መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር

የትምህርቱ ርዕስ | የኢትዮጵያ ወጣቶች ችግር

ወጣትነት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ጸጋ ነው ። ወጣትነት ኃይል ሲሆን መሪ የሚያስፈልገው ነው ። ወጣት ጉልበት ቢኖረውም መንገዱን አያውቀውም ። ፍላጎት ቢኖረውም ብልሃቱ ያንሰዋል ። ቅንዓት በውስጡ ቢቀጣጠልም ጥበብ ይጎድለዋል ። ወጣት መስጠት ይፈልጋል ፣ ያለው ጥሪት ግን አነስተኛ ነው ። ወጣት ዓለምን እቀይራለሁ ብሎ ይነሣል ፣ ዓለምን ለመቀየር ቀዳሚው ራስን መለወጥ መሆኑን ይረሳል ። ወጣት በራሴ ብቻ እቀጥላለሁ ብሎ ይፎክራል ፣ አንዱ ላንዱ መድኃኒት መሆኑን ይዘነጋል ። ወጣት ሁልጊዜ ትክክል መሆንን ይፈልጋል ፣ ፍጹምነት ግን የአንድ አምላክ ጠባይ መሆኑን ይረሳል ። ወጣት ምሬት ያበዛል ፣ መራራን ከማውራት ጣፋጩን ማቅረብ መፍትሔ መሆኑን ይዘነጋል ። ወጣት ምስጋና ያበዛል ፣ ፈጥኖ ለመራገም ይነሣሣል ። ሕፃናት ወጣት ይሆናሉ ፣ ሽማግሌዎችም ወጣት ነበሩ ። ሽማግሌ የማይሆን ወጣት ሊኖር ይችላል ፣ ወጣት ያልነበረ ሽማግሌ ግን የለም ።

የአገራችን ወጣቶች ችግር ምንድነው ? ወጣቶች በችግር ውስጥ እያለፉ እንደሆነ ይታወቃል ። ችግሮቹ ሰንሰለታማ ሲሆኑ ለመለወጥ ግን ከባድ አይደሉም ። መለወጥ የራስ ፈቃደኝነት የአምላክ እርዳታ የሚያመጣው ነው ።

የትምህርት ሥርዓታችን፡-

ጣልያን እንደወጣ በእንግሊዞች ደጋፊነት የተቀረጸው ሥርዓተ ትምህርት ኢትዮጵያን የኖረ እውቀትዋን ፣ አገር በቀል ሀብቷን ያገለለ ነው ። በኢትዮጵያ ልክ ያልተሰፋ ሥርዓተ ትምህርት በእንብርክክ የሚሄድ ትውልድን ፈጥሯል ። ቋንቋ በውስጡ ጥበብ ፣ ቅኔ ፣ ባሕልና ማኅበረሰብን የያዘ ነው ። በፈረንጅ ቋንቋ የተማረ ትውልድ የቋንቋው ሥር ያለበት አገርና ሕዝብ ሲናፍቀው የሚኖር ነው ። በራሱ ቋንቋ ያልተመራ ትውልድ ሊሰለጥን ፣ ሊያድግና ከሌሎች ጥገኝነት ሊላቀቅ አይችልም ። ዛሬ ነጻ መርከብ ቢቆም ሙልጭ ብሎ ለመሄድ የተዘጋጀ ፣ የፈረንጅ አገርን እንደ መንግሥተ ሰማያት የሚጠብቅ ትውልድ ያፈራነው በሥርዓተ ትምህርታችን ነው ። በደርግ ዘመን የመጣው ግብረ ገብ ትምህርትን ከትምህርት ተቋማት ያስወጣው ሥርዓትም መረን ትውልድን ለማፍራት ምክንያት ሆኗል።

እግዚአብሔር የለሽ ሥርዓት

አንድ ሦስተኛውን ዓለም የተቆጣጠረውና ለሰባ ዓመታት ዓለምን የገዛው የኮሚኒስት ርእዮት እግዚአብሔርን የለም ብሎ በመናገር የጀመረ ነው ። በዚህ ምክንያት ሰው እንደ ከብት ታረደ ፣ አራጆችም አሥርና ሃያ ሚሊየን ሕዝብ ገድለው የማይረኩ ሆኑ ። በአገራችንም እግዚአብሔር የለም ማለት እንደ ሥልጣኔ ተቆጠረ ። እግዚአብሔር የለም ብለው የካዱ ካህናትንም እናውቃለን ። በየትምህርት ቤቱ እግዚአብሔር ይመስገን አትበሉ ተብሎ ታወጀ ። ለ17 ዓመታት እግዚአብሔርን የካደ መንግሥት ፣ ክዶ ያስካደ ሥርዓት መጣ ። አራት ኪሎ ያለው የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና ባዕታ ለማርያም ገዳም በግንብ ተዘጉ ። በቀይ ሽብር ለሞቱት ወጣቶች ልቅሶ እንዳይደረግ ተከለከለ ። በአንድ ጥይት ሞቶ እንደሆነ ሃያ ብር ፣ በሁለት ጥይት ሞቶ እንደሆነ አርባ ብር እንድትከፍል እናት ተጠየቀች ። ይህን ተመን ያወጡት የተማሩ የተባሉት የዚያን ጊዜ ሊቆች ናቸው ። በዚህ እግዚአብሔር የለሽ ሥርዓት የተጠመቀው ትውልድ ውድቀቱ ከቃላት በላይ ሆነ ። ጭካኔ ፣ አለመጸጸት ገንዘቡ ሆነ ። ይህ ትውልድ በዕድሜ ቢገፋም ልቡ ጎረምሳ ሆኖ አሁን ድረስ ደም ያፋስሳል ።

ጎሠኝነት

በቂ አሳብ ፣ በቂ እውቀትና በበቂ ርእዮት የሌለው ሰው የሚደበቀው በዘረኝነት ውስጥ ነው ። የአሳብን ፣ የእውቀትን ፣ የርእዮትን ነገር የጠየቁት እንደሆነ እኔ ጎሣዬ ይህ ስለሆነ ነው ብሎ እሳት ያቀጣጥላል ። የሚገርመው አገሪቱን ሲገዙ የኖሩ ሳይቀሩ ተበድለናል ፣ ተገፍተናል ማለታቸው ነው ። የጎሣ ፖለቲካ ብሶተኛ የሚያደርግ ፣ ጭካኔን የሚያለማምድ ፣ ዕረፍት የሚነሣ ፣ ለእኔ ውድቀት እገሌ ነው ተጠያቂው እያለ እጅ የሚጠቁም ነው ። የአሁኑን ትውልድ በጎሠኝነት በክለነዋል ። ከሌላው ጋር የሚኖርበትን ሳይሆን የሚጫረስበትን ጥላቻ አስታጥቀነዋል ። ልበ ወለዳችንን ሳይቀር የሚያምን ምስኪን ወጣት ነው ። ከራሱ ከተማ ውጭ እንዳይኖር አፍነነዋል ። ሁሉ ዘመድህ ነው ብለን ከማስደሰት ሁሉ ጠላትህ ነው ብለን ለጠብና ለጦር  አዘጋጅተነዋል ። ሰላም ስለ ሌለው ሰላም ያሳጣል።

ሱሰኝነት

ሰዎች በአቋራጭ ደስታን ሲፈልጉ ፣ ከራሳቸው ለመደበቅ ሲሹ ፣ ሰበበኛነት ሩጫን ሲከለክላቸው ሱስ ውስጥ ይገባሉ ። በሱስ ውስጥ ሐሰተኛ ፍቅር ፣ ኅብረትና ቸርነት አለ ። እነዚህ በጋራ ለመሞት የማሉ ናቸው ። በሚገርም ሁኔታ አሁን ያሉት ባለሙያዎችና ባለጠጎች በአብዛኛው በሱስ ውስጥ የተዘፈቁ ሲሆኑ እዚህ ማኅበር ውስጥ ያልገባውን ሰው ሥራ እንኳ እንዳያገኝ ይከላከሉታል ። ብዙ ወጣቶች ለአስፈላጊው ነገር ገንዘብ የለንም ይላሉ ፣ ለሱስ ግን አላቸው ። ሱስ ሰውን ዕድሜውን የሚበላ የቁም ምስጥ ነው ። የኢትዮጵያ ወጣቶች አንዱ ችግር እየሆነ ያለው ሱስ ነው ። የሚወጡት የለበጣ ሕጎች “ጫት መሸጥ እንጂ ማስቃም አይቻልም” የሚሉ ናቸው ። ትውልዱ የሚቆረቆርለት አጥቶ ፣ መሪዎችም አባትነታቸውን ዘንግተዋል ።

የሌሎችን ባሕል እንደ ጽድቅ መቍጠር

የራሱን ቋንቋ እንደ ኋላ ቀርነት የሚያይ ፣ የፈረንጅን ቋንቋና ባሕል እንደ ጽድቅ የሚያይ ትውልድ አፍርተናል ። አንድ ፓስተር “ይህን አማርኛ ጌታ ይገሥጸው አይገልጽልኝም ፣ እንግሊዝኛው ይሻላል” ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ ። የገዛ ቋንቋ እየተገሠጸ የሰው አገር ቋንቋ እንደ ጽድቅ እየታየ ነው ። ሕንዶች ያደጉትና ወራሪ ቅኝ ገዥን ያስወጡት የራሳቸውን ነገር በመጠቀም አብዮት አካሂደው ነው ። የሰለጠነው ዓለም ባሕል የዘቀጠ ፣ ሰውን እንስሳ የሚያደርግ ፣ የሕፃን ባሕል ነው ። ደስታና ኀዘኑን ለመግለጥ የማይችል በጭንቀት የታፈነ ባሕል ነው ። የአገራችን ባሕል ግን ሕይወት በዚህ እንዳለ የሚያሳይ ነው ።

ትውልድን አለማስተማር

ቤተ ክርስቲያን ለትውልዱ ውድቀት ተጠያቂ ናት ። በሚገባ አላስተማረችምና ። ቤተ ክርስቲያን ማለትም እኛው አገልጋዮች ነን ። ከሕፃንነት ጀምሮ ትውልድን በቀና መንገድ አለመምራታችን አገር የዛሬውን ዋጋ እንዲከፍል ምክንያት ሆነናል ። ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ስናንጽ ሕንፃ ሥላሴ የሆነውን ሰውን ረስተናል ። እርጉዝ ላይ የሚጨክን ትውልድ ያፈራነው እኛው ነን ። ትውልዱን ለድብድብና ለእኛ ሥልጣን ማስጠበቂያ ስንፈልገው ለገዛ ሕይወቱ ግን አልፈለግነውም ። መለኪያ እስኪጠፋ ድረስ መጠጥ የሚጠጣ ከሆነ የእኛ ነው እያልን ለመናገር በቅተናል ።

ነውርን የሚያደፋፍሩ ስለሚመሩት

በአገራችን የስድብ ፋብሪካ የተከፈተ ይመስላል ። ሰውን ሲያዋርዱ መዋል እንደ ሥራ እየተቆጠረ ነው ። አፍሮ የኖረውን ትውልድ እያደፋፈሩ ካህን እንዲሰድብ ፣ ሽማግሌን እንዲያዋርድ አድርገውታል ። ጨለማና ብርሃንን መለየት ያልቻለ ትውልድ በእነዚህ በማያፍሩ ሰዎች እየተመራ ነው ። ከማንበብ ስድብን መስማት የሚያስደስተው ፣ በነውሩ የሚኮራ ትውልድ መጥቷል ። ተደብቆ የኖረው ጠባያችንን ማኅበራዊው መገናኛ አጋልጦታል ። ማኅበራዊው ሚዲያ አጋለጠን እንጂ ጠባይ አልሰጠንም ።

የዚህ መንገዳችን ውጤቱ ምን እየሆነ ነው ?

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም