እግዚአብሔር ሆይ ብርሃናት ብርሃንነትህን ፣ ፍቅሮች ፍቅርህን ፣ ቸርነቶች ቸርነትህን አያህሉትም ። ባለ መጥፋት የምትኖር ፣ ባለ መታጣት የምትገዛ ፣ ባለ መናወጥ የምትገኝ ፣ ባለ መሰሰት የምትሰጥ ፣ ባለ ማበደር ጸጋን የምትቸር ፣ ያለ ግዴታ የምትወድ አንተ ነህ ። እኔማ የጨበጥሁትን ስለቀው ፣ የለቀቅሁትን ስይዘው ፤ ያወደስሁትን ሳራክሰው ፣ የረገምሁትን ስቀድሰው ፤ የሸኘሁትን ሳሳድደው ፣ አሳድጄ የያዝሁትን ስሰለቸው ፤ ያቀፍሁትን ስገፈትረው ፣ የገፈተርሁትን ሳቅፈው ፤ አበባ የሰጠሁትን አፈር ስበትንበት ፣ ትቢያ የረጨሁትን ወርቅ ሳለብሰው የምኖር ፣ እኔ እኔን መልመድ ያቃተኝ ፍጡርህ ነኝ ። እኔ እኔን ሳላውቀው ለብዙ ዘመን እኖራለሁ ። እኔ አንተን ብሆን ኖሮ እኔን አልፈጥረውም ነበር ። እኔን እኔ ስጠላው አንተ ግን እኔን ወደድኸው ። በነፋሱ አቅጣጫ እንደ ባንዲራ እውለበለባለሁ ። ይሙት ሲባል ከሰማሁ ይገደል እላለሁ ። አቋምና አቋቋም ያጣሁትን ልጅህን በመልካም አስበኝ ። ኖሬ ካልሞትሁ ሞቼ እኖራለሁና እባክህ አግዘኝ ። ማደሪያ ቤቴ ፣ መተዳደሪያ ቀለቤ አንተ ነህ ። ያለፈውን በረከት አድፋፍቼ ዛሬም ስለምንህ ሂሳብ እንተሳሰብ ሳትል ትሰጠኛለህ ። የማትቀየም አንተ ብቻ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 10 ቀን 2014 ዓ.ም.