መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር /2

የትምህርቱ ርዕስ | የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር /2

የኢትዮጵያ ትውልድ መበላሸት ከጀመረ አራት ትውልድ እየሞላው ነው ። ጣሊያን ኢትዮጵያን ትቶ ሲወጣ አካሉ እንጂ መንፈሱ አልወጣም ነበር ። ኢትዮጵያም ከዳግም ወረራ የምድነው በምንድነው ( ብላ መክራለች ። በወቅቱ የተገኘው መልስ ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት አንዱ መዳኛ እንደሆነ ታመነበት ። ለሦስት ሺህ እና ከዚያም በላይ ለሚሆን ዘመናት ታሪክ ፣ ባሕል ፣ ትምህርት ፣ የመድኃኒት ቅመማ ፣ ምክር ፣ ሥነ ቃል ፣ ዜማ ፣ ፍልስፍና ፣ ሃይማኖት የነበራት አገር ምንም እንደሌላት ሆና የራስዋን ጥላ የሌሎችን ለመጨበጥ ተዘረጋች ። ውጤቱ የሌሎችን ላትይዝ የራስዋንም አጣች ። በልክዋ ፣ በግብረ ገብ ሚዛንዋ ያልተቀረጸው ዘመናዊ ትምህርት ከሀዲ ፣ ደፋር ፣ አዋራጅ ፣ ሃይማኖትን አርካሽ ትውልድን ፈጠረ ። መገዳደልም ባሕል ሆነ ። ደጁን ለማጽዳት ጉልበት የሚያንሰው ወገን ጦርነት መጣ ከተባለ ዳር ድንበር የሚዘምት ሆነ ። ትልቁ ጦርነት ድህነትን ማሸነፍ መሆኑን ረሳ ። ስለዚህ የውጭ ገዳይ ቢዘገይ የእርስ በርስ እልቂት ቋሚ ታሪካችን ሆነ ። የመገዛት ስሜትም ስለሌለ ፣ ሁሉም ሰው ራሱን እንደ ገዥ ስለሚያስብ ሰላም ብርቅ የሆነባት አገር ተፈጠረች ። የራስን እውቀት በመናቅ የጀመረው ጉዞ ፣ ለአገር ውለታ የዋሉ ሰዎችን በመጨረስ ቀጠለ ። የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ጣልያንን ያባረሩ አርበኞች ያለቁበት ነው ። በኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. በአንድ ቀን የተገደሉትና በአንድ ጉድጓድ ተቀብረው ኖራ የተነሠነሠባቸው ስድሳ ሚኒስትሮች ዓለምን ለመምራት አቅም የነበራቸው አዋቂዎች ነበሩ ። እናት ሕፃኑን አጥባ ከቆሻሻው ጋር አትደፋውም ፤ የፊውዳሉን ሥርዓት መጥላት ይቻላል ፣  በአገር ንብረት የተማሩ እነዚያን ሊቃውንትና የድሀ ልጆች መፍጀት ግን ትልቅ ኪሣራ ነው ።

የተማረው ትውልድ የቀለም አብዮት በመሰየም እርስ በርስ ተላለቀ ። የሞቱትም አይመለሱም ፣ ያለውም አይማርም ። አሰቃቂ የረሀብ ታሪካችን ዓለምን አስደንግጧል ። ንጉሡ ለልደት ቀናቸው ኬክ አስጋግረው አመጡ ፣ ወሎ ተርቦ እርሳቸው ልደት ያከብራሉ ተብሎ ዙፋናቸው ተነቀነቀ ። የፈረዱት አይቀርምና በ1977 ዓ.ም. ሰባት ሚሊየን ኢትዮጵውያን በረሀብ እንደ ቅጠል ሲረግፉ በእንግሊዝ ዋና ከተማ ሎንዶን ምግብ ይለመናል ፣ በእንግሊዝ ወደብ ላይ ግን ለዐሥረኛው የአብዮት በዓል ውስኪ ይጫን ነበር ። ፖለቲካችን መጠላለፍ ያለበት ፣ ሁልጊዜ ከአዲስ ለመጀመር እንጂ ሐረገ ትውልድ ያለው ሩጫ በፍጹም የሚፈልግ አይደለም ። በዚህ ምክንያት ብዙ ጅምር አንድ ፍጻሜ ያጣች አገር መሠረትን ። የመጣው ሁሉ ፀሐይ አወጣሁላችሁ ይላል ። ያለፈውን ጨለማ በማለት ይረግማል ። ለደርግ የጨፈረ ንጉሡን የረገመ ብዙም ሳይቆይ የጥይት እራት ሆነ ። ገበሬ ከባላባት ጭሰኛነት የመንግሥት ጭሰኛ ሆነ ። መሬት ላራሹ ተብሎ ግን ታወጀለት ። መሬት ሰጥተው ልጁን ለጦርነት መውሰድ ጀመሩ ። ንጉሡ በልጅ ኢያሱ ላይ ግፍ ፈጽመዋል ። ለ19 ዓመታት እንዲታሰር አድርገው ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ሲገባ ደብዛው እንዲጠፋ አደረጉ ። መቃብር ነሡት ። ለምን ነገሥህ ( ተብሎ ኢያሱ ተሰቃየ ። ንጉሡም መቃብር አጥተው የውሻ ሞት ሞቱ ። የኤርትራ ጉዳይ በጥበብ ስላልተያዘ ፣ የእሺታ መንፈስ ማሳየትና ማዳመጥ አለመቻል ያንን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን ሕዝብ አጣን ። ኤርትራን በእኛ ዘመን ወደ እናት አገር መለስን ለማለት ለታሪክ ሽሚያ ብቻ ያደረግነው ጉዞ መልሶ ለያየን ። በዚያም የተወለደው ወጣቱ ትውልድ አንድ መልክ ፣ አንድ ሃይማኖትና ቋንቋ ያለው ቢሆንም የቅርብ ሩቅ ሆነን ቀረን ።

በዚህ ሁሉ የታሪክ አዙሪት ውስጥ የሚወጣው ትውልድ የተቀመመ ክፋት መያዙ አያጠራጥርም ። ስለዚህ ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ትውልድ የችግር ውጤት ላይ ይገኛል ። የራሱን ችግር ዛሬ ሲጀምር ፣ የትላንትን ውጤት ደግሞ ዛሬ እየከፈለ ነው። ይኸው ወጣት አገርን ለመምራት ወደ መድረኩ እየወጣ ነውና ችግራችንን መለየት መፍትሔውን ማፈላለግ በጣም ወሳኝ ነው ።

አውቃለሁ ባይነት

የኢትዮጵያ ወጣት ታሪኩ ፣ ያለፈበት ጦርነት ፣ የሰማው ክፉ ነገር ፣ ያለማመድነው ጭካኔ ከጣለበት ጠባሳ አንዱ አውቃለሁ ባይነት ነው ፤ አውቃለሁ ባይነት አታላይ ነው ። አንዲት የአእምሮ ታማሚ የሆነች ሴት ሁልጊዜ ገንዘብ ልሰጣት ስል “በጣም ብዙ አለኝ ፣ ቤቱ ሙሉ እህል ነው” ትለኛለች ። እውነቱ ግን ልጆችዋ ይራቡ ነበር ። እርስዋም ከሰውነት ተራ ወጥታለች ። ልክ እንደዚህች ሴት በሌላቸው ነገር አለኝ የሚሉ ትውልዶች አውቃለሁ ባዮች ናቸው ። ሰው መንፈሳዊ እውቀት ሊኖረው ይችላል ። የእንጀራ መብያ እውቀትም ይኖረዋል ። የመረጃ እውቀትም አለው ። የቴክኖሎጂ እውቀትም ጊዜው ያመጣው ነውና ወጣቱ በቅርበት ያውቀዋል ። ከእውቀት የሚበልጠው ግን ሰው መሆን ነው ። ይህን እውቀት ወጣቱ እየከሰረው ይመስላል ። ሕይወቱን እንደሚጫወተው ጌም እያየው ነው ። አስፈላጊውንና ራሱን የሚያሳየውን እውቀት ለመስማት ስልቹ ነው ። የእኔ ጉዳይ አይደለም ብሎም ያልፈዋል ። በሚሄድበት መንገድ ክስረት ሲገጥመው ያለው አማራጭ ሞትን መመኘት ይሆናል ። መታገልን የሚፈራ ፣ ከራሱ ጋር ድብብቆሽ የሚጫወት ፣ ወላጆቹን አታውቁም ለማለት የሚደፍር ትውልድ መጨረሻው ያማረ አይደለም ። አውቃለሁ ባይነት ባለ አፍ እንጂ ባለ ጆሮ አያደርግም ። እንደ በቀቀን የሰሙትን መለፍለፍ እንጂ የተዋሐደውን ሐቅ የሚናገር እየጠፋ ነው ። ሁሉንም ነገር ወደ ቢዝነስ የመለወጥ የፍቅረ ንዋይ አምልኮ እየደራ ነው ። ያለፈው የኢትዮጵያ መንገድ እንዲህ ያለ ትውልድ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አድርጓል ። ትውልዱ አያውቅም የሚያውቅ ይመስለዋል ፣ አዋቂዎችንም ንቆና አሳዶ በር ዘግቶ ይኖራል ። የመከረውንም ሊቅ እንደ ጠላት ያያል ። አባቶች፡- “የማይማር መንፈስ አደገኛ ነው” ይላሉ ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም