የዲያቆን አሸናፊ መኰንን … ሰኞ መስከረም 26 – 2007 ዓም
ቤተሰብህን ለማርካት የምታደርገው ድካም የበለጠ አለመርካትን ጨምሮባቸው ይሆን? የሌላውን ሰው ችግር በቀላሉ የምታየውን ያህል የቤተሰብህ ችግር ትዕግሥት ነስቶህ ይሆን? ከየቤቱ አንድ አንድ ሞገደኛ መኖሩ ገርሞህ ይሆን? ሰዎች ያደርጉልህ መልካም ነገር የሕሊና ዕዳ ሆኖብህ ይሆን? የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ዘጠኝን ስትጀምር ምላሹ ተቀምጦልሃል፡፡
ሌሊትና ቀን ከአልጋ የማይወርድ ጣራ ከማየት የተሻለ ምንም የማያይ አንድ ሽባ ሰው ወደጌታ እንዳመጡት ይተርክልናል፡፡ ይህ ሰው በቤት መቅረቱ የቤተሰቡን ደስታ ሳያጨልመው አልቀረም፡፡ እቤት ላሉት ሴቶችና በደጅ ለሚውሉት ወንዶች የዚህ ሰው በቤት መዋል በቀን ውስጥ ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን ያስተክዛቸዋል፡፡ ጉብዝናው በሽባነት አቅም አልነበረውም፡፡ አልጋው ለእርሱ ወንበሩ፣ መኝታው፣ የምግብ ጠረጴዛው፣ ሜዳው…ሁሉም ነበር፡፡ የአልጋ ቁራና መሆኑ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቹ የተሸከመውን የሚሸከመው በኢየሱስ ክርስቶስ ፈውስ ሲነካ መሆኑን አመኑ፡፡ ስለዚህ ከእነአልጋው ተሸክመው ወደ ጌታ አመጡት፡፡ ጌታ የነበረበት ቤት ግን በሰው ተጨናንቆ ስለነበር እርሱን ማግኘት በፍጹም አልቻሉም፡፡ ክርስቶስን ለማግኘት በሩ ቢዘጋ ጣራ መንቀል ሕጋዊ እንደሆነ ተሰማቸው፡፡ በሩን የያዙት የዘመኑ የሃይማኖት መሪዎች ፀሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ (ማር.2÷4)፡፡
እነዚህ ሰዎችም የቤቱን ጣራ አንሥተው ሽባው የተኛበትን አልጋ በገመድ በማውረድ በጌታችን ፊት አቀረቡት፡- ኢየሱስም በእምነታቸው ተደነቀና ‹‹አንተ ልጅ÷ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ›› አለው፡፡ ከሃይማኖት መሪዎችም አንዳንዶቹ ከአንዱ ከእግዚአብሔ በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው አሰቡ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እግዚአብሔ ስለነበር ይችላል፡፡ ኢየሱስ ግን ‹‹ኃጢአት ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ፡- ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?›› አላቸው፡፡ ሽባውንም፡- ተነሣ አልጋህን ተሸከምና ወደቤትህ ሂድ አለው፡፡ ሕዝቡም በመደነቅ ለሰው እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔን አከበሩ (ማቴ.9÷8)፡፡
ጌታ ኢየሱስ የሥጋን ፈውስ ሳይሆን የኃጢአቱን ስርየት ነገረው፡፡ ለምን? ነፍሱ ከተፈወሰች ሌላው ችግር ሁሉ ቀላል ነውና፡፡ ደግሞም ትልቅ በሽታ ኃጢአት ነው፣ ኃጢአት በሽታን ሊያመጣ ይችላል፣ በኃጢአት የመጣው በሽታም ኃጢአት ሲሰረይ ሊሄድ ይችላል፣ ኃጢአት ሳይሰረይም የሥጋ ፈውስ ጥቅም የለውም፡፡ ጌታ ዘላቂውን ሕይወት ይናገራል፡፡ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ‹‹የመጨረሻውን ነገር ብቻ ለምን ነገርኸኝ፣ በመሐል ላይ የሚያጋጥመኝን ለምን አልነገርከኝም?›› ቢለው እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፡- ‹‹እኔ የማያልፈውን እንጂ የሚያልፈውን አልናገርም፡፡››
የሰው ልጅ የሚሆነው ማንነቱና ፍላጉቱ ያለው በማይታየው ነፍሱ ውስጥ ነው፡፡ በዓለም ላይ የሚታየው ነገር ሁሉ ነው፡፡ እንግዲህ እኛ አትርፈን የምንጨነቀው ግን ለ ነው፡፡ የነፍሳችን ጥያቄ በክርስቶስ ተመልሷል፡፡
እግዚአብሔ ሲያቆመን ለብዙዎች እንድንበቃ አድርጎ እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም፡፡ ያ ሰው ለብዙ ዘመን የተሸከመውን አልጋ እርሱም በተራው ተሸከመው፡፡ ለብዙ ዘመን የጠበቁንን፣ ለብዙ ዘመን በችግራችን የረዱንን እኛም በተራችን በበለጠ ፍቅር እንድንሸከማቸው ጌታ ይፈልጋል፡፡ የመዳናችን ውጤት ሌሎችን መሸከም መቻል ነውና፡፡
ሰው የሥጋ ፈውሱን እጂ ኃጢአቱን መስማት አይወድም፡፡ ላይ ላዩን የሆነ ግንኙነት እንጂ ውስጣዊ ኅብረትን አይፈልግም፡፡ ጊዜያዊውን እንጂ ዘላለማዊውን መስማት አይሻም፡፡ የኃጢአትን ይቅርታ ከመስማት የበለጠ ምን አለ? በዓለም ላይ ያሉት ጠበብቶች የነፍስን በሽታ መፈወስ አይችሉም፡፡ ከኃጢአት ሊያድን የሚችለው ብቸኛው የነፍስ ሐኪም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
የትኛው ይቀላል? የአየር መዛባትን ማውራት ወይስ ወደ በረከት አምላክ እጅ መዘርጋት? የትኛው ይቀላል ስለበሽታ መወያየት ወይስ ንስሐ መግባት? የትኛው ይቀላል? እውነትን ማገልገል ወይስ እውነትን እየሠዉ አንድ መሆን?