ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ምዕራፍ አራትን የሚፈጽመው ጌታችን በገሊላ ያደረገውን ሁለተኛውን ምልክት በመናገር ነው ፡፡ የመጀመሪያው ምልክት የቃና ዘገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅ መለወጥ ሲሆን ፣ ሁለተኛው ምልክት ደግሞ የቅፍርናሆሙ ሹም ልጅ መፈወስ ነው ፡፡ ምልክት መዳረሻ እንጂ መድረሻ አይደለም ፡፡ ምልክት የመጨረሻው መጀመሪያ ነው ፡፡ ምልክትነቱም ለነፍስ መዳን ነው እንጂ የመጨረሻው ግብ አይደለም ፡፡ ከዚህ የበለጠ የነፍስ ፈውስ እንዳለ ሰዎች እንዲገነዘቡ ጌታችን ምልክቶች አደረገ ፡፡ በመካከል የኒቆዲሞስና የሳምራዊቷ ሴት መዳንን ዘሎ ሁለተኛ ምልክት አለ ፡፡ ምልክት የሚለው ቃል ለኒቆዲሞስም ሆነ ለሳምራዊቷ ሴት አልተጠቀሰም ፡፡ የነፍስ መዳን ነውና ፍጻሜ ምልክት አይባልም ፡፡ ዋናው መሥሪያ ቤት የደረሰ ሰው ምልክቱን አይፈልግም ፡፡ የነፍስ መዳን በቃሉ፣ በቸርነቱና በእምነት ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡
በዮሐንስ ወንጌል ሰፊ ትርጉም የተሰጣቸው እውነት ፣ ጸጋና እምነት ናቸው ፡፡ እውነትና ጸጋ የጌታችንን ተዋህዶና ቤዛነት የሚገልጡ ናቸው ፡፡ እውነትን ያላጓደለ ጸጋ ፣ ጸጋን ያልጣለ እውነት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጽሟል ፡፡ በመለኮትነቱ ብቻ የማይሞተው ፣ በሰውነቱ ብቻም የማያድነው እርሱ በለበሰው ሥጋ ሞተ ፣ ሥጋም በተዋሐደው መለኮት አዳኝ ሆነ ፡፡ ሞት ለመለኮት ሲነገር ፣ ማዳንም ለትስብእት ተነገረ ፡፡ በዚህ ውስጥም መሞት የሚገባን የማይገባንን ሕይወት እናገኝ ዘንድ ተፈረደልን ፡፡ እምነትም ወደ ራስ አቅርቦ ይህ ለእኔ ነው ብሎ የነጻነቱን ደብዳቤ መቀበልና ላልሰማው ምስኪን ማወጅ ነው ፡፡ እነዚህ የሕይወት አቅሞች በኒቆዲሞስና በሳምራዊቷ ሴት ተፈጽመዋል ፡፡ እውነት እስኪገኝ ብዙ ሙግት ነበረ ፣ ስለዚህ ኒቆዲሞስም “እንዴት” ብሎ ተከራከረ ፡፡ ሳምራዊቷ ሴትም የአሳብ ፍልሚያ አደረገች ፡፡
ጸጋ እንዲሁ ያከብራል ፡፡ የኒቆዲሞስን እውቀት የሳምራዊቷን ሴት አላዋቂነት ሳያገናዝብ ይሠራል ፡፡ በጸጋ ውስጥ መታዘብ የለም ፡፡ መሙላት ብቻ አለ ፡፡ እምነት ደግሞ ልብን ከፍቶ በነጻነትና በደስታ እውነትን መቀበል ነው ፡፡ ወንጌላዊው ተአምራትን አያዳንቅም ፡፡ ተአምራት እንደ አምሮት መቀስቀሻ ነው ፡፡ ጥጋቡ ያለው በነፍስ ድኅት ውስጥ ነው ፡፡ ዋናው ምግብ እስኪመጣ የሚመጡ የአምሮት መቀስቀሻዎች እስከ መጨረሻው አይበሉም ፡፡ እስከ መጨረሻው ከተበሉ ዋናው ምግብ ሲመጣ መግፋት ይከሰታል ፡፡ ዋጋ የተከፈለው ለዋናው ምግብ ነውና ዋጋው መሬት ላይ ይቀራል ፡፡ ምልክት አሳዳጅነት የዘማ ጠባይ ነው ፡፡ ዘማዊ ማለት የሥጋ ፈቃድ ስሜት ያለው ማለት ሳይሆን በአንድ የማይረጋ ማለት ነው ፡፡ በአንድ አምላክ በአንድ አጥቢያ፣ በአንድ አገልጋይ የማይረጋ የዘማ ጠባይ የተቆራኘው ነው ፡፡ ሲዞር የሚውል ፣ ሲዞር የሚኖር ነው ፡፡ ምልክት ፈላጊ አማልክትን አጫራች ነው፡፡ የበለጠ ካገኘ በጨረታው አይገደድም ፡፡
ከእግዚአብሔርም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለን ግንኙነት የሥጋ ሳይሆን የነፍስ ፈውስ ነው ፡፡ የሥጋ ፈውስ የነፍስን ፈውስ ማስካድ የለበትም፡፡ የዘማዊ ጠባዩ አዲስ ሲያገኝ የትላንቱን ያማል ፡፡ እንዲሁም በሥጋ የተፈወሰ በነፍስ የተፈወሰባትን ቤተ ክርስቲያን ሲያማ ይኖራል ፡፡ ያጠመቀችውን ፣ ያቆረበችውን ፣ የዘላለም ሕይወትን ያቀረበችለትን ቤተ ክርስቲያን ከጊዜያዊ ጭንቀት ዳንሁ ብሎ ሲተች ይኖራል ፡፡ በድኅነተ ነፍስ ክርስቶስ ራሱን ይሰጠናል ፡፡ በምልክቶች ግን ኃይሉን ያሳየናል ፡፡ የማያልፈውን የተቀበለ የሚያንሰውን አጣሁ ብሎ ማዘን አይገባውም ፡፡ ቢሆንም እግዚአብሔር ይረዳልና በትዕግሥት ሊጠብቀው ይገባል ፡፡ አምላኩን እንደ ውስን ቆጥሮ በየስፍራው ሊፈልገው አይገባም ፡፡ እርሱ በተለየ ቦታ ሳይሆን በተለየ ልብ ይገኛል ፡፡
በአብዛኛው አብያተ ክርስቲያናት ዓለምን ያኮረፈ ምእመን እንጂ ዓለምን ቀብሮ የመጣ ሰው ማግኘት እየቸገረ ይመስላል ፡፡ ዓለም ፈገግ ያለችለት ቀን ተንጋግቶ ይወጣል ፡፡ በነጠላ መጥቶ በቡድን ይወጣል ፡፡ የክርስትና በሩ ጠባብ ነው ፡፡ በጠባቡ በር የምንገባው በሰፊ እምነት ነው ፡፡ በሩ የሚጠበው ለከሃዲዎችና ዓለምን ለሚወዱ ነው ፡፡ ከእምነት መጥበብ የተነሣም መግባት ከባድ ሆኖባቸዋል ፡፡ ጠባብ መንገድ አንድ መንገድ ነው ማለት መሄጃ እንጂ መመለሻ የለውም ፡፡ ይህንን መንገድ ቃል ኪዳን የሌለው ሰው አይፈልገውም ፡፡
ምልክት የሚናፍቀው ወገን የአገሩን ጠበል እየናቀ ከውጭ አገር ጠበል በዶላር ገዝቶ ሲጠቀም ስናይ አገርን አለመቀበል እንጂ የሃይማኖት አጀንዳ አይደለም እንድንል ያደርገናል ፡፡ ሁሉም ሰው በራሱ ሕመም ያለቅሳል ፡፡ ለራሱ ሕመምም ሁሉንም ነገር መሞከር ትክክል እንደሆነ ያስባል ፡፡ ለዘመናት ያገለገሉት አገልጋዮችን አንድ ቀን እፈውስሃለሁ ባለው ሰው ሲለውጡ በብዙ አገራት አይተናል ፡፡ በአገራችን ባሉ ፎቆች ላይ ውኃ ታች እንጂ እላይ መድረስ ያቅተዋል ፡፡ ታች ወይም ምሳሌው ላይ የቀረው በዚያ ብቻ ሲረካ እውነቱ ላይ ግን መድረስ ያልቻለው ትውልድ መርካት ያቅተዋል፡፡ በየዐውደ ምሕረቱ የሚሰሙ ምስክርነቶች ለንስሐ ስለመብቃት የተደረጉ ስእለቶች አይደሉም ፡፡ መቅደስ እየሠራን መቅደስ ሰውነታችን ግን ፈርሷል ፡፡ በሬ እያመጣን እኛ ግን ወጥተናል ፡፡ ከሌላው እየቀማን አሥራት በኩራት እናወጣለን ፡፡ ድሮ ሌቦች ስእለት ይሳሉ ነበር ሲባል እንሰማለን ፡፡ አሁን ሰምተን አናውቅም ፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት ከሆነ ርእሱ አይገርምም፡፡ የሠራተኛ ደመወዝ እየከለከሉ መባ መስጠት ትርጉም የለውም ፡፡ ይህ የግፍ ገንዘብ አገልጋዮችን ቢያባላቸው ምን ይደንቃል ?
የመጨረሻው ዘመን አማንያን ለብ ያሉ እንደሆኑ መጽሐፍ ይገልጣል፡፡ ያልሞቁ ያልቀዘቀዙ እንደሆኑ ያስረዳል ፡፡ ጨርሶ ማመንም ሆነ ጨርሶ መካድም አይታይባቸውም ፡፡ እንዲህ ያለው ማንነት በጣም አደገኛ ማንነት ነው ፡፡ የለዘዘ ነገር ሊያኝኩትም ሊተፉትም አስቸጋሪ ነው ፡፡ በአገራችን እግዚአብሔር የለም እያለ በአደባባይ የሚያስክደው ልጁን ክርስትና ለማስነሣት ጎረቤቱን ሲልክ እናውቃለን ፡፡ ምልክት አፍቃሪነት ለዛዛ እምነትን ይወልዳል፡፡ ጌታችን ውኃን ወደ ወይን ጠጅ እንዲለውጥ ቅድስት እናቱ ስትለምነው ጊዜዬ አልደረሰም ያለው ለምንድነው ?
1- እነርሱ የጎደላቸውን አውቀው ይጠይቁ ማለቱ ነው ፡፡
2- በተአምራት ውኃውን ወይን ጠጅ ማድረግ እችላለሁ ፣ በመሥዋዕትነት ግን እውነተኛውን ደሜን ወይን አድርጌ እሰጣለሁ ማለቱ ነው ፡፡ ከተአምሩ በላይ ወደ መሥዋዕትነቱ እንዲያዩ እየነገረ ነው ፡፡ ማዳኑ መሥዋዕትነት ፣ ተአምሩ ግን የቃል ትእዛዝ ይጠይቃል፡፡
ጌታችን ተአምራት ከማድረጉ በፊት ኃጢአትህ ተሰረየችልህ የሚለው የነፍስ ፈውስ ስለሚቀድም ነው /ማር. 2፡5/ ፡፡ የሚቀድመው ሲቀድም የሚከተለው በግድ ይከተላል ፡፡ በሌላ ስፍራም ፡- “ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና” ብሏል /ማቴ. 5፡29-30/ ፡፡ ከመንግሥተ ሰማያት እንደ ገዛ አካል የሆነች ሚስትም ልታስቀር አይገባም ማለቱ ነው ፡፡ ጌታችን ከአካል በላይ መንግሥተ ሰማያትን አክብሯል ፡፡
አዎ ዮሐንስ ወንጌላዊ የኒቆዲሞስንና የሳምራዊቷን ሴት መዳን ምልክት አላለውም ፡፡ ፍጻሜ ነውና ፡፡ የቅፍርናሆሙ የንጉሥ ቤት ሹም አማኝ ነበረ፡፡ ይህ ሰው የሚያገለግለው ሄሮድሳውያንን ነው ፡፡ ሄሮድስ ማለት የነገሥታት የመዐርግ ስም ነው ፡፡ ዐጼ እንደ ማለት ነው ፡፡ የኤዶም ዘሮች ሲሆኑ ታላቁ ሄሮድስ ለሮማው ቄሣር ባሳየው ታማኝነት የንግሥና በትርን ለእርሱና ለዘሩ ተቀብሏል ፡፡ ሄሮድሳውያን አማኝ አልነበሩም ፡፡ ጌታችንን በሕጻንነቱ ያሳደደው ሄሮድስ ፣ ዳግመኛም የዮሐንስን አንገት ያስቆረጠውና በጌታችን መሞት የተስማማው ሄሮድስን መጥቀስ ይቻላል ፡፡ በማያምኑ ነገሥታት ቤት ግን የሚያምኑ ሰዎች አሉ ፡፡ ከብሉይ ኪዳን አብድዩ የተባለው ሰው የንጉሥ አክአብ አገልጋይ ነበረ ፡፡ ኤልዛቤል ነቢያትን ስታስገድል መቶ ነቢያትን በዋሻ ደብቆ የመገበና ከሞት ያዳነ ነው /1ነገሥ. 18/፡፡ በኋላም የነቢዩ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ሁኖ ትንቢተ አብድዩ በመባል የሚታወቀውን የጻፈ ነው ፡፡ የሚገርመው ትንቢቱ የሚናገረው ስለ ኤዶማውያን ነው ፡፡ እነዚህ በኋላ ዘመን ሄሮድሳውያን የሆኑ ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር በከሃዲዎች መካከል አማኞች ፣ በረከሰ ከተማ ቅዱሳኖች ፣ በቤተ መንግሥት አዋጅ አስለዋጮች አሉት ፡፡
ቀጣዩ ምዕራፍ ምዕራፍ አምስት ነው ፡፡ ምዕራፍ አምስት ሁለት አከፋፈል አለው ፡-
1- ከቁ. 1 – 9 የመጻጉዕ መዳን
2- ከቁ. 10 – 47 ፈውሱ ላመጣው ተቃውሞ ጌታችን የሰጠው መልስ፡፡