“ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ ።” (መዝ. 38፡13) ።
የቅዱስ ዳዊት ትግሎች ብዙ ነበሩ ።
1- በቤቱ የተገፋ ነበር
እንደ መጨረሻ ልጅነቱ ፣ እንደ መልከ መልካምነቱ ፣ ጥበብ የሞላበት ብላቴና እንደ መሆኑ እንክብካቤ ያላገኘ ነበር ። ራሱ በገዛ አንደበቱ ሲናገር፡- “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” ብሏል (መዝ. 26 ፡ 10)። አባትና እናት ከተወ ማን ይቀበላል ? አባትና እናት ጥለው የሚቀበል እግዚአብሔር አለ ። የጠፋ ቤተሰብን የሚያገናኙ አካላትን እያየን እየሰማን ነው ። ወላጅ ጥሎ እግዚአብሔር እንደሚያነሣ ማረጋገጫ ነው ። ሊቁ፡- “አንተ አቡነ ወአንተ እምነ – አንተ አባታችን ነህ ፤ አንተ እናታችን ነህ” ይለዋል ። “ስም ይወጣል ከቤት ይከተል ጎረቤት” እንዲሉ ቤተሰብ ከጣለ የሚያነሣ ሰው ማግኘት ፣ እኅት ወንድም ከናቀ የሚያከብር መፈለግ ከባድ ነው ። አባራሪ ሲያባርር ሯጭ ሁሉ ወደ ቤቱ ይፈጥናል ። ጠላት ሲያባርር ወላጅ ደጁን ከዘጋ በምድር ላይ ሌላውን ማመን ሊከብድ ይችላል ። ሕይወት ግን ሁለመናዋ የተዘጋ አይደለም ። ሰው የዘጋውን የሚከፍት እግዚአብሔር በመንበሩ አለ ።
ቅዱስ ዳዊት የወላጅ ደጅ በቤተሰብ ሲዘጋበት ፣ የአገር ደጅ በንጉሡ ሲቆለፍበት እግዚአብሔር ግን የነሐሱን መወርወሪያዎች ሰብሮ ምድሩን አወረሰው ። “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ” ብሎ ዘመረ ። ሳኦል ሲጠፋ እርሱ ሲነግሥ ተመልክቷል ። (መዝ. 36 ፡ 9)። ጌታችንም፡- “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና” ብሏል። (ማቴ. 5 ፡ 5)። ብልጦች ምድርን እንወርሳለን ብለው ብዙ ስልት ይነድፋሉ ። ተወድደው እንደሆነ ወዲያው ይጠላሉ ። ተፈቅረው እንደሆነ ይሰለቻሉ ። የዋሃን ግን እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ናቸውና እንደ ዳዊት ምድርን ይወርሳሉ ። “የማታ ማታ እውነት ይረታ” እንዲሉ የማታ ማታ የዋሆች ያሸንፋሉ ። የዋህ ማለት እውነትን በፍቅር የያዘ ማለት ነው ። ዳዊት የዋህ ፣ ኀዳጌ በቀል/በቀልን ለጌታ የሚተው ሰው ነበር ። ዳዊት ለጠላቱ ልቅሶ የሚቀመጥ የይቅርታ ልብ የነበረው ሰው ነው ።
እኛም በቁራሽ እንጀራ ወላጅ አድልቶብን ይሆናል ። ካሉት ልጆች እኛ እያለን የተረሳን ሆነን ይሆናል ። እነዚያ እንጂ እርሱስ ዋጋ የለውም ተብለን ይሆናል ። ወንድማችን እያጠፋ እኛ የምንገረፍ ፣ ቤተሰብ ሲሰባሰብ እኛ ለግብዣ የማንጠራ ሆነን ይሆናል ። አንዳንዴ የሌለውን ልጅ እናትም አትወደውምና በማጣታችን ተገፍተን ይሆናል ። ባዕድ የሚኖርበትን አገራችንን መኖር አትችሉም ተብለን ተባርረን ይሆናል ። ቤት አልባ ፣ አገር አልባ መሆን እንዴት ተብሎ እንደሚለቀስበት ግራ ገብቶን ይሆናል ። የእግዚአብሔር አሠራር ግን ድንቅ ነው ። ያሰበልን ቦታ የሚያደርሰን በመግፋት ነው ። እኛማ ትክል ድንጋይ ነን ። የሚያፈስሰውን ቤት መልቀቅ እንፈራለን ። አከራይ ሲያባርረን ቤት እንሠራለን ። አንድ ቤት ሳይሆን ሁለት ቤት እንገነባለን ። ወዳጆቻችን ከጠቀሙን ይልቅ ጠላቶቻችን የጠቀሙን ይበልጣል ። ቤተሰብ የገፋን ከሆንን አንተን ይህ ቤት አይችልህም እያሉን ነው ። ለአገር የታጨ ቤት አይችለውምና ። ድንቅ ፈጠራ ለዓለም ያበረከቱ አይችልም ተብለው ከትምህርት ቤት የተባረሩ ናቸው ። ሰዎች ሲረግሙህ ፣ ሃይማኖተኛ ነን ባዮች ሲኦል ማድረሻ ውግዘት ሲያስተላልፉብህ አቅምህን ፈርተውት ነው ።
ዳዊት ለሥራ የሚፈለግ ለመብል የተረሳ ብላቴና ነበር ። መነሻው ታናሽ ቢሆንም እግዚአብሔር መድረሻውን ታላቅ አደረገለት ። ባለው ለማመስገን የሚሞክር ፣ ሲደሰት በምስጋና ፣ ሲከፋ በእንባ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወጋ ነበር ። እግዚአብሔርም ማድነቅ ይወዳልና፡- “እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።” (የሐዋ. 13 ፡ 22)። ሰው ቢገፋን እግዚአብሔርን መጠጋት ይቻላል ። በእሮሮ ከመኖር በፍቅር መዘመር ፣ በራእይ መሮጥ ታሪክ ይለውጣል ። አይዟችሁ በርቱ ። መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- “ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል” (ኢዮብ 8፡7) ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም.