መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የዛፍ ላይ እንቅልፍ

የትምህርቱ ርዕስ | የዛፍ ላይ እንቅልፍ

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ                                                       ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18/2007 ዓ.ም.
በአገራችን ምስራቃዊ ክፍል ከሚገኙ ከተሞች መካከል በአንዱ ጆሮዬ የሰማውና ልቤ የታዘበው ነገር ለዚህ ጽሑፍ መዘጋጀት በምክንያትነት አገልግሏል፡፡ ባለሥልጣን የነበረ አንድ ሰው (የዛሬን አያድርገውና) ዓይንን ከሚያማልል አካባቢው፣ ለኑሮ ምቹ ከሆነ ቤቱ፣ ደኅንነቱን በሚያረጋግጡ ዘቦች ከተከበበበት ኑሮው ወንጀል ሠርተሃል ተብሎ ወኅኒ (ማረሚያ) ቤት ወረደ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከሥልጣን ጋር በተያያዘ የሚነሡ ሰዎች በሕብረተሰቡ ዘንድ ቋሚ ተጠርጣሪ ናቸው፡፡ ለዚህም ያለፉ ልምዶቻችንን በእማኝነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አስተዳደጋችንን ብንፈትሽ እየሰማን የመጣነው ሹመት ከመብላት ጋር፣ ሽረት ደግሞ ከቁጭት ጋር እየተዜመልን ነው፡፡ ዛሬ የምናየው ሚዛን አልባነትና ጅምላዊ ፍረጃ የመጣውም ከዚሁ ቅኝት በመነሣት እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን የደመወዛቸውን ግማሽ ለተቸገሩት የሚያውሉ፣ ለወንጌል መስፋፋት በገንዘባቸው ያደሩ፣ ከሙላታቸው ብቻ ሳይሆን ከጉድታቸውም የሚያካፍሉ እንዳሉም እናስተውላለን፡፡
እግዚአብሔር ለረዳው ሰው ስልጣን አንዱ የአገልግሎት ክፍል ነው፡፡ “መሪው ከተመታ መንጋው ይበተናል” የሚለውም ወታደራዊ ስልት ከዚሁ ሐቅ የመነጨ ነው፡፡ አንድ አባት በመሪነት ጸጋ ላሉ አገልጋዮች የመከሩትን ምክር ሁሌም አልረሳውም፡፡ እንዲህ የሚል ነበር፡- “ልጆቼ ሆይ በጉዞ ላይ ካለ አንድ መኪና ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ተሳፋሪ ቢቅም ቢጠጣ ምንም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ሾፌሩ ቢቅምና ቢያጨስ ግን ጉዞ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም መሪው ያለው በእርሱ እጅ ነው፡፡” እኚህ አባት የተናገሩት ለአጭር ጊዜና በአጭሩ ቢሆንም መልዕክታቸው የያዘው አሳብ ግን ብርቱና የዕድሜ ልክ ነው፡፡

ሰዶማዊነትን ያራመዱ መሪዎች ሕዝባቸውን ሰዶማውያን፣ ጭካኔን ያበረታቱ መሪዎች ትውልዱን ጨካኝ ላማጠው የማይራራ፣ ጦርነትንም መፍትሔ ብለው ያስተማሩ መሪዎች ወገናቸውን ተናካሽ ነው ያደረጉት፡፡ መሪ ሲወሰልት ሕዝብ ወስላታ፣ ባለሥልጣን ሲስት ሠራተኞች ስሁታን መሆናቸው ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ገንዘብና ቁስ፣ ስልጣንና ምቾት ተገምደው የጠፈሩት ኑሮ ቢኖረንም ይህ ያለ መቀጮ የሚታለፍ ጉዳይ አይሆንም፡፡ አሁን ስለ ሰማሁት ልንገራችሁ ወንጀለኛው ባለ ሥልጣን ለዚህ የበቃው ገና ላልተወለደና ይህችን ምድር (ቁሳዊ ዓለም) ላልተቀላቀለ በእናቱም ማኅፀን ላለ ልጁ ስም በማውጣት መሬት /ቦታ/ በመያዙ ነው፡፡ ሰው ያለው ቊሳዊ ነገር ለሥጋቱ ልጓም ሊሆነው አይችልም፡፡ የሥጋ ከፍታም ፍርሃቱን አይንድለትም፡፡ ዘመናችንን ለመዋጀት ብንሞክር ሥልጣኔ ደምቆ የሚታይበት፣ የሰው ዕውቀትና ንቃት ያየለበት፣ ዓለም አንድ መንደር እንደሆነች የሚለፈፍበት፣ ለአንድ ሰው እልፍ አማራጭ እንዳለ የሚሰበክበት ነው፡፡ ዳሩ ግን የሕዝቦች ሥጋት፣ ኑሮዬ ይበቃኛል ብሎ አለመርካት፣ ገና የይሆናል ፍርሃት በዛፍ ላይ የማንቀላፋትን ያህል የሕይወት መርበትበት እየጨመረ መጥቷል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ በወንዝ ፍርሃት በወንበዴዎች ፍርሃት በወገኔ በኩል ፍርሃት በአሕዛብ በኩል ፍርሃት በከተማ ፍርሃት በምድረ በዳ ፍርሃት በባሕር ፍርሃት በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት በርሀብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ፡፡” (2ቆሮ. 11÷ 26-27) ይላል፡፡  ምን አልባት ሐዋርያው በዚህ ዘመን ቢኖር ኖሮ ከዚህም በላይ ስለ ብዙ ፍርሃቶች ይጽፍ እንደነበር የምናስብ እንኖራለን፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም ብንሆን አንድ እንኳን ቢጠቀስልኝ የምንለው ፍርሃት በኑሯችን ውስጥ አለ፡፡ ነገር ግን በሐዋርያው ሕይወት ውስጥ እጅግ መሳጭና ሕያው እውነቶች እንደነበሩ እናስተውላለን፡፡
ኑሮዬ ይበቃኛል ማለትን መርኁ ያደረገ ቁጥብ አኗኗር፣ ኃይልን በሚሰጥ በክርስቶስ ሁሉን የቻለ የእምነት ድፍረት፣ ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ ሞትም ጥቅም ነው የሚል ቆራጥነት፣ ሀገሬ ሰማይ ፤ ብድራቴ የድል አክሊል ነው ያለ ዕረፍት ነበረው፡፡ ሰውን ጥረቱና ንቃቱ፣ እውቀቱና ብልሃቱ የሚሻውን ዕረፍት ሊሰጡት አይችሉም፡፡ ሊቁ አውግስጢኖስ እንዳለ ክርስቶስ ጋር ደርሰን ካላረፍን በእርሱም ውስጥ ለመኖር ካልተሸነፍን በበቃኝ የምንገላገለው አንዳች ነገር አይኖርም፡፡
ከእምነት በሆነ ድፍረት ውስጥ ስንሆን ፍርሃት፣ አእምሮን የሚያልፍ ሰላም ሲኖረን ጭንቀት፣ የእግዚአብሔርን ክንድ ስንንተራስ ሥጋት ሁሉን በሚችል አምላክ ልጆች ፊት ሊቆም ሊገዛንም አይችልም፡፡
እግዚአብሔር ዕረፍት የሆነላቸው ሰዎች በሚንቀለቀል እሳት፣ አንበሳ ማደሪያው በሆነ ጉድጓድ ውስጥ እንኳን ምቾትና እረፍት ነበራቸው፡፡ ምነው ታዲያ እኛ ያማሩ መኝታዎቻችን፣ እይታን የሚማርኩ መኖሪያዎቻችን፣ አሉን የምንላቸው ነገሮች በዛፍ ላይ የማንቀላፋትን ያህል ሆኑብን? የእግዚአብሔር ሰው ያስተውላል፣ ልቡን ወደ ዘላለም ዕረፍት ያቀናል፣ ዘለቄታዊ ለሆነውም መፍትሔ ይሸነፋል፡፡ ያን ጊዜ እንኳን መኖር መሞት ውስጥም ጥቅም እንዳለ ይገነዘባል፡፡
የምንሰማው ድምጽ፣ የምናየው ድርጊት፣ የምንውላቸው ሰዎች ሁሉም ለመሥጋትና ለመፍራት ምክንያት ሆነውን ሊሆን ይችላል፡፡ እረፍታችን ግን ከምክንያቶቻችን በላይ ነው፡፡ እርሱም እንዲህ ይላል ፡- “ዕረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ” (መዝ. 45÷10)፡፡ አምላክ የሚለው ቃል ለኑሯችን ምን ያህል እንደተብራራ ማወቅ ባልችልም ከዚህ በላይ የሚያሳርፍ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የእግዚአብሔር አምላክነት መሳይም ሆነ ተካካይ የሌለው ነው፡፡ መከራዎቻችን ሊመሳሰሉ፣ ችግሮቻችን ካለፈውና ከሚመጣው ችግር ሊተካከሉ ይችላሉ፡፡ እርሱን ግን እንኳን ከድካማችን ከብርታታችን ጋርም ልናወዳድረው አይቻለንም፡፡ አብርሃም ከዘመድ አዝማዶቹ ተለይቶ ወደ ሥጋት ምድረ በዳ የተሰደደው የማያሰጋውን እግዚአብሔር ይዞ ነው፡፡ ዮሴፍ በወንድሞቹ ተሽጦ ግብጽ ሲወርድ የማይሸጥ የማይለውጥ እግዚአብሔር ነበረው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል፡- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ.11÷28)፡፡ እትው በዕረፍት!     
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም