“አቤቱ ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ ።” (መዝ. 38 ፡ 4) ።
“በሉ እናንተም ሂዱ እኛም ወደዚያው ነን ፣
ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው ፤”
ዛሬ የሞተው ሰው ይኑር ብንል አንድ ቀን መሞቱ አይቀርም ። ሞት የማይቀር የሰው ዕጣ ነው ። የሰው ልጅ አእምሮው ለሞት ስለተሸነፈ ለበሽታ መድኃኒት ሲፈልግ ፣ ለሞት ግን መድኃኒት ለመፈለግ አልተነሣም ። ሁሉን ያስተካከለ ሚዛን ሞት መሆኑን እናያለን ። የድሀውን ሞት ባለጠጋው ፣ የምስኪኑን ሞት ንጉሥ ይሞታል ። የመቃብር ስፍራዎችን ስንጎበኝ ከእኛ የተሻሉ ኃያላንና ጠቢባን መቃብር ውስጥ እንዳሉ እናረጋግጣለን ። ነጭ ይለብሱ የነበሩ ሽቅርቅሮችን ስናስብ ዛሬ አፈር/ጭቃ ውስጥ ተኝተዋል ። መሬትን ለመርገጥ ይጸየፉ የነበሩ ዛሬ ድንጋይ ተጭኗቸዋል ። ቤታቸውን አያምኑት የነበሩ ዛሬ ሁሉን ትተው ላይመለሱ ባዶ እጃቸውን ከቤታቸው ወጥተዋል ። በሕይወት ዘመናቸው ይጨነቁለት የነበረው ነገር ፣ እኔ ከሌለው ይህ ነገር ምን ይሆናል ? ከሌለሁ እገሌም ቆሞ አይሄድም ሲሉ የነበሩ እነርሱ ሞቱ እንጂ ሕይወት እየቀጠለ ነው ። በሽታዬን አይስማ ቀድሞኝ ይሞታል ብለው ሲታክቱ የነበሩ ሞታቸው ተሰምቶም ነገሮች እየቀጠሉ ነው ። እርግጥ ነው ከሞተ ጋር የሞተ አላየንም ። ሁሉም የራሱን ምጽአት ወይም ዕለተ ሞቱን ይጠብቃል።
የሕንዱ የነጻነት መሪ የነበሩት ማኅተማ ጋንዲ፡- “ተስፋ መቍረጥ ሲሰማኝ በታሪክ ሁሉ ምንጊዜም የፍቅር መንገድ ማሸነፉን አስባለሁ ። ጨካኞችና ነፍሰ ገዳዮች ነበሩ ፤ ለጊዜው የማይደፈሩ መስለው ይታያሉ ። ሆኖም በመጨረሻ ሁልጊዜም ይወድቃሉ ። አስታውሱ !! ሁልጊዜ!!” ብለዋል ። ሶቅራጥስም፡- “በዚህች ምድር ሁሉም ነገር ያልፋልና ስታገኝ ከልክ በላይ አትደሰት ፣ ስታጣም አብዝተህ አትከፋ” ብሏል። መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ክፍል ይህን ያረጋግጥልናል ። የዘፍጥረት መጽሐፍ ሁሉም ነገር ጅማሬ እንዳለውና ወደ ተጻፈለት ግብ እንደሚጓዝ ይነግረናል ። የዘጸአት መጽሐፍ ኃያላን ሰጥመው ድሆች እንደሚሻገሩ ያወሳል ። የዘሌዋውያን መጽሐፍ በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፈውን እግዚአብሔር ስለማገልገል ይተርካል ። የዘኁልቍ መጽሐፍ በእግዚአብሔር የታወቅን ፣ የራስ ጸጉራችንም የተቆጠረ መሆኑን ይተነትናል ። የዘዳግም መጽሐፍ እኛ ስናልፍ ትውልድ እንደሚቀጥል ይገልጻል። የኢያሱ መጽሐፍ ሁሉም ነገር በጊዜው ፍጻሜ እንደሚያገኝ ያስተነትናል ። የመሳፍንት መጽሐፍ ሁሉም መሪ የሆነበት አገር እንደሚፈርስ ያትታል ።
የሩት መጽሐፍ ለሚያልፍ ችግር የማያልፍ ሕይወትን ማጣት እንደማይገባ ያስረግጣል ። የሳሙኤል መጽሐፍ አህያ ፈላጊ ሳኦልን ፣ እረኛውን ዳዊት ያከበረውን እግዚአብሔር በመግለጥ ትልልቆች ሁሉ የጀመሩት ከትንሽ መሆኑን ያብራራል ። የነገሥት መጽሐፍ አገርን የሚመራ እግዚአብሔር መሆኑን ይገልጣል ። የዜና መዋዕል መጽሐፍ ስለ አገርና ስለቤተ ክርስቲያን ደግ ደጉን ብቻ ማሰብ እንደሚገባ ያትታል ። የዕዝራ መጽሐፍ እግዚአብሔር ከሰጠን ስጦታዎቻችን አንዱ ደራስያን/መጽሐፍ የሚጽፉ መሆናቸውን ያስተምራል ። የነህምያ መጽሐፍ አገር ፈርሶ በለማ ከተማ ቢኖሩም ልብ እንደማያርፍ ይገልጻል ። የአስቴር መጽሐፍ እኔ የማስፈልገው ለማን ነው ? የሚለውን ጥያቄ ያነሣል ። የኢዮብ መጽሐፍ የተዋረደው ሁሉ የከበረ እንደነበር ይናገራል ። የዳዊት መዝሙር እግዚአብሔርን በሕይወት ውጣ ውረድ ሁሉ መጠጋት እንደሚገባ ያስረግጣል ። የምሳሌ መጽሐፍ ከሰው ጋር መኖር መቻል ትልቅ ጥበብ መሆኑን ይገልጻል ። መጽሐፈ መክብብ ደስታም ኀዘንም ሁሉም ያልፋል ፣ የአሁኑ የመጨረሻ አይደለም ይለናል ። የሶቅራጥስ አሳብም ከዚህ ከመክብብ መጽሐፍ ይቀዳል ።
ብዙ ሰው የሚናገረው ነገ አንደበቱ እንደሚታሰር ሆኖ አይደለም ። ብዙ ሰው የሚሮጠው ነገ እንደሚቆም ዘንግቶ ነው ። ብዙ ሰው የሚጨነቀው ሞት የሚባል ጥሪ እንዳለ ረስቶ ነው ። ሰው ሞት እንዳለ እያሰበ ቢራመድ አይደናቀፍም ። ትልቁ ሞኝነት ወዳጅን እየቀበሩ እኔ አልሞትም ብሎ ማሰብ ነው ። ልጅን እየቀበሩ ገና ግፍ የሚሠሩ ወላጆች መኖራቸው ይገርማል ። ሞቱን የሚያስብ ትልቅ ጠቢብ ነው። የቀረን ዘመን በጣም አጭር ነው ። የምንዘገየው ለጥቂት ቀን ነው ። ስለዚህ አንደበታችንን መጠበቅ አለብን ። ዘግይቶ የተፈታው አንደበት ቀድሞ ይዘጋልና ለአንደበታችን ጠንቃቃ መሆን ይገባናል ። ነቢዩ በየቀኑ ካለው ተናግሮ አናጋሪ ማረፍ ስለፈለገ “ጥቂት ተወኝ” ብሎ ለመነ ።
“እኔ መንገደኛ ተሸኝቶ አዳሪ ፣
ምን ክፉ አናገረኝ እንግዲህ ከቀሪ ፤
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም.