“ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ” /ዮሐ. 4፥5/ ።
ጌታችን ጉዞውን የጀመረው ከኢየሩሳሌም ወደ ሰማርያ ነው ። ቢያንስ አርባ ኪ.ሜ. ተጉዞአል ። ከሰማርያ አውራጃ ሴኬም ከተማ ሲደርስ ቀትር ነበረ። ረሀብና የውኃ ጥም ገጥሞታል ። ረሀቡ ደቀ መዛሙርቱን ምግብ እንዲገዙ በመላኩ ፣ ጥማቱ ደግሞ ሳምራዊቷን ሴት ውኃ በመለመኑ ይታወቃል ። ጌታችን ከረሀብና ከጥማት የተነሣ ደክሞ ነበር ። በሰማርያ አውራጃ ካሉት ከተሞች በጣም ውብ የነበረችው ያች የሸለቆ ከተማ ሴኬም ነበረች ። ሴኬም በሁለት ተራሮች በገሪዛንና በጌባል መካከል የተመሠረተች ከተማ ናት ። ገሪዛንና ጌባል ጉልህ ሆነው ይታያሉ ። እግዚአብሔር በረከትንና መርገምን ያስተማረባቸው ተራሮች ናቸው ። ገሪዛን ፍጹም ለምለም የነበረ ተራራ ሲሆን ጌባል ደግሞ ፍጹም ደረቅ የነበረ ተራራ ነው ። በዚያ ዘመን የነበረው ቡራኬ እግዚአብሔር እንደ ገሪዛን ያለምልምህ የሚል ሲሆን ርግማኑም እግዚአብሔር እንደ ጌባል ያድርቅህ የሚል ነበር ። እያንዳንዱ የሴኬም ነዋሪ ከቤቱ ሲወጣ እነዚህን ሁለት ተራሮች ይመለከት ነበር ። ለእግዚአብሔር ቢታዘዝ እንደ ገሪዛን እንደሚለመልም በእግዚአብሔር ላይ ቢያምጽ ደግሞ እንደ ጌባል እንደሚደርቅ ያስብ ነበር /ዘዳ. 11፥29/።
ሳምራውያን ገሪዛንን በጣም ያደንቁ ነበር ። አብርሃም የሠዋው ሙሴም መሥዋዕት እንዲሠዋበት ያዘዘው በገሪዛን ነው ብለው ይናገሩ ነበር ። ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመት በፊት መቅደሳቸውን በገሪዛን ተራራ ላይ ሠሩ። የገሪዛን መቅደስም የበለጠ ነው ብለው ይሰብኩ ስለነበር አይሁዳውያን በጣም ይበሳጩ ነበር ። ከመቃብያን ወገን የሆነው ዮሐንስ ሂርቃኖስ ሰማርያን ለማስገበር በ136 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ ዘመተ ። የገሪዛኑንም መቅደስ አፈረሰ ። ከዚህ በፊት በነበረው የአምልኮ ቦታ ክርክር ላይ የመቅደሱ መፍረስ ርእሱን አደገኛ አደረገው ። ሳምራዊቷ ሴት ጌታን እንደ ነቢይ ባየችው ጊዜ ፡- “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፡- ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው” /ዮሐ. 4፥20/። ይህን በምትናገርበት ጊዜ የገሪዛን መቅደስ ፍርስራሾች ይታዩ ነበር ። አምልኮ በኢየሩሳሌም ነው ወይስ በገሪዛን የሚለው አሳብ ጦርነትን የወለደም ነበር ። ይህች ሴት ያቀረበችው ጥያቄ ተራ ጥያቄ አልነበረም ።
ሲካር ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን ከሴኬም በስተደቡብ የምትገኝ አነስተኛ መንደር ናት ። ታላላቅ ታሪኮች ስለተከናወኑባት ግን መጽሐፉ ከተማ ይላታል /ዮሐ. 4፥5/ ። ቫቲካን አንድ ቀበሌ ሳለች አገር ትባል የለ ! ሲካር ከሴኬም አንድ ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን የውኃው ምንጭ ደግሞ ከሲካር 500 ሜትር ርቀት ላይ ያለ ነው ። ጌታችን ሳምራዊቷን ሴት ሲያገኛት ያ ምንጭ 2 ሺህ ዓመታት ያህል አገልግሎት እየሰጠ ነበር ። ይህ ምንጭ ዛሬም በእስራኤል ምድር አንድ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶበታል ። ወደ ምንጩ የሚያስወርደው ከወለሉ በታች ስድስት ሜትር ዝቅ ያለ ነው ። የዛሬው የውኃው ጥልቀት 32 ሜትር ያህል ነው ።
ሴኬም ቀድሞ የከነዓናውን በኋላ የእስራኤል ርስት ሆናለች ። በዚህች በሴኬም ወይም በሲካር አብርሃም መሥዋዕት አቅርቧል /ዘፍ. 12፥6-7/። ያዕቆብም በገንዘቡ የገዛት ከተማ ናት /ዘፍ. 33፥19/። በእህታቸው በዲና መደፈር ምክንያትም የያዕቆብ ልጆች የሴኬምን ሰዎች በሰይፍ ስለት አጠፉ /ዘፍ. 34/። ያዕቆብም ወደ ልጁ ወደ ዮሴፍ ተሰዶ በግብጽ ሳለ የመጨረሻ ቡራኬውን ሲያስተላልፍ ሴኬምን ለተወዳጅ ልጁ ለዮሴፍ ርስት አድርጎ ሰጠው /ዘፍ. 48፥22/ ። ያዕቆብ ይህችን ምድር ለዮሴፍ የሰጠው በግብጽ ምድር ላይ ስደተኛ ሁኖ ነው ። ያዕቆብ ስደተኛ ነው ፣ ለልጁ አገር ይሰጣል። ልጁ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው ፣ ያዕቆብ ግን ትንሽ መንደርን ይሰጠዋል ። አሁን ያሉት በግብጽ ነው ፣ ያዕቆብ ግን ወይ በሕይወቱ አሊያም በሞቱ ከነዓን እንደሚገባ ተስፋ አለው ። ከዚህ የምንማረው፡-
1- በያዝነው ትልቅ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰጠን ትንሽ እንደምንባረክ ነው ። እግዚአብሔር የሰጠን ሴኬምን ከሆነ ስማችን የሚጠራው በዚያው ነው ። ዮሴፍ ዛሬ በግብጽ አይነሣም ። ግብጽን በሙሉ ቢገዛም ትንሿና የልጅነት አገሩ ሴኬም ግን ትበልጥ ነበር ። እግዚአብሔር ገና በጥዋቱ የሰጠን ትንሽ የመሰለን ጸጋና ስጦታ እርሱ ይበልጣል ።
2- በምድር ላይ ስደተኞች ነን ። ነገር ግን የሰማይ አገርን ለሌሎች እናወርሳለን ። ሐዋርያው ፡- “ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” ይላል /2ቆሮ. 6፥9-10/። ስደተኛው ያዕቆብ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበረው ፣ ጌሤምን የምታህል ርስት ለሰጠው ለልጁ ለዮሴፍ ሴኬምን ሰጠው ። ነገሥታትም ቢሆኑ የሚቀበሉት አለ ። የአባት ስጦታ ትንሽ ቢመስልም በረከቱ ለዘላለም ነው ። ከትልቁ እግዚአብሔር የምንቀበለው ትንሽ ስጦታ የለም ። እግዚአብሔር የሰጠን ሁሉ ትልቅ ነው ።
3- አሁን በምድር ላይ ነን ። ቀጣይ ግን በሰማይ ነን ። ይህች ዓለም ከንቱና ብላሽ ደግሞም ኃላፊ ናት ። እንደ ልባሽ ጨርቅ ናትና ትነትባለች ፣ እንደ ጤዛ ናትና ትረግፋለች ፣ እንደ ጀንበር ናትና ትጠልቃለች ፣ እንደ ሕልም ናትና ትጠፋለች ፣ እንደ ቅጠል ናትና ትረግፋለች ፣ እንደ ጽዋ ናትና ለተረኛ ትሰጣለች ። ስለ ዓለም ከንቱነት ስለ እግዚአብሔር ኃያልነት ማሰብ ፣ መመስከር በእውነት ይገባል ።
ጌታችን ከኢየሩሳሌም ወደ ሰማርያ የመጣው ወደዚህ ወደ ሲካር ነው ። ወንጌላዊውም እንዲህ ይላል ፡- “ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ” /ዮሐ. 4፥5/ ። ያዕቆብ ለዮሴፍ በሰጣት ሲካር ላይ ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት መንግሥቱን ሰጣት ። ያዕቆብ የሚያስጠማውን ውኃ በሰጠበት ሲካር ላይ የማያስጠማውን ውኃ ለሴቲቱ ሰጣት ። እርሱ ከያዕቆብ ይበልጣል ።