የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰማዕት ያለ

እውነተኛ ጠፍቶ እንጂ ዛሬም ሰማዕትነት አለ ፡፡ ሰማዕትነት ቆሞ አያውቅም፡፡ ሰማዕታትም በጣም ይቀንሱ ይሆናል እንጂ ጠፍተው አያውቁም ፡፡ የነጻነት ዘመን የመሰለው ከጽድቅ ነጻ ለሆኑ ክርስቲያኖች ፣ በሁለት ወገን በእውቀትና በመንፈሳዊነት ለመከኑት ነው ፡፡ ስለጸኑት ስታስብ ትጸናለህ ፡፡ ስለ ሰማዕታት ስታነብ ብዙ እንደ ቀረህ ታውቃለህ ፡፡ ስለ ጻድቃን ስታነብ የገንዘብ ፍቅርን ትጠየፈዋለህ ፡፡ እመን ፣ አትመን የሚል ሙግት በአደባባይ ባይኖርም በእያንዳንዱ ቀን ካልወሰንህ ክርስቶስን መከተል አትችልም ፡፡ በዋጋ የመጣው ሃይማኖት ያለ ዋጋ አይቀጥልም ፡፡ ሃይማኖት ለእኛ መሰከረች እኛም ለሃይማኖት እንመሰክራለን ፡፡ ያለ እግዚአብሔር ከመኖር ከእግዚአብሔር ጋር መሞት ይሻላል ፡፡ የእምነት ጀግኖች አምነው የኖሩ ብቻ ሳይሆኑ አምነው የሞቱም ናቸው ፡፡ እምነት ሕያው ነውና “ነበር” አይስማማውም ፡፡ መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት ዓለምን መናቅ ፣ የመንፈስ ቅዱስን መጽናናት ለመውረስ ስለ ኃጢአት ንስሐ መግባት ይገባሃል ፡፡ ዓለሙ የሚያከብርህ ዓለምን ስትንቅ ነው ፡፡ ዱርዬና ዓለም አክባሪያቸውን አይወዱም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህ የሚታወቀው የተጣሉትን ስታስታርቅ ነው ፡፡
እግዚአብሔርን ስትክድ ዓለሙ ያምንሃል ፡፡ ዓለሙን ስትክድ እግዚአብሔር ያምንሃል ፡፡ አስመሳይነት ዳሩ ገነት ውስጡ እሳት ነው ፡፡ እውነተኛነት ዳሩ እሳት ውስጡ ገነት ነው ፡፡ እግዚአብሔርን የከሰርክበት ማንኛውም ድል ሽንፈት ነው ፡፡ መትረፍ ማለት ከመኪና አደጋ ማምለጥ ሳይሆን የነፍስህን ቤዛ ማወቅና ማመን ነው ፡፡ የዕድር መዝገብ አውቆህ የሕይወት መጽሐፍ ካላወቀህ ከሁሉ ይልቅ ምስኪን ነህ ፡፡ እንደ ጴጥሮስ በልቤ አምኜ በአፌ እክዳለሁ አትበል ፡፡ ምስክርነት በአፍ እንደሆነ ክህደትም በአፍ ነውና ፡፡ እንደ አርዮስም በልብ ክደህ በአፍህ አትመን ፡፡ ይህ መዋረድ ነውና ፡፡ ለራስህ ክብር ካለህ በእምነትህ ጽና ፡፡ በሃይማኖት ውስጥ የሚታመነው አንዱ እግዚአብሔር ፣ የዘላለሙ አዲስ ነውና ሃይማኖት አይታደስም ፡፡ እናድሳለን እያሉ ከሚያቆሽሹ ፣ እናምናለን እያሉ የከበሩትን ከሚያዋርዱ ተጠንቀቅ ፡፡
ሃይማኖት ራሱ ገንዘብ ነውና በሃይማኖት ገንዘብ አትመኝ ፡፡ ስለ ሰው ሞተሃል ፣ ስለ እግዚአብሔር ኑር ፡፡ ሰዎችን ላለማስቀየም ጠጥተሃል ፣ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ሥጋና ደሙን ተቀበል ፡፡ መከራ ሳይመጣ የሚያስክዱ መናፍቃን ናቸውና ተጠንቀቅ ፡፡ መናፍቅነት እውነት የተቀባ ውሸት ነው ፡፡ አረማውያን የሆኑ ነገሥታት ሰይፍ ቢያነሡ ሰማዕታትን አበዙ ፡፡ መናፍቃን ግን ብዙ አማንያንን አስካዱ ፡፡ መናፍቅነት አለሁ እያሉ መሞት ነው ፡፡ እውነቱ እውነት ስለሆነ እንጂ ስለሚያመጣው ውጤት አትከተለው ፡፡ እግዚአብሔር ከዛሬው መከራ ያድናል ፣ ባያድነንም እርሱ እግዚአብሔር ነው ፡፡ ከአረማውያን የወርቅ መቅደስ ይልቅ የጌታ ሥጋና ደም የሚፈተትባት የሣር ክዳን ቤተ ከርስቲያን ትበልጣለች ፡፡ እውነት በሌለበት ሰማዕትነት የለም ፡፡ ዛሬ ሰማዕታትን ገሸሽ ብሎ እውነትን ራሷን ለመሰየፍ ትግል ያለን ይመስላል ፡፡ እውነተኞች እንጂ እውነት ግን አትታሰርም ፡፡
እንግዳ ሲመጣ የሚበሳጭ ሰው ሦስት ነገሮች የጎደሉት ነው ፡፡ አንደኛ፡- ቤቱን ማስተካከል ያቃተው ፤ ሁለተኛ፡- የሚያቀርበው በረከት የሌለው ፤ ሦስተኛ፡- ፍቅርን የተራቆተ ሰው ነው ፡፡ ሞት ሲመጣም የሚሸበር ንስሐ ያልገባ ፣ በጎ ያልሠራና በፍቅር ያልኖረ ሰው ነው ፡፡ ሞት ከአሮጌ ቤት ወጥቶ አዲስ ዓለም መውረስ ነው ፡፡ ከጠባብ እስር ቤት ወጥቶ በሰፊው ዓለም መንገሥ ነው፡፡ የምትወደውን ሰው በሰማይ ለማግኘት ከፈለግህ ዛሬ ቃለ እግዚአብሔርን ንገረው ፡፡ ዛሬ እንደሚሞት መዘጋጀት ፣ ዘላለም እንደሚኖር መሥራት ይገባሃል ፡፡ በአባት የተገደሉ በዓለም ላይ አሉ ፡፡ ክርስቶስ ግን የሞተልህ አባትህ ነው ፡፡ አባት ሲጠላ እናት ማማጸን ይቸግራታል ፣ እግዚአብሔር ግን ከጠላትና ከወዳጅ ባላጋራ ይጠብቅሃል ፡፡
ዛሬ ለወንድምህ የምትናገረውን ክርስቶስ በፊትህ ቢቆም የምትናገረውን መሆን አለበት ፡፡ ክርስቶስ መንገድ ቢጠይቅህ እንዴት ብለህ ታመለክተዋለህ ? መንገድ የጠፋውን ሰው እንደዚህ አግዘው ፡፡ ለክለሳ ተመልሰህ አትመጣምና ዛሬ በጎ ተግባር ፈጽም ፡፡ የተዋረደ አስተሳሰብ ካላቸው ጋር የተከበረ አሳብህን ይዘህ አትከራከር ፡፡ ያለ አጥር ያደገን ሰው ሥነ ሥርዓት ማስያዝ አስቸጋሪ ነው፡፡ “ከጥሬዎች ጋር አብረን እየዋልን ፣ እነርሱ እስኪበስሉ እኛ ተቃጠልን ” የተባለው ለዚህ ነው፡፡ ወላጁ ያለፋበት ሕጻን ቤተ ክርስቲያንና አባቶችን የሚያደክም ወጣት ነው ፡፡ ከወፈፌ ተጠንቀቅ ፣ መቼ እንደሚያብድ አታውቅምና ፡፡
ሰዎች ሲረግሙህ እግዚአብሔር ይመርቅሃል ፡፡ ተወድደህ ከነበረህ በረከት ተጠልተህ የምታገኘው በረከት ይበልጣል ፡፡ ማንም ሳይመክርህ ሕይወትህ ከታረመ ፣ እግዚአብሔር መምህርህ ነበረ ፡፡
የደስታ ቋሮ/14
 
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 11/2010 ዓ.ም.

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ