ዓለም ከንቱ ባትሆን፣ አብባ ባትረግፍ ፣ ታይታ ባትጠፋ ይቆጭ ነበር ። እነዚያን ወገኖቻችንን ለምን ሞቱ ? ብለን አዝነን ባላባራን ነበር ። ዓለም ከንቱ መሆንዋ ሰማይን እንድንናፍቅ አደረገን።
አዲስ ነገር በዓለም ላይ የለም። ሊድርህ የመጣው ሰው ሊቀብርህ ይሰበሰባል። ስትዳርም ያንተን ድግስ አትበላውም፣ ስትሞትም በስምህ የተደገሰውን አትቀምሰውም። የሕይወትህ መግቢያና መውጫ የዓለም ጉዞህ ተመሳሳይ ነው። ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ የእግዚአብሔር ሆኖ ተወልደሃል፣ ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ የእግዚአብሔር ሆኖ በሞት ትወሰዳለህ። ስትወለድ ምጥ ነበረ፣ ስትሞትም ጣር አለ። ስትወለድ ሰዎች ተሰብስበው ማርያም ፣ ማርያም ይሉ ነበር። ስትሞትም ሰዎች ተሰብስበው በሰላም ያሳርፈው እያሉ ይለምኑልሃል። ስትወለድ እትብቱን ይቆርጡልሃል፣ ያን ቀን እናትህ ስለቱን አትይዘውም፤ ስትሞትም ይገንዙሃል፣ አሁንም እናትህ አትቀርብህም። ስትወለድ ወንድ ተወለደ ብለው ጥይት ይተኩሳሉ፣ ስትሞትም ኧረ ጀግናው ሄደ እያሉ ጥይት እንደ በቆሎ ያረግፋሉ።
ስትወለድ አታውቅም ነበር፣ ስትሞትም ምን እየተከናወነ እንዳለ አታውቅም። ስትወለድ እንኳን ማርያም ማረችሽ ያሏት እናትህን ስትሞት እግዚአብሔር ያጽናሸ ይሉአታል። ስትወለድ ለራስህ ታለቅስ ነበር፣ ስትሞት ሌሎች ላንተ ያለቅሳሉ። ስትወለድ ዛሬ የምትጋደልለትን ቋንቋ አታውቅም ነበር፣ ስትሞትም ቀድሞ አንደበትህ ይያዛል። ስትወለድ ሰዎች ከመሬት አንሥተው ተሸክመውሃል፣ ስትሞትም ሰዎች ተሽክመው ወደ መቃብር ይወስዱሃል። ስትወለድ ማንንም የማትጎዳ ምስኪን ነበርህ፣ ስትሞትም ማንንም የማትጎዳ ምስኪን ትሆናለህ።የተቀየሙህም ይቅር ይሉሃል። ሙት አይወቀስ ድንጋይ አይነከስ ብለው ስላንተ ደግ ደጉን ብቻ ያወራሉ። ስትወለድ ዕራቁትህን ነበር ፣ ስትሞትም ዕራቁትህን ትሄዳለህ። ስትወለድ ወደ ሐሰተኛው ዓለም መጣህ፣ ስትሞት ወደ እውነተኛው ዓለም ትሄዳለህ።
ስትወለድ ወላጆችህ አያውቁህም ነበር፣ ስትሞት እንሸኝህ ብለው አይከተሉህም። ስትወለድ አምባሳደር ሆነህ መጥተሃል፣ ስትሞት ወደ አገርህ ተጠርተሃል። ስትወለድ ከልደትህ በፊት የሚያውቅህ እግዚአብሔር ነበረ፣ ስትሞትም ሰማይን የሚያወርስህ እርሱ ብቻ ነው። ስትወለድ ራስህን አትከላከልም ነበር፣ ስትሞትም ቢያቃጥሉህ እንኳ አትቆጣም። ስትወለድ ዓይኖችህ ሰው አይገላምጡም ነበር፣ ስትሞትም ማንንም አትበድልም። ስትወለድ ያንተ ያልሆነ ቤት ገባህ፣ ስትሞት ያንተን ንብረት ለቀሪው ትተህ ትሄዳለህ። ስትወለድ በትንሽ ጨርቅ ተጠቅልለህ ነበር፣ ስትሞትም በትንሽ ሳጥን አሸገው ከቤትህ ያወጡዋል። ስትወለድ ካህናት ሊያጠምቁህ ይጠብቁ ነበር፣ ስትሞትም ሊጸልዩልህ ይመጣሉ ። ስትወለድ ያዩህ ሞትህን ሲሰሙ ያዝናሉ።
ልደትህ ሞትህን ያያል፣ ሞትህ ልደትህን ያስታውሳል። ከተወለድህ ቀን አንሥቶ ወደ ሞት እየተጓዝህ ነው። የልደት ቀንህን ስታከብር ዕድሜህ የተጨመረበት ብቻ ሳይሆን ዕድሜህ የተቀነሰበትን በዓል እያከበርህ ነው።
አንተ ወገኔ !
ሁሉን ትትህ ትሄዳለህና በሁሉም ነገር አትጨነቅ። ዓለምን ከኋላህ ፣ ክርስቶስን ከፊትህ አድርገህ ትሄዳለህና ሌላውን ቀምተህ አዳሪ አትሁን። ሌላውን እየቀብርህ አንተ የምትቀር መስሎህ አትስገብገብ ። ለማትኖርበት ዓለም ሰብስበህ ወደምትኖርበት ሰማይ ባዶ እጅህን እንዳትሄድ ተጠንቀቅ። ዘመኑ አልቋልና ወደ ጌታህ ዕቅፍ ለመግባት በንስሐ በሥጋ ወደሙ ፍጠን! ለእኔም ጸልይ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም