የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመታዘዝ ፍቅር (ማቴ.10÷5)

                   ቤተ ጳውሎስ፤ ማክሰኞ ሰኔ 30 2004 ዓ.ም.
ሰባኪው በዛሬ ዘመን ፍቅር ጠፋ ካለ በኋላ ምን ፍቅር ብቻ ጠብም ጠፋ አለ ይባላል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር ሽንገላ ሆኗልና፡፡ ተጣልቼሃለሁ ማለትም ፍቅር ነው፡፡ በዘመናችን ግን ሁሉን ነገር በጥርስ ያልቃል፡፡ ታዲያ የጠፋው እረኛ ብቻ ይሆን? በግስ አለ ወይ?
አንድ ሰው እንዲህ አለ፡- ‹‹ዘመናዊው ዓለም ትእዛዙን ያለዋወጠው ይመስለኛል፡፡ ልጆች ለወላጆቻቸው ይታዘዙ ሳይሆን ወላጆች ለልጆቻቸው ይታዘዙ፡፡›› በጊዜያችን ልጆች ወላጆች ስላታዘዟቸው ይቆጣሉ፡፡ ወላጆቻቸውን የሚወዱት ፍላጎታቸውን እስካሟሉ ድረስ ነው፡፡ ስለዚህ ወላጆች ወልደው አሳድገው ፍሩን እየተባሉ ነው፡፡ የልጆች ድምጽ በሚሰማበት በተባረከው ዘመናችን የልጆች ጆሮ የተደፈነበት እንዳሆን መጸለይ ያስፈልገናል፡፡ ልጆች ‹‹እምቢን›› በክትባት መልክ የወሰዱት እስኪመስል የየቤቱ ክፉ ቋንቋ ሆኗል፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር ትክክል ነው የምንለው የልጆች አሳብ ዓመታት በተቆጠሩ መጠን ትክክል አንለውምና ከወዲሁ ማሰቡ ጥሩ ነው፡፡ እኛ በወላጆች የተጎዳን ከሆንን በተራችን ደግሞ በልጆች እንዳንጎዳ ማሰቡ ደግ ነው፡፡ ልጆቻችን እሺ ስለማይሉ በሰለጠነው አመለካከታችን ‹‹መቅጣት የለብንም፣ እሺ እንዲሉ ማስረጃ ማቅረብ አለብን›› እንላለን፡፡ አዎ ይህ ንግግራችን በረከት ራቀን ከማለት ተለዋጭ ንግግር ሆኖልናል፡፡ በእውነት ያለጉቦ የሚላኩ ልጆን እናገኝ ይሆን? ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት የሚል ልጅ አይተን ይሆን? አዎ እኛ ለእግዚአብሔር ያሳየነውን ልጆች ለእኛ እያሳዩ ከሆንስ ምን እንላለን?

የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አሥር ቁጥር አምስትን ሳነብ የመጀመሪያዎቹን ቃሎች አልፎ መሄድ የማይሆን ሆነብኝ፡፡ የዘመናችንን ክርስትና የሚጠይቅ ድንቅ ቃል ነው፡፡ ‹‹እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው÷ አዘዛቸውም›› (ማቴ.10÷5)፡፡
በደስታ የሚላክ የሚታዘዝ ሰው ፍቅሩ ፍጹም ነው፡፡ መላክና ማዘዝ የሚፈጸመው በላኪውና በሚልካቸው መካከል ፍቅር ፍጹም ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ትዕዛዝን አስደሳች የሚደርገው የምንቀበልበት ልብ ነው፡፡ ሊቀ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ፍቅር ብቻ በድካም የሚሠራውን ያለ ድካም እንዲሠራ ታደርጋለች›› ብሏል፡፡ ሴትዬዋ ልጁን እዚህ ቦታ ሄደህ ይህን አድርገህ ና›› ቢሉት እሺ ብሎ ወጣ፡፡ ሲዞር ውሎ ማታ ላይ ‹‹ደርስህ መጣህ ወይ?›› ቢሉት አልሄድኩም አለ፣ ለምን ቢሉት ‹‹ሳስበው ሳስበው ደካመኝ›› አለ ይበላል፡፡ ዛሬም በእግዚአብሔር ቤት በጉልበታቸው ያረገዙ ሲያስቡት የደከማቸው በዝተው ይሆን?
ብዙዎች ‹‹ክርስትና ከባድ ነው›› ይላሉ፡፡ መቼም ክርስትናን በክብደት የሚያሳየን ጠላት ነው፡፡ ሁለት ሺህ የሕግ ዝርዝሮችን አንድ ሺህ የሽማግሌ ወጎችን የተሸከሙ ሙሴና ተከታዮቹ እንኳ ምን ይበሉ? እኛ ይህ ሁሉ ቀንበር ተነሥቶልን ክርስትና ከባድ ነው እንዴት እንላለን? ማመን ከከበደን አዎ ክርስትና ከባድ ነው፡፡ ማስረጃ ካለን ግን እምነት ቀላል ነው (ማቴ.11÷28-30)፡፡
እግዚአብሔር አብ እግዚብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ በክብር የተካከለ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድን ልኮታል፣ ለመስቀል ሞት አዞታል፤ እግዚአብሔር ወልድም መንፈስ ቅዱስን ልኮታል፣ ለሚያምነብት ሁሉ ናኝቶታል፡፡ በሥላሴ መንግሥት መላክና ማዘዝ ደግሞም መታዘዝ ፍቅር እንጂ ብልጫነት አይደለም፡፡
በዚህ ዓለም ክብር ምስጋና ያለው ማዘዝ ሳይሆን መታዘዝ ነው፡፡ ጌታም ‹‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ›› አለ (ዮሐ.14÷15)፡፡ ትእዛዙ ፍቅር ናት፣ ፍቅርም የትእዛዝ ፍጻሜ ናት፡፡ መታዘዝ እውነተና የሚሆነው ከፍቅር ሲመነጭ ብቻ ነው፡፡ ከፍቅር የሆነ መታዘዝ አይደክምም፡፡
ዛሬ በቤተክርስቲያን እረኛ ብቻ ሳይሆን መንጋም እየጠፋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የዘመናት ችግር ቤተክርስቲያንን የሚመራው ሕዝቡ ነው፡፡ ይህን እናስተካክል የተባለ እንደሆነ ‹‹ሕዝቡ›› ይባላል፡፡ አማኞች በዛሬው ዘመን እረኛ አይፈልጉም፡፡ አራዊት ጠባቂ አይፈልጉም፣ በጎች ግን እረኛ ይፈልጋሉ፡፡ ደፍረን የምንልካቸውና የምናዛቸው በጎች ከጠፉ የቤተክርስቲያን ህልውና ያሰጋል፡፡ ውድ አንባቢ ሆይ! ሰው ሲያዝ ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ሲያዝ ልብን ያያል፡፡ ሰው ሲያዝ ብቃትን ያያል‹ እግዚአብሔር ሲያዝ እምነትን ያያል፡፡ ሰው እውቀትን ያደንቃል፣ እግዚአብሔር እምነትን ይባርካል፡፡ እኛስ እንታዛዝ ይሆን?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ