የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰውን ያህል አለማክበር

እርጉዞች ሕይወት ተሸክመዋልና ቀጣይ ትውልድንም እያሸጋገሩ ነውና በጣም የተከበሩ ናቸው። ሕይወት ለመስጠት እናት መሞት የለባትም ተብሎ ትልቅ ዘመቻ ተደርጓል። በወሊድ የሚሞቱ እናቶች ቁጥርም ቀንሷል። እርጉዞች ያማራቸው ነገር ይቀርብላቸዋል ። አምሮአቸው ካልተደረገላቸው በፅንሱ ላይ ሽታ የሚባል ምልክት ይወጣል እየተባለ በተለምዶ  ይነገራል።  በሰለጠነው ዓለም በሕዝብ መጓጓዣ አውቶብስና ባቡር ላይ የእርጉዝ ሴት መቀመጫ ተለይቶ ተሠርቷል። በዚህ ወንበር ላይ ማንም አይቀመጥም። እርጉዝ ሴት ብትነጫነጭ ማንም አይሰለቻትም ፤ ብታዝዝ ማንም አይለግምባትም። ኃይለኛ ባል በዚህ ወቅት ይለዝባል። ኃይለኛ ጎረቤትም ሁለት ነፍስ ናት ብሎ ያዝንላታል። እርጉዝ የተሸከመችው ፅንስ ለአገርና ለዓለም የሚተርፍ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ሊሆን ይችላል።

በየትኛውም ዘመን ለእርጉዝ ክብር ይሰጣል። የምትቀና  ሴት ባልዋ እርጉዝ ሴት በመንገድ ላይ ቢያግዝ ደስተኛ ናት። እርጉዝ በልዩ ዓይን የምትታይ፣ መኪና የያዙ የማያቋርጧት ክብርት ናት። ጌታችን ሊወለድ ሲል ግን ድርስ እርጉዝ የሆነችው እመቤታችን ሁሉ በር ዘጋባት። ሰዋዊ ባሕል፣ ሰብአዊ ርኅራኄ ክርስቶስ ጋ  ሲደርስ ቆመ። በዚያ የብርድ ወራት፣ በዚያ የቀን ጨለማ በሆነ ክረምት በበረት ተወለደ።  የሰውን ያህል እንኳ አላከበርነውም። ወንጌላዊ ዮሐንስ ይህን ታዝቦ፦ “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” አለ። (ዮሐ.1፥11) ። እርሱ በሥጋ ከእስራኤል ወገን መጣ እስራኤል ከበረት እስከ መስቀል አልተቀበሉትም ። እርሱ ፍጹም ሰው ሆኖ መጣ ፣ የሰው ልጆች አልተቀበሉትም።

ተቀባይነት ማጣት ሕመሙ ከፍ ያለ ነው። የገዛ ወገናቸው ያልተቀበላቸው ባዕድ ግን ያከበራቸው ብዙ ሰዎች አሉ። በአገራቸው አሸባሪ ተብለው በሌላ ዓለም አስተማሪ የሚባሉ አያሌ ናቸው።  ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር የታወቀ ነው። ነቢይ በገዛ ዘመኑም አይከበርም። ህልውናቸውን ሳይሆን መቃብራቸውን ያከበርንላቸው አያሌ ናቸው። ያን ጊዜ ፀፀት ይሆናል የማይጠቅም ፀፀት ነው። የሰው ልጅ ሲፈጠር በአእምሮ ጠባይ ፣ በመጻሕፍትና በመምህራን እንዲማር ሁኖ ነው። ሞት የሚያስተምረን እየገረፈ፣ በፀፀት እሳት እየለበለበ ነው። እርጉዞች ምን አማራችሁ? ይባላሉ ፣ እመቤታችን ይህን አላገኘችም። ክርስቲያን መብቱን ፣ የዜግነቱን  ክብር፣ የቤተሰብን ፍቅር፣ የወገንን  አንቱታ ቢያጣ ክርስቶስን መሰለ ማለት ነው።

ሰባኪው የአንድ መምህርን ያህል ክብር ሊያጣ ይችላል። መንፈሳዊው አባት የሥጋ አባትን ያህል ተቀባይነት ሊነፈገው ይችላል። ክብር የሚያውቁ ሰዎች ክርስትና ጋ ሲደርሱ ማክበር ይሳናቸዋል። የሰዎችን ሃይማኖት የሚያከብሩ ቤተ ክርስቲያንን ማክበር ይቸገራሉ። በአውሮፓ ከክርስቲያን ይልቅ ሌላ ሃይማኖት ያለው ሥራ የመቀጠር ዕድሉ እየሰፋ ነው። የቡድሃ  ሃይማኖት መናንያንን የሚያከብሩ የክርስቲያን መነኰሳትን ለማክበር በጣም ይጨነቃሉ። ስለ ታላቁ እስክንድር ብጣሽ ወረቀት ቢገኝ ዓለም ሁሉ አውርቶ አይጨርስም ። ስለ መሢሑ ኢየሱስ ይህ ሁሉ መዛግብት እያሉ ማንም አያወራም። አዎ ለሰማይ የቀረበ ከምድር ይገፋል ። ይሉኝታ ያላቸው ለክርስቲያን ሲሆን ይሉኝታ ያጣሉ። የማይሳደቡ ጨዋዎች  ክርስትናን በድፍረት ይሳደባሉ። እግዚአብሔር የለም ብለው የሚናገሩ አላህ የለም ብለው አይናገሩም። መጽሐፍ ቅዱስን ሲተቹ የሚውሉ በነካ እጃችን ቁርዓንን እንንካ አይሉም።

ክርስትና ከዓለም ቀረብኝ ፣ ፍርድ ተጓደለብኝ የሚል የብሶት ሃይማኖት አይደለም። መገፋትን በትክክለኛ መንገድ ላይ የመቆም ምልክት የሚያደርግ ሃይማኖት ነው። ክርስቲያን  መግደልን ይፀየፋል፣ መሞትን ግን እንደ ዕድል ይቆጥረዋል። ሰማዕትነት እንዳያመልጣችሁ እያለ ይጠራራል።  አዎ መገፋት ወደ ክርስቶስ የመጠጋት ምልክት ነው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምቹ ኑሮ ፣ ጥሩ አሟሟት ያገኘ ጻድቅ የለም። ሐዋርያ ጳውሎስ፦ “በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት ፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው ፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤” ይላል (ፊልጵ .1፥28)

ለሰው የሚደረገው ለጌታ አልተደረገም ! ለሰው ያለንን ክብር ለጌታ አላሳየንም። ሲቸግርን ስንመጣ፣ ሲመቸን ስንጠፋ አንሳቀቅም። ስንት ጉድ ያስተናገደ  ቤታችን ክርስቶስን ለማክበር ፈቃደኛ አይደለም።

ጌታ ሆይ ወደ ራስህ መልሰን !
ይቀጥላል
#ዲያቆን #አሸናፊ #መኰንን
መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ