በጥሩ ጀምሮ በጥሩ አለመፈጸም እንዳሳዘነ ይኖራል ፣ የአገራችን ችግር አጨራረስ ነው። ዕለታዊውን እንደ ዘላለማዊ መኖር እየበረከተ ነው። ስንባላ፣ ስንነጣጠቅ፣ ስንፈራረድ፣ ስንጨካከን ዘላለም በምድር ላይ የምንኖር ይመስላል። ዓለም ብላሽ ነው። የተበላሸ ሥርዓት የሚያስተዳድረው፣ የማይታዩ ረቂቃን አጋንንት የሚዘውሩት ፣ እግዚአብሔርን በገዛ ምድሩ እናስወጣው ብለው ሰውና ሰይጣን የሚመክሩበት ነው። ዓለም ብላሽ ነው። የወደቁትን ስናይ ቆመው የሚያውቁ አይመስሉም። ያ ሁሉ ውበት ምነው በአንድ ጊዜ ረገፈ? ያ ሁሉ ቁመና ምነው መሬቱን ሞላው? የቆሙትን ስናይ የሚወድቁ አይመስሉም። የጠፋውን ስናይ የነበረ አይመስልም። ያለውንም ስናይ የሚጠፋ አይመስልም። የነበረ ያለና የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነው። አልፋ ወ ኦ እርሱ ብቻ ነው።
ዓለም ብላሽ ነው። ወተቱን የሚያጠቁር ማሩን የሚያመርር ነው፡፡ ሌባን የሚያወድስ፣ ንጹሑን የሚያረክስ ነው፡፡ ዓለም ብላሽ ነው፣ ያልሰጠ ስስታምን እያከበረ ሰጪውን ሰው የሚሳደብ ነው። ዓለም ብላሽ ምሁሩን እብድ፣ አላዋቂውን ሐቀኛ ብሎ የሚጠራ ነው። ዓለም ብላሽ ነው፣ ጥቂት ቀን የቀረውን ሽማግሌ አስለቅሶ የሚሸኝ ነው። ዓለም ብላሽ ነው፣ እውቅውና አንቱታው ለሰይጣን ወድቀው ለሰገዱ የሚሰጥ ነው። ዓለም ብላሽ ነው፣ የጋራ ጥቅምን እንጂ የጋራ ፍቅርን የማያወራ ነው። ዓለም ብላሽ ነው፣ በአደባባይ እየሸመገለ በጓዳ መሣሪያ የሚሸጥ ነው። ዓለም ብላሽ ነው ፣ ባለቤቱ ያልበላውን ሀብት ወራሾች እበላለሁ ብለው የሚጋደሉበት ነው። ዓለም ብላሽ ነው፣ በእልልታ አግብተው በኡኡታ የሚኖሩበት ነው። ዓለም ብላሽ ነው፣ በፍቅር ጀምረው በመጋደል የሚፈጽሙበት ነው። ዓለም ብላሽ ነው፣ እየለመኑ የገቡ ፣ እየተሳደቡ የሚወጡበት ነው።
በዚህ ዓለም ላይ የተሰጠን ነገር ሁሉ የመንገድ አበል ነው፣ ዋናው ደመወዝ በሰማይ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ተልእኮ አለን። አደራችንን የምናስረክበው በሰማይ ነው። ጡረታ ስለ ወጣን ጨረስን ማለት አይደለም። አታስፈልጉም ስለ ተባልን የእኛ ነገር አበቃለት ማለት አይደለም ። እስከ ሕይወታችን ሕቅታ ድረስ ሥራ አለን። ዋጋ ከፋዩ እንደ እኛ ዋጋ ጠባቂ የሆነው ሰው አይደለም። ከሰው መጠበቅ ያስቀመጠንን ጌታ አለማወቅ ነው። ለመኖር እንጀራ እንደሚያስፈልግ ራእይም ያስፈልጋል። አበሉን እንደ መጨረሻ ደመወዝ ማየት ዋጋን ማሳነስ ነው። በሰማይ የዘላለም ሕይወት፣ የሕይወት አክሊል፣ የጽድቅ አክሊል ይጠብቀናል። የዘላለም ሕይወት ላመኑ፣ የሕይወት አክሊል ትሩፋት ለሠሩ፣ የጽድቅ አክሊል ወንጌልን ላገለገሉ ይሰጣል።
ዓለም ብላሽ ነው። ሰው ሲሞት ወደ እውነተኛው ቦታ ሄደ ይባላል። ይህ ዓለም ውሸት ነው። ውሸት ልብን አያሳርፍም። በጥንት አይሁድ ትውፊት ዓለም ስምንት ሺህ ዓመት ሲሞላት ታረጃለች ይባል ነበር ። ዓለም አርጅታ በቅባት ብዛት ተኳኩላ ቀርባለች። ዓለም በምርኩዝ ገብታለች። መሬቱ እንኳ ያለ ጉቦ ያለ ማዳበሪያ አያበቅልም። አዎ አዲሲቱን ዓለም እንጠብቃለን። ከአራዊት ዓለም በጉ ወደሚያስተዳድራት ዓለም እንሸጋገራለን።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም.