የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሠሪው እግዚአብሔር

“ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።” /ዮሐ. 5፡17/፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን ለዚያ የሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛ እውነተኛ ሰንበትን ወይም ከስቃይ ማረፍን ፣ ከጭንቀት መገላገልን፣ ከቀንበር መላቀቅን ከእስራት መፈታትን አደለው ፡፡ ጌታችን የሕይወት ሰንበት ለመሆን ወደ ዓለም መጥቷልና ፡፡ በታላቅ ማዳኑ በሚመሰገንበት ቀን ታላቅ ጥላቻና አምባጓሮ ተነሣበት ፡፡ ታላላቅ ተአምራቶች ታላላቅ ፈተና ይዘው እንደሚመጡ ብዙ ጊዜ አናስተውልም ፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ ሲሠራ እግዚአብሔርን የሚያምኑት እምነታቸው ሲያድግ የማያምኑት ግን ልባቸው የበለጠ እየጸና ይመጣል ፡፡ ሁሉም በየአቅጣጫው በየዕለቱ ያድጋል ፡፡ የሚወጣውም ይወጣል ፣ የሚወርደውም እጅግ ይወርዳል ፡፡ ጌታችን በሰንበት ቀን በመፈወሱ ፣ ሥራ እንደ ሠራ ያህል ተቆጠረበት ፡፡ የሰንበት ጠበቆች ነን የሚሉ አይሁድ ተነሡበት ፡፡ እርሱ ግን ምስክሮች እንጂ ጠበቆች የሉትም ፡፡ በያዙት ቀን እንኳ ብዙ ጭፍሮችን መላክና መደምሰስ ሲችል እርሱ ግን ይህን አላደረገም ፡፡ ለማዳን እንጂ ለማጥፋት አልመጣምና ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ ጠባይና አሳብ ተነሥተው ካልተረጎሙት አስጨናቂና አስፈሪ ይሆናል ፡፡ ስብከት ሰውን ማምጫ ብቻ ሳይሆን መሸኛም ይሆናል ፡፡ ምክንያቱም ቃሉ የእግዚአብሔር ፣ አሳቡ ግን የሰው ሲሆን ከማዳን ይልቅ ያጠፋል ፡፡ ሰዎችን ለንስሐ ማብቃት ያለብን የእግዚአብሔርን ፍቅር ተናግረን እንጂ በፍርሃት አስጨንቀን አይደለም ፡፡ በፍርሃት ሁሉ ሊገብር ይችላል ፡፡ እውነተኛ ምርኮኞች ግን የፍቅር ተነሳሕያን ናቸው ፡፡ እውነተኛ ንስሐ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር የሚደረግ መጽናናት ያለበት ዕንባ ነው ፡፡
ጌታችን የሰንበት ጌታ መሆኑን አልተረዱም ፡፡ በሰንበት አንድ በግ ወደ ገደል ቢገባ የሚያወጡ አይሁድ በሰንበት በቤተ ሳይዳ የወደቀ ሰው ሲነሣ ተቃወሙ ፡፡ ከሰው ይልቅ ለበግ ዋጋ ነበራቸው ፡፡ በሰንበት በሬ ቢወድቅ የሚያነሡ የዘመናት እስረኛ ሲፈታ አጉረመረሙ ፡፡ ዛሬም ብርና ወርቅን ለመቀበል የተዘጋጀነውን ያህል ነፍስ ለመቀበል ካልተዘጋጀን አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ የሰንበትን ጌታ ያለማክበር ኃጢአት ነው ፡፡
ጌታችን ግን ለአንዱ ቀን ፣ ለአንዱ ሰንበት የሠራው ሥራ ሲገርማቸው ያልሠራበት ቀን እንደሌለ ነገራቸው ፡፡ ሁልጊዜ በሥራ ላይ ነው ፡፡ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ መባሉ በሠራው ሥራ መርካቱን ለመግለጥ እንጂ ሥራ መፍታትን የሚያመለክት አይደለም ፡፡ ሰባተኛውን ቀን ሲቀድስም ተግባረ ነፍስን በሙሉነት ለመፈጸም ቀንን መስጠቱን ፣ ዘመንን በሙሉነት መስጠትን ከአንድ ቀን በመነሣት ለማለማመድ ነው ፡፡ በቀንና በቦታ የተወሰነ አምልኮ ወደ መንፈሳዊ አምልኮ እንዲያድግ ጅማሬ ነው ፡፡ ቢሆንም ሰንበት የእግዚአብሔር ነው ፡፡ ይህን ቀን በራሳቸው ስም የሰየሙ ብዙ ቄሣሮች ነበሩ ፡፡ ክርስቲያኖችም የጌታ ቀን በማለት መጥራታቸው ለዚህ ነው ፡፡ በመሠረቱም በሂደቱም ቀንና ዘመን የጌታ ነው ፡፡ አይሁድ እግዚአብሔርን በስድስት ቀን ወስነውት በሰባተኛው ቀን እንደማይሠራ ያስቡ ነበር ፡፡ ነገር ግን እርሱ ያልሠራበት ዘመን የለም ፡፡ ሁልጊዜ በሥራ ላይ ነው ፡፡ ለአንድ ሰንበት ከገረማቸው በጥንተ ፍጥረት በነበረችው ሰባተኛ ቀንም እንዲመሽ እንዲነጋ ያደረገው እርሱ ነው ፡፡ ሰንበትን ሻሪ መሆኑን ሲናገሩ ጌታ ግን የሰንበት መሥራች መሆኑን ተናገረ ፡፡ እንደ ሕግ አፍራሽ ሲቆጥሩት እርሱ ግን ሕግን የሠራ መሆኑን ገለጠ ፡፡ ሊሰሙ የማይፈልጉትን አሰማቸው ፡፡ እርሱ አምላክ የሚሆነው ሰዎች ሲስማሙ አይደለም ፡፡ እርሱ ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው ፡፡ የሰንበት ተግባር ድሆችንና ሕሙማንን መጎብኘት ነው ፡፡ ጌታችን ሰንበትን በዓላማዋ እንድትውል አደረጋት ፡፡ ብቻዋን ዕረፍት አይደለችም ፡፡ በሚያሳርፍ ተግባር ታሳርፋለች እንጂ ፡፡
እግዚአብሔር ዛሬም በሥራ ላይ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ ነው ፡፡ የዓመት ፣ የወር መባቻ ፣ የሰንበት አምላክ አይደለም ፡፡ እርሱ የጊዜ ቀጠሮ የሌለበት ሁልጊዜ የሚሠራ አምላክ ነው ፡፡ እግዚአብሔር መሥራቱን ድሮ ያቆመ የሚመስላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡ እግዚአብሔር ግን ታሪክ አይደለም ፡፡ በአንድ ዘመንም በርትቶ በአንድ ዘመን የደከመው አይደለም ፡፡ ሁልጊዜ ሳይታክት የሚሰጥ ፣ ሳይደክም የሚሸከም ነው ፡፡ የእስራኤልን ልጆች ነጻ እንዲያወጣ ሙሴን በላከው ቀን እግዚአብሔር “ያለና የሚኖር” የሚለውን ስሙን ገለጠለት ፡፡ ያለና የሚኖር ማለት እንደ ጥንቱ ዛሬም ይሠራል ፡፡ እንደ ዛሬው ጥንትም ሠርቷል ማለት ነው ፡፡ እግዚአብሔር ታሪክ አይደለም እርሱ ሕያው አምላክ ነው ፡፡ የእነ አብርሃም አምላክ የዚህ ትውልድም አምላክ ነው ፡፡ ለአብርሃም የሠራውን እንደ አብርሃም የሚያምን ከተገኘ ዛሬም ይሠራል ፡፡ በአምላክነቱ የታመነ ነው ፡፡
“ኢየሱስ ግን፦ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።” /ዮሐ. 5፡17/፡፡ ጌታችን የሚሠራው ልክ እንደ አባቱ መሆኑን ተናገረ ፡፡ በሰንበት በመፈወሱ እግዚአብሔርን የተቃወመ ስለመሰላቸው ይህን አለ ፡፡ ለእግዚአብሔር የቀኑለት እየመሰላቸው እግዚአብሔርን እየተቃወሙ ነውና ፡፡ ዳግመኛም አባቱ የሚሠራውና እርሱ የሚሠራው አንድ ዓይነት ተግባር እንደሆነ ገለጸላቸው ፡፡ ሥላሴ በአካላት ግብራቸው ሦስት ሲሆኑ በመለኮት ግብራቸው ግን አንድ ናቸውና ፡፡ የአካላት ግብር ውሳጣዊ ግብር ሲሆን የመለኮት ግብር ግን አፍአዊ ግብር ነው ፡፡ በመለኮት ግብር ውስጥ ፍጡራን በረከትና ጸጋን ይቀበላሉ ፡፡ ስለዚህ ሥላሴ የታመመውን የሚፈውሱት በአንዲት ግብር ነው ፡፡ ጌታችን ይህን ገለጸላቸው ፡፡ እስከ ዛሬ ይሠራል አለ ፡፡ አብ ተግባሩን የሚፈጽመው በቃሉ ወይም በወልድ ነው ፡፡ ቃሉ ነውና አብ ሠራ ይባላል ፡፡ እኛ በልባችንና በቃላችን መካከል ልዩነት እንደሌለ እንዲሁም አብና ወልድ በመለኮታዊ ግብራቸው አንድ ናቸው ፡፡ ሥላሴን አንዲት ፈቃድ ፣ አንዲት ግብርና አንዲት ሕይወት የሚያሰኛቸው ይህ ነው ፡፡ አሊያ በመጻጉዕ መፈወስ ምስጋና መቅረብ ያለበት ለማን ነው ?
እስከ ዛሬ ይሠራል አለ ፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች በጎነትን ያደርጋል ፡፡ ያ በጎነት በቤተ ሳይዳ የጀመረ ሳይሆን ሁልጊዜ የሚኖር ነው ፡፡ ቤተ ሳይዳ የተፈጸመው ከሥራው አንዱ እንጂ ብቸኛ ተግባሩ አይደለም ፡፡ እግዚአብሔር የታወቀና ያልታወቀ ፣ የተገለጠና ያልተገለጠ ተግባር አለው፡፡ ጌታችን አባቱ በሠራበት ዘመን ሁሉ እሱም እንደ ሠራ ተናገረ ፡፡ ከአባቱ ጋር በዘመን ፣ በክብር በሥልጣን አንድ ነውና ፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም ይሠራል ፡፡ እስከ ዛሬ ለእስራኤል ፣ እስከ ዛሬ ለሰው ልጆች ፣ እስከ ዛሬ ለእያንዳንዳችን ሠርቷል ፡፡ እግዚአብሔር ከተጠራበት ስያሜ አንዱ ሠሪው የሚል ነው /ኢሳ. 27፡11፤ 29፡16፤ 45፡9፣11/፡፡
–    ሲሠራ የማይሳሳት
–    ሲሠራ ነገርን በጊዜው ውብ የሚያደርግ
–    ሲሠራ ብልሃተኞች የማይተቹት
–    ሲሠራ ለሞተው ነገር ሕይት የሚሰጥ
–    ሲሠራ የሌለውን እንዳለ አድርጎ የሚጠራ ነው ፡፡
አበጀዋለሁ ስትሉ ድንጋይ ላይ እንደ ወደቀ ሸክላ ሁሉም ነገር የተሰበረባችሁ ፣ ይቅርታ አወርዳለሁ ስትሉ ቃላችሁ ጦርነት ያስነሣባችሁ ፣ አገለግላለሁ ስትሉ ድምፃችሁ አልሰማ ያላችሁ ፣ እየቀረብኩ ነው ስትሉ ፍላጎታችሁ ይበልጥ የራቃችሁ ፣ ጥሩ ለመሆን ስትነሡ ሰዎች ክፉ ሆነው የጠበቁአችሁ ፣ እግዚአብሔር በዛሬው ዘመን ፍርድ ያቆመ መስሏችሁ እጅግ የታከታችሁ ፣ ይህች ዓለም ለክፉዎች ተላልፋ የተሰጠች የመሰላችሁ ፣ … ለሠሪው እግዚአብሔር ቦታ ልቀቁለት እርሱ በጊዜው ነገርን ውብ አድርጎ ይሠራዋል ፡፡ ስለማይታየን እንጂ ዛሬም እግዚአብሔር እየሠራ ነው ፡፡ ዛሬም በቤቱ ይሠራል ፡፡ ኀዘነተኞች ይጽናናሉ ፣ የደከሙ ይበረታሉ ፡፡ ክደው የኖሩ ይጠመቃሉ ፡፡ ዛሬም በዓለሙ ይሠራል ፡፡ ከበደላችን በላይ ምሕረቱ በዝቷል ፡፡ ፀሐይ ይወጣል ፣ ነፋስም ይነፍሳል ፡፡ ከእኛ እንጂ ከእርሱ አልጎደለም ፡፡ ዛሬም ይፍርዳል ፡፡ ገዥዎች ወደ መቃብር ይወርዳሉ ፣ ባለጠጎች ባዶ እጃቸውን ይሸኛሉ ፡፡ ምስኪኖች እንጀራ ይጠግባሉ ፡፡ ዛሬም ይሠራል ፡፡ ብዙ የወለዱ መካንነት ይሰማቸዋል ፡፡ የተነቀፉ የልጆች ወላጅ ሁነዋል ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ