይላል (2ጢሞ 1፥9)፡፡ በዓለም ላይ ከእግዚአብሔር ጥሪ ውጭ ቅዱስ ወይም ልዩ ጥሪ የለም፡፡
2.    ሰማያዊ ጥሪ፡- “ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ….” ይላል (ዕብ 3፥1)፡፡ ትልቅ ዕድለኝነታቸውን እየነገራቸው ነው፡፡ ጥሪው ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ፣ የሚያልፍ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለመዳንና ለአገልግሎት ይጠራናል፡፡ በዚህ ክፍል የምናየው የአገልግሎትን ጥሪ ነው፡፡ ሁለቱም ጥሪ ፈቃደኝነትን ሲጠይቅ ለመዳን ጥሪ እሺ አለማለት የዘላለም ሞት፣ ለአገልግሎት ጥሪ እሺ አለማለት ደግሞ የተበላሸ ኑሮን ሽልማት አልባ ክርስትናን ያመጣል፡፡
የጥሪ እንቅፋቶች
          ጥሪው ሁለት ዋና ዋና እንቅፋቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ከውስጣችን ያለ እንቅፋት ሲሆን ሁለተኛው ከውጭ የሚመጣው እንቅፋት ነው፡፡ ዋናውና ከባዱ ራሳችን ጋ ያለው እነቅፋት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንመለከት፡-
1.     ራስን ያለ መጠን ማየት፡- የሰው ልጅ ራሱን ያለ ጌታ ሲያይ የአገልግሎትን ጥሪ እየገፋ ይመጣል፡፡ ማንም ሠራተኛ በራሱ በጀት መንግሥትን አያገለግልም፣ በራሱ መሣሪያም ለንጉሥ የሚዘምት ወታደር የለም፡፡ እግዚአብሔር ለመንግሥቱ በጀትና ኃይል አለው፡፡ እኛ አቅምና ኃይል ቢኖረን እንኳ ለመንፈሳዊው መንግሥት የማይጠቅም ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ሥራ ከሰው ኃይል ይልቅ በመንፈሱ የሚሠራ ስለሆነ ነው፡፡ ሙሴ ንግግር አለመቻሉን አስቦ ጥሪውን እንቢ አለ፡፡ እግዚአብሔር አፈኛውን አሮንን ትቶ ሙሴን ሲመርጥ አልተሳሳተም፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ቅንነትን እንጂ ችሎታን አይደለም፡፡
2.    አካባቢን ማየት፡- ጌዴዎን እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ የቤተሰቡን ትንሽነት አየ፡፡ ዛሬም ጣዖት ከሚያመልክ ቤተሰብ፣ ወይም በዝሙት ከሚተዳደር ወገን የተወለዱና ያደጉ ጥሪው ሲመጣ አካባቢያቸውን ያያሉ፡፡ የእግዚአብሔር ጥሪ ግን ከታሪካችን በላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር የዛሬ እሺታችን ላይ ክብሩን ይገልፃል እንጂ ታሪካችን ላይ አይዘገይም፡፡
3.    ቤተሰብን ማሰብ፡- አንድ ጌታን መከተል የጀመረ ደቀ መዝሙር ከጥሪው ወደ ኋላ ለማለት አባቴን ቀብሬ ልምጣ ብሎ ጠየቀ፡፡ ጥያቄው ዕለታዊ ቀብርን የሚመለከት አይመስልም፡፡ ትንሽ መርዳት አለብኝ የሚል ስሜት ነው፡፡ ጌታ ግን አሳቡን አላደነቀለትም፡፡ “ኢየሱስም፡- ተከተለኝ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው” (ማቴ. 8፥22)፡፡ ቤተሰቤን ነጻ ማውጣት አለብኝ በሚል እሳቤ ከአገልግሎት የወጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ እኛ የእግዚአብሔርን ቤት ስንሠራ እግዚአብሔር የእኛን ቤት እንደሚሠራ አለማሰብ ነው፡፡
የጥሪው ውጫዊ እንቅፋቶች፡- ከሚወዱንና ብዙ ከተመኙልን ሰዎች የሚወጣ ነቀፋ አለ፡፡ ጌታን ብለህ እንዲሁ መንከላወስ ነው፡፡ ገና ነህ፣ ይደረስበት ነበር፣ ሁሉም የራሱን ኑሮ እየኖረ ነው፤ አንተ ከጓደኞችህ በታች ሆንህ በማለት ጥሪውን ከቁሳቁስ ጋር ያወዳድሩብናል፡፡ ሕይወትን እንዳገኘ የተሰማው ሰው ቁሳቁስ አጣሁ ብሎ አያዝንም፡፡ ይህንን ውጫው እንቅፋት መናቅ ይገባናል፡፡ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ሊለየን ይችላል? (ሮሜ 8÷35-39)፡፡
እግዚአብሔርን ለማገልገል ጥሪው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ይነገረን ሆናል፡፡ ለሙሴ የሆነው እንደዚህ ነው፡፡ ኢያሱ ግን ጥሪውን የተቀበለው በሙሴ በኩል ነው፡፡ አንዳንዴ ጥሪው በልባችን ይሰማናል፡፡ አንዳንዴ ጥሪውን እምቢ እያልን ይከተለናል፡፡ ብዙ ጥሪ የነበራቸው ዓለም ያመለጠቻቸው መስሏቸው ሄዱ፣ ግን የፈለጉት ላይ ቢደርሱም የፈለጉት የሚያረካ አይደለምና አልረኩም፡፡ ፈጥነው ከእግዚአብሔር ጋር ካልታረቁ ሕይወታቸው በትግል ውስጥ ማለፉ የማይቀር ነው፡፡
የእግዚአብሔር ጥሪ ዋጋ ያለው ጥሪ ነው፡፡ ዋጋም የሚያስከፍል ጥሪ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለጠራን ዓላማ ዛሬ እንድንለይ በቅዱስ መንፈሱ ያግዘን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም