የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነፍስ ማዕበል

አባ ጳኵሚስ እንዲህ አለ፡- “የክፋት መጀመሪያ ሁከት ነው ።”
የሰው ልጅ ውድቀት የጀመረው ለሐሜት በር የከፈተ ዕለት ነው ሰይጣን እግዚአብሔርን ባማላት ጊዜ ሔዋን በዝምታ ሰማችው በዚህ ምክንያት ሐሜት መናገር ብቻ ሳይሆን መስማትም ሆነ ሐሜት እየሰፋ ይመጣልና አዳምንም ጋበዘችው ሐሜቱም ቅናትን ወለደ እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ጌታ ሁኖ እኛ እንዴት የምድር ብቻ ገዥ እንሆናለን የሚል ቅናት ተፈጠረ ቅናት ልቡናን ያሳውራልና ድፍረትን ወለደ በዚህም ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ የሰው ልጅ ሕይወትም በሁከት ተሞላ
ስለ እግዚአብሔር ቀና አመለካከት ባልያዝን ቊጥር ነፍስ በታላቅ ሁከት ውስጥ ትገባለች የነፍስ መታወክም በኃጢአት የመደሰት እልህ ውስጥ ያስገባታል የተከለከሉ ነገሮች ሁሉ ሌሎች ሲያደርጉት ሰላም ናቸው ፣ እኔ ብቻዬን እንዴት እረበሻለሁ ? የሚል ምክንያታዊነት ውስጥ ነፍስ መግባት ትጀምራለች ትጥቋን ጥላለችና በቀላሉ በጠላት ቀስት ትወድቃለች ሁከት የክፋት መጀመሪያ ነው
በራሱ ኑሮ ደስታ የሚሰማው ሰው ስለ ሌሎች ኑሮ ለማወቅ ፈቃደኛ አይደለም የሌሎችን ገመና እየሰማ መጽናናት የሚሻ ሰው ውስጡ የሚያሰቃየው ሰው ነው ሐሜት የሚወለደው ከሁከት ነው የእነ እገሌን ዘር ፣ ኑሮና ገቢ ካላወቅሁኝ ዕረፍት የለኝም የሚል የሐሜት ፆር እርሱ ትልቅ መታወክ ነው ሐሜት ማጉረምረምን ይወልዳል ማጉረምረም የአውሬ ድምፅ ነው የሚያጉረመርም ቀጥሎ ሊበላ ነው አጉረምራሚ ድምፁ የሚሰሙትን ሁሉ ያውካል የሚያጉረመርሙ ሰዎች “ቆይ” ፣ “አሳየዋለሁ” በማለት ለጥፋት ይነሣሣሉ ሐሜት እኔ ብቻ ተጎዳሁ ፣ ሁሉም በጥሩ እየኖረ ነው የሚል ሐሰተኛ መረጃ ስላለው ሰውን ሁሉ በመልካም ማየት አይችልም አዎ ሁከት ብቻውን አይታወክም ፤ ጎረቤትንም ያውካል
በዓለም ላይ የሚሆኑትን ነገሮች በሥጋዊ ሚዛን ብቻ መመዘን ሁከትን እየወለደ ይመጣል ይልቁንም በዛሬ ዘመን የሚሆኑት ነገሮች ግድ መሆን ስላለባቸው ነው ጌታችን በጣት ጠቅሶ የመንካት ያህል ስለዚህ ዘመን ነግሮናል ይህን ያህል ነግሮን እንዲህ ከታወክን ባይነግረን ምን ልንሆን ነበር ? ስግብግብነቱ  ፣ መጨካከኑ ፣ ፍቅር በወረት መተካቱ እነዚህ ሁሉ የመጨረሻውን ዘመን የሚያመለክቱ ናቸው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችም የመጨረሻው ዘመን ምልክት ናቸው እነዚህን ሁሉ ስናይ ከመታወክ ማስተዋል ይገባል ምላሻችን ሁከት ከሆነ ለጭንቀት እንዳረጋለን ቀኑን በድፍረት አምጪ ኪኒን ፣ ሌሊቱን ደግሞ በእንቅልፍ ኪኒን ለመግፋት እንዳረጋለን
ግድያዎች በዘመናዊው ዓለም የዕለት ዜና ናቸው ልጆች ቤተሰቦቻቸውን ፣ ወጣቶች ተማሪዎችን ፣ ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው እስከ ሞት ድረስ የሚጨካከኑበት አንዱ ምክንያት መበዳደል ስላለ ሳይሆን ሁከት ስለ በረታ ነው ሁከት የክፋት መነሻ ነው ሰው በእርጋታ ውስጥ ካልሆነ ከዚህ የእሾህ አጥር መውጣት አይችልም የሁከት ስሜቱ ሰውን እንዲጠላ ያደርገዋል ሌላውን ለመውደድ አስቀድሞ ራስን መውደድ ግድ ነውና የሁከት ስሜቱ ስለ ሰው መልካም እንዳይናገር ያደርገዋል የሁልጊዜ ተቺነቱ ውስጡን ሲቆረቁረው አክቲቪስት ነኝ ፣ እውነትን ራቁቱን የምናገር ነኝ እያለ ለራሱ የመዐርግ ስም ይሰጣል ጆሮ ተዘግቶ አፍ ሥራ ከበዛበት ይህ መታወክ ነው ሰው በሁከት ውስጥ ሲሆን እርሱን የሚመስል የታወከ ነገር ይፈልጋል ጸጥ ያለ ጉባዔ እንኳን አይፈልግም ሁሉም ነገር ጸጥ ሲል የልቡ ሁከት ለጎረቤቱ የተሰማበት እየመሰለው ይጨነቃል በግርግር አምልኮ ውስጥም ይደበቃል ያለ ዕረፍት መናገር ፣ ያለ ዕረፍት ስልክ ማውራት ፣ ያለ ዕረፍት ማገልገልም የሁከት ምልክት ሊሆን ይችላል ራስን በማዳመጥና ሰውነትን በማሳረፍ መውጣት ይገባል እንጂ እንዴት ይህ ነገር መጣብኝ በማለት መደነቅ አስፈላጊ አይደለም እግዚአብሔር ባይገድብልን የማይመጣብን ነገር የለም
አራዊት በቶሎ እርምጃ የሚወስዱብን የታወከ ፊት ካዩብን ነው ይህ ሰው ታውኳል ሊገድለኝ ይችላል ብለው ቀድመው ይገድላሉ በሁከት ውስጥ ያለ፣ ሰው አፍጥጦ ሲያየው ፣ አንድ ነጭ መከራ ረጅም ሰዓት ከተከታተለችው፣ አንድ ሰው ስልክ ደጋግሞ ከደወለለት መጠራጠር ይጀምራል ከጥርጣሬው ከመቶ አንድ ስለሚሆን ራሱን እንደ አዋቂ እየቆጠረ ይመጣል ከዚህ በኋላ ለራሱ ነቢይ እንደሆነ በማሰብ ትከሻዬ ደስ አላለውም እያለ በትከሻ አንቴና መመራት ይጀምራል ሁከት የክፋት መጀመሪያ ነው መባሉ እውነት ነው
የሰውን ስም ሲያጠፉ የሚውሉ ፣ በሰው ላይ ጭቃ መቀባት ሥራቸው የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ፣ በአካላቸው ላይ ሳይቀር የሚሳቀቁበት ነገር ያላቸው ሰዎች ናቸው ይህን የሥቃይ ስሜት የሚያልፉት ሌሎችን በማራከስ ስለሚመስላቸው ስም ሲያጠፉ ይውላሉ እነዚህ ሰዎች ላለባቸው ችግር ሐኪምን ቢያማክሩ መልካም ነው ዝም እንዲሉ ከመወትወት ጎደለን የሚሉትን ነገር እንዲታከሙ መርዳት ችግሩን ከሥሩ ይፈውሰዋል በዚህ ዘመን የራስ ኑሮም ፋታ አልሰጥ ብሎ ስለ ሰው ማውራት በሽታ ብቻ ነው አዎ እኔ ቆንጆ ነኝ ለማለት እገሌ አስቀያሚ ነው ማለት ተገቢ አይደለም የአስተዳደግ ቀውሶች ፣ የማንነት ጥያቄዎች ለብዙ ሰዎች የሁከት መነሻ ናቸው ሰው እግዚአብሔርን ሲያገኝ ብቻ ያለፈው ክፉ ታሪኩም ለበጎ ይሆንለታል
ያለ በቂ ዝግጅት መድረክ ላይ መሰየም ሁከት ይወልዳል ትምህርቱ ሲያልቅበት ስድብና ውግዘት ይጀምራል ድራማ እየሠራ ሲኮምክ ይውላል ስስ ልብ ያላቸውን በከንቱ ወሬ ይጠልፋል ከመንደር ነገረኛ የማይለዩ ሰባኪዎችን የምናፈራው በሁከት ምክንያት ነው የሰው ንስሐ መድረክ ላይ የሚያወሩ ፣ የሚሰማቸውን ሕዝብ የሚያንጓጥጡ ፣ ፍቅር የሌለው አብዮታዊ ስብከት የሚሰብኩ እነዚህ ሁከት የሚረብሻው ሰዎች ናቸው ያለ በቂ ዝግጅት ወደ ትዳር መግባትም ሁከትን ይወልዳል በቂ ዝግጅት የዕድሜም ፣ የኢኮኖሚም ፣ የእውቀትም ነው ብዙ ሰው ሚስት ሳይሆን የሚፈልገው እናት ነው ብዙዎችም ባል ሳይሆን የሚፈልጉት አባት ነው ሚስት እናት ፣ ባልም አባት መሆን አይችሉም ትዳር የጋራ ፍቅር ፣ የጋራ ጥረት ነው
ሌሎች መልካም ነገር ሲያገኙ ዓይናችን መቅላት ከጀመረ በእግዚአብሔር ፊት ወድቀን “ጌታ ሆይ ቅናት ቤቱን ሊሠራብኝ የመሠረት ድንጋይ እየጣለብኝ ነውና እባክህን አድነኝ” ማለት ተገቢ ነው ቅናት እንደ ቃየን ገዳይ ያደርጋል ከቤተ ክርስቲያን ጀምሮ ያለው ሁከት መነሻ ቅናት ነው በቅናት መጻሕፍትን አቃጠልን ፤ ውጤቱ ምን ሆነ ስንል፡- ሰውና ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃጥል ትውልድ አተረፍን ዛሬም መንቃት አልቻልንም መጻሕፍት ሲቃጠሉ ቀጥሎ ሰዎች ይቃጠላሉ
በሽታዎች የሚያመጡብን ሁከት አለ በሽታው ከሚጎዳን ይልቅ መጨነቁ ይጎዳናል ለዚህ ነው ግዴለሾች ብዙ በሽታ ይዘው በሕይወት አሉ የሚጨነቁት በትንሽ በሽታ ይሞታሉ በሽታው ከሚያሳጣን ነገር ጭንቀት የሚያሳጣን ነገር ይበልጣል ከሰዎች ጋር በልክ መኖር አለመቻልም የሁከት መነሻ ነው አንቺ አንተ እየተባባሉ የሚጣሉ ፍቅራቸው ቅጥ ያልነበረው ፣ በአንድ እጅ ካልጎረስን አንጠግብም ያሉ ናቸው እስከ ነገ የመዋደድ አሳብ ካለን ዛሬ መጨለጥ አስፈላጊ አይደለም ፍቅርን ከስሜት መለየት በጣም ወሳኝ ነው ስሜታዊ ፍቅሮች እያሉም ጭንቀት ፣ ሄደውም ብስጭት ናቸው ብቻ የአባ ጳኵሚስን ምክር እንደግመዋለን፡-
“ የክፋት መጀመሪያ ሁከት ነው ።”
ጸሎት
ከራሴ ይልቅ ራሴን የምትቀርበው ፣ እኔ ከምለው ይልቅ እኔነቴን የምታግዘው አንተ ነህ እኔ ጠፍቼ ሳለሁ አንተ በመገኘትህ እንዳልሞት አደረግኸኝ እኔ ፈርቼ ሳለሁ አንተ በድምፅህ አለሁ ብለህ አረጋጋኸኝ እልህ ከዓለም ጋር እንዳብር ስታደርገኝ አንተ ግን ወደ መንፈስ ቅዱስ ኅብረት መለስከኝ እግዚአብሔር ሆይ ተመስገን ሰይጣን በነፍሴ ላይ ከሚያመጣው ማዕበል መርከብ ሁነህ ጠልለኝ ያንተ ሰላም ይግዛኝ ለዘላለሙ አሜን
የበረሃ ጥላ 8
ሐሙስ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ